የዳግማዊ አጼ ምኒልክ 176ኛ እና የእቴጌ ጣይቱ 180ኛ የትዉልድ ቀን


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የትዉልድ ቀን

ግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ቅዳሜ ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ ዓ.ም. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሱ።

አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጁን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር ‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ ይላል ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፉ (ገጽ ፲፪)

ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ።አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱ የሸዋውን አልጋ የምኒልክ አባት ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ወረሱ።

ዓፄ ተዎድሮስ በጥቅምት ወር ፲፰፻፵፰ ዓ/ም ትግራይንና ወሎን አስገብረው፣ አቤቶ ምኒልክ ገና የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ፤ የድፍን አማራንና የወሎን ጦር አስከትተው የሸዋውን ንጉሥ ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ሸዋ ገቡ። ሁለቱ መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ተዘጋችተው ሲጠባበቁ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ባደረባቸው ሕመም ጥቅምት ፴ ቀን አረፉ። በዚህ ጊዜ የሸዋ መኳንንት ሕጻኑን ምኒልክን ከጠላት እጅ እንዳይወድቅባቸው ይዘው ሸሹ፤ ዳሩ ግን ዓፄ ቴዎድሮስ እንደሚከታተሏቸው ስላወቁ ኅዳር ፴ ቀን ፲፰፵፰ ዓ/ም የልጅ ምኒልክ ሠራዊትና የዓፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በረከት ላይ ገጥሞ የምኒልክ ሹማምንት እነአቶ በዛብህ፣ እነአቶ አንዳርጋቸው ሁሉ ተያዙ። ልጅ ምኒልክም ለቴዎድሮስ ገባ።

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ (ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ እስከ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ.ም.) ከ፲፰፻፶፯ እስከ ፲፰፻፹፪ ዓ/ም የሸዋ ንጉሥ ከዚያም ከ፲፰፻፹፪ እስከ ፲፱፻፮ ዓ/ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ።

የእቴጌ ጣይቱ የትዉልድ ቀን

Tayitu.JPGጣይቱ ብጡል «ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል ቅፅል ስም የታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብ ዳር ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፪ ዓ/ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ።

በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሠረት በተወለዱ በ ፹ ቀናቸው ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፰፻፴፫ ዓ/ም በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊትን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቁ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የተማሩባቸውም መፃሕፍት ተጽፈው ይገኙ የነበረበትን የግዕዝ ቋንቋ አጣርተው ያውቁ ነበር። እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ከባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የዓፄ ቴዎድሮስን ባለሟል አግብተው ነበር።

እሳቸውም ጣይቱ ብጡል ትምህርት እንዲቀስሙ ለማድረግ ልዩ መምህር ቀጥረውላቸው እንደነበር ይታወቃል። እቴጌ ጣይቱ በማኅደረ ማርያም ሆነው ሲማሩና መፃሕፍትን ይቀጽሉ በነበሩበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ እንደነበሩ ይተረክላቸዋል።