በጎረቤት አገራት ያለ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ብር ባለበት እንዲመክን ይደረጋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • ብር ለመቀየር የሚሄድ ሰው በራሱ ስም የባንክ አካውንት ይከፍታል
አዲስ ዘመን – ከብር ኖት ለውጡ ጋር ተያይዞ ሊፈጸሙ የሚችሉ ህገወጥ ድርጊቶችን ከመከላከል አኳያ በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ብር ለመቀየር የሚሄዱ ሰዎች በራሳቸው ስም የባንክ አካውንት እንዲከፍቱ የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገለፀ።በተመሳሳይ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ብር በጎረቤት አገራት ያለ እንደመሆኑ ይህ ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ እና ባለበት እንዲመክን እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የብር ኖት ለውጡ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ነው፡፡ ከብር መቀየር ጋር በተያያዘ ውክልና የማይቻል ሲሆን፤ ሰዎች ብር ለመቀየር ሲመጡ በራሳቸው ስም አካውንት እንዲከፍቱ ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ በጎረቤት አገራት ያለው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ብር ህገ ወጥ እንደመሆኑ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ እንዲመክን ይደረጋል፡፡
እንደ ዶክተር ይናገር ገለጻ፤ ህትመቱን በተመለከተ በቁጥር 2ነጥብ9 ቢሊዮን ሲሆን፣ በመጠን ሲገለጽ ደግሞ 262 ቢሊዮን ይገመታል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረው በጣሙን ከዚህ ያነሰ ነው፡፡
መጠባበቂያ ጭምር እንዲታተም ተደርጓል፡፡ ለዚህ ሁሉ 3ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ለብር ለውጡም ቢሆን በቂ ገንዘብ አለ፡፡
ከገንዘብ ለውጥ ጋር ተያይዞም በባንኮች የሚፈጸም ጥፋት ካለ እንደ ጥፋቱ እየታየ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ቀደም ሲል የወጡ መመሪያዎች ከአዲስ የብር ህትመት ጋር ተዳምረው የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
ከለውጥ ጋር በተያያዘም ብር ለመቀየር ይዞ የሚሄድ ሰው በራሱ ስም ነው የባንክ አካውንት የሚከፈተው፡፡ በውክልና አይቻልም፡፡ የራሳቸው ያልሆነ ብር ይዘው የሚሄዱና በሌላ ሰው አካውንት ውስጥ ገንዘብ ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይሄንን ማስቀረት ስለሚገባ ነው እያንዳንዱ ብር ለመቀየር የሚሄድ ሰው መታወቂያውን አሳይቶ አካውንት እንዲከፍት የሚደረገው እና ብር የመቀየር ስራውን የሚሰራው፡፡
በተመሳሳይ በህገ ወጥ መልኩ ያለን ብር መቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አቶ ይናገር ጠቅሰው፣ በተለይ በድንበር አካባቢ ያለውን ዝውውር ከመከላከል አኳያ የፀጥታ አካላት ስራውን እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ የጸጥታ አካላቱ ለዚህ የሚሆን የሰው ሃይል በማደራጀት ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡
በጎረቤት አገራት ከፍተኛ የኢትዮጵያ ብር እንዳለና ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ህገ ወጥ ስለሆነም ባለበት እንዲመክን እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ይሄንንም ለማድረግ የሚያስችል በቂ ዝግጅት በጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ እንዳለም አስታውቀዋል፡፡
በድንበር አካባቢ ያሉ ባንኮች ወደዚህ ህገ ወጥ ስራ ውስጥ እንዳይገቡ ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር ተነጋግረናል ያሉት የባንኩ ገዥ፣ በድንበር አከባቢ ህገ ወጥ ገንዘብ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከጸጥታ ሃይሉ በተጨማሪ ህብረተሰቡ፣ በየአካባቢው ያሉ የአስተዳደር አካላትም የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዘበው፣ ለዚህ ደግሞ የተቻለውን ያህል ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
ዶክተር ይናገር እንዳብራሩት፤ እነዚህ ብሮች በቀለም፣ በመጠን፣ በደህንነት መጠበቂያና ሌሎችም ተቀይረዋል፡፡ ባለ ሁለት መቶው ኖት ደግሞ እንደ አዲስ የመጣ ገንዘብ ነው፡፡
እነዚህ የብር ኖቶች ሌላው ለየት የሚያደርጋቸው ቀደም ሲል በዐይነ ስውራን ይነሳ የነበረውን ቅሬታ በሚቀርፍ መልኩ ዐይነ ስውራን የሚለዩአቸው ምልክቶች በሁሉም የብር ኖቶች ላይ በሁለቱም ጠርዝ ላይ ተቀምጠውበታል፡፡
በአጠቃላይ ይፋ የተደረጉት አራት የብር ኖቶች ከፍተኛ የደህንነት መጠበቂያ አላቸው ፤የአምስት ብር ኖት ለጊዜው ባለበት የሚቀጥል ሆኖ በሂደት ወደ ሳንቲም የሚቀየር ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን