ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ጋምቤላ ክልል በጎርፍ መጥለቅለቅ ተፈናቅለዋል

ጋምቤላ፦ በዐሥር ሺህዎች በጎርፍ መጥለቅለቅ ተፈናቅለዋል – DW
ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ ውስጥ በጎርፍ መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ዐስታወቁ። የጎርፍ መጥለቅለቊ አደጋ የተከሰተበት ወረዳው ኢትዮጵያን ከሱዳን በሚያዋስን አካባቢ ነው፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ ቤት ከተፈናቃዮች መካከል ወ/ሮ ኛዳክ ፓችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰሞኑን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክናያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከነቤተሰቦቻቸው በትምህርት ቤት አጥር ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። መንግስት የአልባሳትና የምግብ አቅርቦት ባለማድረጉም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ወ/ሮ ኛዳክ ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የላሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋርዊች ቢየል በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሱዳንንና ኢትዮጵያን የሚያዋስነው ጂካዎ ወንዝ ሞልቶ በተፈጠረው ችግር ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ የሚኖሩትም በትምህርት ቤቶች እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
እንስሳት እንደሞቱና የግጦሽ ሜዳዎችም በጎርፍ በመሸፈናቸው እንስሳቱም ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸውን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡ አደጋው ከጳጉሜ ጀምሮ የተከሰተ ሲሆን ከክልል ርዳታ እንዲቀርብ ሪፖርት ቢደረግም ጉዳቱን መጥቶ ከመመልከት ውጪ እስካሁን ምንም እርዳታ እንዳልተገኘ ገልፀዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ ሰይፉ ወልዴ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአካባቢው ሰዎች አኗኗር ለእንደዚህ ዓይነት አደጋ እንደሚያጋልጥ አመልክተዋል። በመሆኑም ሰሞኑን በአካባቢው የጎርፍ መጥለቅለቅ መድረሱን አመልክተው የተጠቀሰው የርዳታ ፈላጊ ቁጥር ግን የተጋነነ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሆኖም ርዳታ ወደ አካባቢው ለመላክ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። በዘንድሮው ክረምት በተለያዩ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጎርፍና ናዳ በመፍጠሩ በርካቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።(DW)
ፎቶ፦ የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት