ሕወሓቶች ከኢትዮጵያ ትርምስ አንድ ነገር ይወድቅልናል የሚለው ቀቢፀ ተስፋቸው እውን ይሆናል ብዬ አላምንም – አቶ አስራት ጣሴ

እኔ ህውሓት በአሁኑ ወቅት ጣር ውስጥ የገባ ይመስለኛል። በሁለት መንገድ የተሳለ ሰይፍ መሃል የቆመ ነው የሚመስለኝ። የሚያመጡት ሃሳብ ሁሉ መልሶ የሚበላቸው እንጂ እድል የሚሰጣቸው አይደለም። ከጥፋታቸው ተምረው አይመለሱም። ከዚህ በኋላም ይመለሳሉ ብዬ አላምንም።
በተአምር ግን መልካምነት ቢመጣ ለትግራይ ህዝብም የሚበጅ ስለሆነ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። በነገራችን ላይ ህውሓትን አንድም ቀን ከትግራይ ህዝብ ጋር አይቼው አላውቅም። የትግራይ ህዝብ የሚከበር፤ የኢትዮጵያ ታሪክ መሰረት ነው። የአክሱም ታሪክ መሰረት ነው። ኢትዮጵያዊነትን ከማንኛው ህዝብ በላይ የሚመለከት ነው። ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ቀንአዊነት ከፍተኛ ነው።
ህወሃት አሁን ላይ ዝም ብሎ አንድ ተዓምር የሚጠብቅ ይመስለኛል። አሁን ያለበትም ሁኔታ ሆነ የጫካ ታሪኩ የሚያሳየው ድርጅቱ ራሱ መቅሰፍት የሚደርስበት መሆኑን ነው። ይህንን የምልሽ ግን ከትግራይ ህዝብ ለይቼ ነው።
ህገመንግሰቱ እኮ የክልልም ሆነ አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ የሚችለው ምርጫ ቦርድ መሆኑን ይደነግጋል። ስለዚህ ለምርጫ ቢካሄድም ውጤቱ ተቀባይነት የለውም፤ የተመረጡ ሰዎች በማዕከላዊ መንግስት ቦታ አይኖራቸውም፤ ለእነዚያ ሰዎች የሚላክ በጀት አይኖርም።
የሚከፈልም ደመወዝ አይኖርም። ምክንያቱም እውቅና የለምና ነው። ህውሓቶች ግን ይህንን ነገር ከግምት ውስጥ አግብተውታል ብዬ አላስብም። ይልቁንም የምርጫ መራዘም ከማንም በላይ እነሱን ነው የሚጠቅመው ባይ ነኝ።
ምርጫው ሲራዘም የእነሱም የሥልጣን ጊዜ ይራዘማል ማለት ነው። ይህ አንድ መውጫ በር ነበር፤ ግን ይፈሩታል፤ በጎ መስሎ እንዳይጎዳቸው ይሰጋሉ። አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ እየተነቃነቀ ነው፤ የወረዳ ጥያቄ በብዛት እየተነሳ ነው። ከአድዋ አመራር ሊሾምልን አይገባም እያሉ ነው።
ወጣቶች በሰበብ እየተገደሉ ነው። እነዚህ ሰዎች የትግራይ ህዝብ ጎትቶ ያወጣናል የሚል አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ናቸው። ምክንያቱም ህውሓት እንደፓርቲ አለ ለማለት ይቸግረኛል፤ አሁን ያለበት የጣር ጊዜ ከሞት የሚያድናቸው አይመስለኝም፤ ቀናትን ይቆጥራሉ እንጂ ፤ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ትርምስ አንድ ነገር ይወድቅልናል የሚለው ቀቢፀ ተስፋቸው እውን ይሆናል ብዬ አላምንም። ላይ ናቸው።
ይህንን የሚሉት ሰዎች ራሳቸው ህገ መንግስቱን ሲጥሱ እኮ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀፅ 103 ላይ በየአስር ዓመቱ የህዝብ ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የህዝብ ቆጠራውና የ 1997ቱ ምርጫ አንድ ላይ በመዋሉ ህውሃት /ኢህአዴጎች ሁለቱንም አንድ ላይ ማካሄድ አይቻልም በማለት የህዝብ ቆጠራውን ዘለውታል። ያን ሲያደርጉ እኮ የህግ መንግስት ትርጉም አልጠየቁበትም። ለነገሩ አምባገነን ስለሆኑ ማን ይጠይቀናል፤ ማን ይናገረናል? በሚል እንደሆነ ይታወቃል።
ዛሬ ደግሞ በኮቪድ በሽታ ዓለም እንዲህ በመላው ዓለም ከ50 በላይ አገሮች የተለያዩ ምርጫዎች ያሸጋገሩበት ወቅት ነው። እነዚህ ሰዎች ናቸው ታዲያ «ህገመንግስት ተሸረሸረ» ብለው የሚጮሁት!።
ሌላ አንድ ምሳሌ ላንሳ አቶ ቃሲም ፊጤ የሚባል የኦሮምያ ክልል ተወካይ የፓርላማ አባል የነበረ አንድ ወቅት በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ያለመከስስ መብቱ እንዲነሳ ተጠይቆ ነበር። ፓርላማው በሆነ አጋጣሚ ሳይሰበሰብ ይቅርና ያለመከስስ መብታቸው ሳይነሳ ይቀራል። በማግስቱ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማው ተሰብስቦ እንዲነሳ አስደረጉ።
ይህንን ነው እንግዲህ ህገመንግስት ማክበር የሚሉት! ሌላም አንድ ምሳሌ ልጨምርልሽ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠው ሲመጡ አቶ መለስ ግን ሂዱና ተመልሳችሁ ሌላ ምረጡ ብሎ ነው አቶ አለማየሁ አቶምሳ እንዲሾሙ የተደረጉት።
እንዲህ አይነት አምባገነን በኖረበት አገር ህገመንግስት ነበር፤ ህገመንግስት መከበር አለበት ብለው ሲጮሁ በምን አንደበታቸው እንደሚናገሩ ይገርመኛል። እንዴት ይሉኝታ እንደጠፋባቸውና ህሊናቸውን እንደሳቱ ማስተዋልም ይቻላል።
ለሙሉ ቃለምልልስ https://www.press.et/Ama/?p=32918