ተግባራዊ እንቅስቃሴ- አንድ ዶላር በቀን  #ግርማ_ካሳ

ትላንት ዶ/ር አብይ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ለዳያስፖራው ጥሪ አስተላልፈዋል። አንድ ሚሊዮን ሊሆን የሚችል ዳያስፖራ በቀን አንድ ዶላር ቢሰጥ፣ በወር ሰላሳ ሚሊዪን ዶላር እንደሚሆን የገለጹት ዶ/ር አብይ ያ ገንዘብ ትልቅ ስራ እንደሚሰራ ነው ያስረዱት።የዶ/ር አብይ ንግግር “ከዳያስፖራው ተግባራዊ መደመር ያስፈለጋል” በሚል  ርእስ ቀደም ሲል በብዙ ድህረገጾ በወጣዉና ብዙዎች ባነበቡት አንድ ጽሁፌ ጋር በጣም ተመሳሰለብኝ።፡ ዶ/ር አብይ ወደ አሜሪካ ሲመጡ ፣ ከዳያስፖራው ጋር ተነጋግረው፣ ሆ ተብሎ ብቻ መለያየት ሳይሆን ተግባራዊ መደመር አስፈላጊ እንደሆነ በገለጽኩበት ወቅት አንድ ሚሊዮን የሚሆን ዳያስፖራ ፣ አንድ ዶላር ቢሰጥ እያልኩ ኢሰሩ የሚችሉትን በምሳሌ አቅርቤ ነበርና።

የተጨበጡ፣ ዳያስፖራው ሊሰራቸው ከሚችላቸው ተግባራዊ እንቅሳሴዎች መካከል የተወሰኑትን አስቀምጫለሁ። ቢያንስ በአራት አመት ተኩል ውስጥ ዳያስፖራው በመጀመሪያው አመት በቀን አንድ ዶላር፣ በተቀሩት ሶስት አመት ተኩል ደግሞ ሁለት ዶላር ቢያዋጣ የአዲስ አበባ መለስተኛ፣ የጅቡቱ-አዲስ፣ የአዋሽ፣ ወልዲያ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶችን ወጪ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት እንደሚችል ንበር የገለጽኩት።

ወገኖች አቅሙ አለን። ያለ ምንም ጥርጥር ይሄን ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ ማድረግ እንችላለን። ትልቁ ነገር ሕዝብን ማነሳሳትና የተነሳሳው ህዝብ ለስራ እንዲሰማራ በቂ፣ ግልጽ፣ ጥራት ያለው አሰራርን መዘርጋት ነው።

  1. ዶ/ር አብይ የተለየ ፈንድ እንደሚዘጋጅ፣ በሁሉም አገሮች ዜጎች በቀላሉ ገንዘብ መልክ እንዲችሉ አካዉንቶች እንደሚከፈቱ ገልጸዋል።በዚህ መልኩ ማንም ኢትዮጵያዊ አካባቢዊ ባለው ባንክ በኩል ድጋፉን ማስገባት ይችላል።
  2. ይሄን ፈንድ የሚቆጣጠርና ማኔጅ የሚያደርግ ኮሚሽን እንደሚቋቋም ነው ዶር አብይ የገለጹት። ይሄ ጥሩና አስፈላጊ ዉሳኔ ነው። በዚህ ረገድ ይሄ ኮሚሽን ከኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበራት፣ የእምነት ተቋማት ጋር አብሮ በመስራት ሕዝቡ ጋር በተገቢ መልኩ መድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል ባይ ነኝ። ገንዘብ አዋጡ ብቻ ማለት አይሰራም። ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት  ፈልገው ማግኘት፣ ጨዋነትና ትህትና በተሞላበት መልኩ ማሳመን፣ ማግባባት አስፈላጊ ነው።
  3. ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ቆንስል መስሪያ ቤቶች ሚና ቀላል አይደለም የሚሆነው። በመሆኑም በዚያ የሚቀመጡ ወገኖች በተቻለ መጠን በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው፣ የድርጅት አባል ብቻ ስለሆኑ የተቀመጡ መሆን የለባቸውም። ቢቻል ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስተር ከመሆናቸው በፊት የተሾሙ አማብሳደሮች ቢቀየሩ በጣም ጠቃሚ ነው። ትንሽም ብትሆን ኢትዮጵያዉያን ገንዘብ እንዳይረዱ እንቅፋት የሚሆንባቸውና፣ ጥያቄ የሚፈጥርባቸው ከሆነ ትንሿን ነገር ገለል ማድረግ አስፈላጊ ነው።
  4. በገንዘብ አሰባሰቡ ዙሪያ ፣ ለምሳሌ በአሜሪካ የራሱ የሆነ ሕግ አለ። በተቻለ የገንዘብ ማሰባሰቡ የአሜሪካን ሕግ በጠበቀ መልኩ እንዲሰራ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።

አንዳንድ ወገኖች “ኢትዮጵያ እዳ ያለበት ወያኔዎች ስለዘረፉ ነው። እነርሱን ማስመለስ ያስፈልጋል” ይላሉ።፡ትክክል ናቸው። ከሕዝብ የተዘረፉ ገንዘቦችን የማስመለስ ስራ መሰራት አለበት። ለዚህ ራሱን የቻለ ሌላ ኮሚቴ ወይም ኮሚሽን መቋቋም ነው የሚኖርበት። ባለስልጣናቱ እነማን ናቸው ?  ምን ያህል ገንዘብ ነው የተዘረፈው? የየት አገር ባንክ ነው ገንዘቡ የተቀመጠው ? ….የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የማጣራት ፣ ከዚያ በየአገራቱ ክሶችን የመመስረት..ስራዎች መሰራት አለባቸው። ቀላል ስራ አይደለም። ይሄ ስራ እስኪጠናቀቅ እኛ እጅ አጣምረን እንቀመጥ ማለት ስህተት ነው።

አንዳንዶች ደግሞ ሁላችንም በየተወለድንበት የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ እንሰማራ የሚሉ አሉ።፡ያም ተገቢ ነው። በአመት ከመቶ ሺህ ዶላር በላይ ደሞዝ የሚያገኙ አንድ ሺህ የሚጠጉ የጎንደር ልጆች ወይም ኦሮሞዎች እንጠፋለን ብዬ አላስብም። ከመቶ ሺህ  አንድ ሺህ ዶላር ቢመድቡ አንዳ፣ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሆናል። በአንዳንድ ሚሊዮን ዶላር፣ለአስር የጎንደርና የወለጋ ሆስፒታሎች ቢያንስ አንድ አንድ የ መሳሪያዎችን መግዛት ይቻላል። መቶ ሺህ ለሚያገኝ አንድ ሺህ ለአካባቢው 360 ደግሞ በአገር ደረጃ ለባቡር ግንባታዎች ቢሰጥ ብዙ አይሆንበትም። ጠቅለል ሳደደርገው፣ በአገር ደረጃ የምንሰራውን እንደ አንድ ኧግር ሕዝብ ተሰባሰብን እያደረግን በተወለድንባቸው አካባባቢዎች በተጨማሪ መስራት እንችላለን። አንዱ ሌላውን አይተካም። ሁለቱም አብረው መሄድ ይችላሉ። እንደው በጣም የሚበረታታ ነው።

ከማዋጣጡን በተጨማሪ አገርንና ሕዝብን የሚረዱ ቀላል የሚመስሉ በርካታ ስራዎችም አሉ።፡ከነዚህ መካከል ፡

  • ወደ ቤተሰቦቻችን ስንል በቀጥታ በባንክ ብንልክና የጥቁር ገበያ ሙሉ ለሙሉ የሚቆምበትን መንገድ ብንፈልግ ጥሩ ነው። በአገር ቤት ያላችሁም ጥቁር ገበያን አትጠቀሙ።
  • በአገር ቤት በተቻለ መጠን አገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶች ካሉ እነርሱን እንጠቀም። ዊስኪ ከምንጠጣ ጠጅ፣ ጂንስ ከምንለብስ ካኪና የአገር ባህል ጃኖ እንልበስ።
  • ወደ አገር ቤት ስንመላለስ በተቻል መጠን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንጠቀም።
  • ወዳጄ ልጅ ተክሌ አንድ ሀሳብ አቅርቢ ሰማሁ። በየአመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያዉያን እገር ኳስ ዉድድር ከዚህ በኋላ በአገር ቤት ማድረጉ ጠቃሚ ነው። የ እግር ኳስ ዉድዶች ሲደረጉ፣ አዘጋጅ ከተማዎች በጣም ይጠቀማሉ። ሲያትል፣ ዳላስ፣ ዲሶ ….ኢትዮጵያዊያን በነዚህ ከተሞች ብዙ ዶላር ነው የሚያፈሱት። እስቲ እነዚህ ዶላሮች አዋሳ፣ ባህር ዳር፣አዳማ ..ብናፈሳቸውስ ?