ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ማንኛውም ፖለቲካ ነክ እስሮች በአብይ ዕውቅና አላቸው – መስከረም አበራ

መስከረም አበራ – ከትናንት በስቲያ አብይ አህመድ በህዝብ ያልተወከሉ የፓርቲ ተወካዮች ፊት ቀርቦ፣ ንግግር ሲያደርግ ነበር። ለይስሙላ የቀረቡለትን ጥያቄዎች በተለመደ አፍአዊ ማሽሞንሞኑ ካለፈ በኋላ፣ ስለፍትሕ አካላት ተምኔታዊ ቃል ተነፈሰ። ቃሉ ውሸት የሞላው ነበር። በፖለቲካ አቋም የተለዩትን ወገኖች ስለማሳሰሩ የዘነጋ ይመስል፣ “የፍትሕ አካላት በነፃነት መስራት አለባቸው። ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ማክበር አለበት።” አለ። ይሁን እንጂ አቶ ልደቱ አያሌው በግምት ለአራተኛ ጊዜ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፃሚ ሳይሆንላቸው ቀርቷል። ዳኞቹ “ጦር ቢኖረን፣ ልከን እናስፈታህ ነበር” ያሉት አቅመ-ቢስነታቸውን በመረዳታቸው ነበር። እንግዲህ አብይ የሚዋሽለት የፍትሕ ስርዓት ለዜጎች መሰቃያ እንጂ የትክክለኛ ፍርድ ማግኚያ አልሆነም።
በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ማንኛውም ፖለቲካ ነክ እስሮች በአብይ ዕውቅና አላቸው። አንድ ሰው ከታሰረበት እስከሚሰቃይበት ሰዓት ድረስ ዘርዘር ያለ የስራ አፈፃፀም ለበላይ አካል ይደርሳል። ይህ የበላይ አካል እስረኛ በአደራ አስቀምጦ አንድ ጠባብ እስር ቤት ውስጥ እንዲንገላታ ከአብይ ጋር ተማክሮ ትዕዛዝ ያስተላልፋል፤ ወይም አብይ የበላይ አካሉን ቦታ ተክቶ መመሪያ ያወርዳል። አቶ ልደቱ እየደረሰባቸው ያለው ወደር-የለሽ የፍትሕ መዛባት በዋናነት ከአብይ የመጣ ‘ነው።’ የሚባለው ለዚህ ነው። “የታችኞቹ አመራሮች ናቸው እንዲህ የሚበድሉት” የሚሉ ወገኖችም፣ በዚህ ዘመን ስለተተከለው የአንድ ግለሰብ አምባገነናዊነት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ዘንግተውታል። ሆኖም የአቶ ልደቱ እስር የማንቂያ ደወል ሆኖላቸው፣ እንዲነቁ በተደጋጋሚ እያቃጨለ ነው።
ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬም ነገ ሃገሪቱ በአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ስር እስካለች ድረስ ፍትሕ እና ርትዕ ተቀብረው ይቀራሉ። የሃሳብ ልዩነት የመታሰሪያ ሰበብ ይሆናል። ሌላው ቢቀር፣ ግለሰብን መተቸት ራሱ በ’ስም ማጥፋት’ ክስ ያስቀስፋል። እናም፣ አብይ ፓርላማ ላይ የተናገረው፣ ስለፍትሕ ስርዓቱ ዝንፈት አለማወቁን ለማሳየት ያደረገው ከንቱ ጥረት፤ በአቶ ልደቱ እስር ይበልጥ ተጋልጧል፤ ዛሬም አቶ ልደት የዋስትና መብታቸውን ተከልክለው እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉና።