ወንጀሉን አልፈጸምንም ! ጥፋትም የለንም ! – በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጣሪዎቹ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናገሩ።

BBC Amharic : በአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙት አራቱ ተጠርጣሪዎች ማለትም ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ አለማየሁ እና ላምሮት ከማል እያንዳንዳቸው “ወንጀሉን አልፈጸምንም። ጥፋትም የለንም” በማለት ዛሬ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ይህን ያሉት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕግ እና ጸረ ሽብር ችሎት ዛሬ ረቡዕ በቀረቡበት ወቅት ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ወቅት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የማቆም አቅሙ የለንም ያሉ ሲሆን፤ 4ኛ ተጠርጣሪ ላምሮት ከማል በበኩሏ ጠበቃ ለማቆም ብፈልግም ሊወክለኝ ፍቃደኛ የሆነ ጠበቃ ላገኝ አልቻልኩም ብላ ነበር።

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎቹ መከላከያ ካላቸው እንዲያቀርቡ እና መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ሲል ውሳኔ አስተላልፎ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በዚሁ መሠረት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች የተመደቡ ጠበቃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ይሁን እንጂ የተመደቡት ጠበቃ የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20.5ን በመጥቀስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ላሉት ተከሳሾች መቆም እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ 4ኛዋን ተከሳሽ [ላምሮት ከማልን] ግን ለመወከል የተሰጣቸው ውክልና እንዲነሳ ጠይቀዋል።

ስለተከሰሱ ሰዎች በሚያትተው አንቀጽ 20.5 ተከሳሾች በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው ይላል።

ጠበቃውም አረተኛዋ ተከሳሽ ፍቃደኛ ሆኖ የሚቆምላት ጠበቃ አጣች እንጂ ጠበቃ የማቆም አቅም አላነሳትም ስለዚህም “ውክልናችን ትክክል አይደለም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ መንግሥት የመደባቸው ጠበቃ አራተኛዋ ተከሳሽንም እንዲወክሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በሌላ በኩል የተከሳሾች ጠበቃ ተከሳሾቹ የክስ መከላከያ እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግም ፖሊስ መስክሮችን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጠ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ግን ዐቃቤ ሕግ ራሱ መስክሮቹን ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ አዟል። በዚሁ መሠረት ከኅዳር 23 እስከ 25/2013 ዓ.ም ምስክሮቹን ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተዕእዛዝ ሰጥቷል።

አራቱ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንጽ 32/1 ሀ እና ለ አንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3/2 በመተላለፍ መከሰሳቸው ይታወሳል።

ታዋቂው የኦሮምኛ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለፈው ዓመት ሰኔ 22/2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ምሽት ላይ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉን ይታወሳል።

የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እና አለመረጋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸው እና በሺዎቹ የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።