‹አባይ የግብጽ የተፈጥሮ (የአላህ) ስጦታ ነው›› የሚለውን የውሸት ትርክት ለዓለም አቀፍ ተቋማት መናገርና ማቅረብ የዜግነት ግዴታ ነው – ኡስታዝ አቡበከር አህመድ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“በዓባይ ጉዳይ የግብጽ አቋም ስህተትና ስግብግብነት የተሞላበት ነው›› – ኡስታዝ አቡበከር አህመድ
(አዲስ ዘመን ) – ኢትዮጵያውያን በዓባይ ዙሪያ የግብጽን የውሸት ትርክት በማጋለጥ እውነታውን ለዓለም ኅብረተሰብ ማሳወቅ እንደሚገባቸውና በዓባይ ጉዳይ የግብጽ አቋም ፍጹም ስህተት የሆነና ስግብግብነት የተሞላበት ነው ሲሉ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ተናገሩ።
ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በአባይ ወንዝ እንደ ባለቤት ያጣነውን መብት፣ በአልሲሲ መንግሥት እየተፈጸመ ያለውን ደባና ‹‹አባይ የግብጽ የተፈጥሮ (የአላህ) ስጦታ ነው›› የሚለውን የውሸት ትርክት ለዓለም አቀፍ ተቋማት መናገርና ማቅረብ የዜግነት ግዴታ ነው።
ማንኛውም ዜጋ ያለማንም ቀስቃሽ የአገሩ አምባሳደር መሆን እንዳለበትና የዜግነት ግዴታውእንደሆነም የጠቆሙት ኡስታዝ አቡበከር በውሸት የፖለቲካ ሴራ የሚያሴሩትን አካላት በተገኘው አጋጣሚ ለዓለም ማህበረሰብና ተቋማት ማጋለጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ግብጻውያን በዩኒቨርሲቲዎቻቸው የሚገኙ ታላላቅ የእስልምና እምነት አስተማሪዎችን ጭምር የእስልምና መርሆችንና ሕግጋትን ጥሰው ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ‹‹አላህን›› ሳይፈሩ እየዋሹ እንዳሉና በኢትዮጵያ ላይ በደል ማድረሳቸውንም በእውነተኛ ማስረጃዎች አስደግፎ ማጋለጥ እንደሚገባ ኡስታዝ አቡበከር አስታውቀዋል፡፡
ኡስታዝ አቡበከር በገለጻቸው፤ ግብጻውያን በዓባይ ጉዳይ ላይ የያዙት የተሳሳተ ትርክት ዋና ምክንያት በትምህርት ቤት ሥርዓተ ትምህርታቸው በማካተት ለዜጎቻቸው ከሕፃንነታቸው ጀምረው ግንዛቤ በመፍጠራቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ለዓለም ማህበረሰብና ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ውሸትን ሰብከው ወደ እውነት ደረጃ በማድረሳቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኡስታዝ አቡበከር በኢትዮጵያ በኩል ይሄንን የውሸት ትርክት በመገልበጥ ስለ ዓባይ ጉዳይ እውነታውን የማስተዋወቁ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ያለአግባብና ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተሰራ ያለውን ደባ ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅም እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ ኡስታዝ አቡበከር ገለጻ፤ የግብጽን የእኔ ብቻ ልጠቀም አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለው ሲያብራሩ፤ ከ‹‹ቁርዓን ቀጥሎ የነብዩ መሐመድ (ሱ.ዐ.ወ) የሐዲስ ምንጭ በሆነው ‹ሰሂህ ቡኃሪ ሐዲስ› ላይ እንደተገለጸው ሁለት ሰዎች አትክልት በሚያጠጡበት ውሃ ተጋጭተው፣ ከታች ያለው ሰው ከላይ ያለውን ቅድሚያ ለእኔ ይልቀቅልኝ በሚል ይከስሰውና ፍትህ በመፈለግ ከነብዩ መሐመድ (ሱ.ዐ.ወ) ፊት ይቀርባሉ፡፡
ነብዩ መሐመድ (ሱ.ዐ.ወ)ም ጥያቄህ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ከምንጩ አጠገብ ያለው ቅድሚያ ሊጠቀም ይገባዋል፡፡ አጠጥተህ ሲበቃህ ልቀቅለት፡፡ ከምንጩ መነሻ ያለው ሳያገኝ እንዴት እሱን አልፎ ከእኔ ይድረስ ትላለህ? በሚል ተቆጥተውና ገስጸው በፍትሃዊ መንገድ መፍትሄ ሰጥተዋቸዋል ሲሉ የኢትዮጵያ በወንዙ ውሃ ፍትሃዊ የመጠቀም መብት በእስልምና አስተምሮ ጭምር የሚደገፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግብጽ መንግሥት ያለአግባብና ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተሰራ ያለውን ደባ እና የውሸት ትርክት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ የዜግነት ግዴታ እንደሆነም ኡስታዝ አቡበከር አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን