በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለንና ወንበራ ወረዳዎች የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን ለመጥቀስ ያልፈለጉ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንዳመለከቱት ከአንድ ወር ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በተለይ በቡለንና ወንበርማ ወረዳዎች በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡
ታጣቂዎቹ ህንፃ ማፍረስ የሚችል መሳሪያ እንደታጠቁ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የፀጥታ ኃይሉ ለመከላከልና ተከታትሎ ለመያዝ ቢሞክርም አስቸጋሪ መሆኑንና በአንድ አቅጣጫ ሲታዩ በሌላ አቅጣጫ በመምጣት በሰው ልጅ ሊፈፀም የማይገባው ጥቃት እየፈፀሙ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የሚፈፅሙት በቀን እንደሆነና ከአንዳንድ የመንግስት መዋቅር አካላት ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችልም ገምተዋል፤ ምክንያታቸውን ሲገልፁም «ታጣቂዎች ወደነበሩበት አካባቢ የፀጥታ ኃይል ሲንቀሳቀስ ቀድሞ መረጃ ስለሚደርሳቸው አካባቢውን ለቅቀው ይሰወራሉ » ብለዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ በርካታ የቆሰሉ፣ ህይወታቸው ያለፈ ነዋሪዎች መኖራቸውንና ከታጣቂ ሀይሉ በኩልም በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱን ስለሁኔታው ማብራሪያ እንዲሰጡን ስልክ ቢደወልላቸውም ፤ መረጃ በተንቀሳቃሽ ስልክ እንደማይሰጡ ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የሚመለከታቸውን የቤኒሻንጉል ክልል ኃላፊዎችን ለማግኜት ጥረት ቢደረግም ስልካቸው ባለመነሳቱ ሊሳካ አልቻለም።
——————
በመተከል ዞን ከታጣቂ ሀይሎች ጥቃት እራሳቸውን ለመጠበቅ በሚል በጫካ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ ከ300 በላይ ዜጎች ወደ ቄያቸው ተመለሱ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በታጣቂ ሀይሎች ከተሰነዘረው ጥቃት ሸሽተው በጫካ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ 12 የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ 310 በላይ ንፁሀን ዜጎች በፌደራልና በክልል የፀጥታ ሀይሎች በተሰራ ኦፕሬሽን ወደ ቄያቸው መመለሳቸው ተገለፀ፡፡
በቅርቡ ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ኤርታል ቀበሌ ላይ በታጣቂ ሀይሎች በተሰነዘረ ጥቃት የአካባቢው ሰላማዊ ሰዎችን እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ወደ ጫካ ተበታትነው እንደነበረ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ጃራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት 12 የጤና ባለሙያዎች እና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በወቅቱ ከተፈጠረው ጥቃት በመሸሽ በጫካ ውስጥ እራሳቸውን ደብቀው መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
ሆኖም በፌደራልና በክልል የፀጥታ ሀይሎች በተሰራ ኦፕሬሽን በህይወት ተገኝተው ወደ ቀበሌያቸው እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር 300 የሚሆን ንፁሀን የማህበረሰብ ክፍሎች በተመሳሳይ ከጥቃቱ ሸሽተው በቀበሌው በቅርብ እርቀት ወደሚገኝ ጫካ እራሳቸውን የሸሸጉ መሆኑን ገልፀዋል ም/ል ኮሚሽነር ነጋ
እነዚህንም ዜጎች ወደ ቄያቸው መመለስ መቻላቸውን እና ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹን የመደምሰስ ስራው በመካሄድ ላይ ነው ያሉት ኮሚሽነር ነጋ በጫካ እራሳቸውን የደበቁ ንፁሀን ዜጎችን ወደ ቄያቸው የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ነግረውናል፡፡
ሙሉ በሙሉ የኦፕሬሽን ስራው እንደተጠናቀቀ በተደራጀ መልኩ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ የተፈጠረውን ተመሳሳይ ጥቃት ለመቀልበስ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሀይሎች ገብተው የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሙሉ የኦፕሬሽን ስራው እንደተጠናቀቀ መረጃው ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡
በመተከል ዞን ቡለን እና ወንበራ ወረዳ ላይ የፀጥታ ችግር ከመከሰቱ በፊት በጉባ ወረዳም እነዚህ የታጠቁ ሀይሎች ገብተው በንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀምረው እንደነበር ይታወቃል፡፡