ህወሓት ትግራይ ምክር ቤት ካለው 190 መቀመጫዎች ውስጥ 189ኙን በማግኘት አንዱን ለተቃዋሚዎች ሰጥቷል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBC Amharic : ባለፈው ሳምንት ትግራይ ክልል ከተካሄደው ምርጫ ተርፈው ከነበሩትና በተመጣጣኝ ውክልና እንደሚከፋፈሉ ከተገለፀው 38 የምክር ቤት መቀመጫዎች ህወሓት 37.35ቱን ማግኘቱ ተገለጸ።

በዚህም መሰረት የክልሉ ምክር ቤት ካለው 190 መቀመጫዎች ውስጥ 189ኙን በማግኘት ከአንድ መቀመጫ በስተቀር ሁሉንም መውሰዱን ምርጫ ኮሚሽነሩ መምህር ኪዳነማርያም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

በምርጫው ከተሰጠው አጠቃላይ 10 ሚሊዮን 840 ሺህ 159 ድምጽም ህወሓት 10 ሚሊዮን 655 ሺህ 840 የመራጮች ድምጽ በማግኘት፣ አጠቃላዩን በሚባል ደረጃ የምክር ቤቱን ወንበር ተቆጣጥሮታል።

በክፍፍሉ ቀመር መሰረት 0.65 ድምጽ ያገኘው ባይቶና የተባለው ፓርቲ ቀሪዋን ብቸኛ አንድ ወንበር እንደሚወስድም ተገልጿል።

በተመጣጣኝ ውክልና እንደሚከፋፈሉ ከተገለጹት 38ቱ የምክር ቤቱ መቀመጫዎች ከተሰጡት የመራጮች ድምጽ አንጻር የአንዱ ወንበር ውክልና 285,267.3 የነበረ ሲሆን ከህወሓት ውጪ ይህን ያህል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ የለም።

በምርጫው ከተሳተፉት አምስት ፓርቲዎች መካከል ክልሉን በብቸኝነት ላለፉት 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ያስተዳደረው ህወሓት 10,655,840 ድምጽ፣ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነው የቀረቡት አዳዲሶቹ ፓርቲዎች ባይቶና 93,495 ድምጽ፣ የትግራይ ነጻነት ድርጅት 58,779 ድምጽ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ 27, 987 ድምጽ እና ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ደግሞ 3,088 ድምጽ አግኝተዋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ጳጉሜ 04/2012 ዓ.ም በተካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 2,789,254 መራጮች ውስጥ 2,757,495 ሕዝብ በምርጫው ላይ ተሳትፏል ተብሏል። ይህም 98.8% እንደሆነ ተመልክቷል።

በተጨማሪም ድምጽ ከሰጡ መራጮች መካከልም 31,759 ድምጽ ለየትኛውም ተወዳዳሪ ሳይሆኑ የባከኑ እንደሆነ መመዝገቡን ኮሚሽኑ አሳውቋል።

በመላው አገሪቱ በነሐሴ ወር ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ተወሰነ ቢሆንም፤ የትግራይ ክልል ግን በተናጠል ምረጫውን ለማካሄድ በመወሰኑ ሲያወዛግብ ቆይቶ ነበር።

በዚህም መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ሕገ ወጥና ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ ከምርጫው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው መግለጹ ይታወሳል።