የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ ከጠበቅነው በላይ የተሳካ እና ፈር ቀዳጅ ነበር – ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ

“ጉባኤው ከጠበቅነው በላይ የተሳካ እና ፈር ቀዳጅ ነበር”- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት
በቀጥታ ለህዝብ እንዲተላለፍ የተደረገው መድረክ ከተጠበቅነው በላይ የተሳካ እና ፈር ቀዳጅ እንደነበር የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ አስታወቁ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ይህን የተናገሩት የፌዴራል የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ለ3 ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ ሲያጠናቅቅ ባቀረቡት የመዝጊያ ንግግራቸው ነው።
ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በግልጽ በተጠቀሱ ሶስት አንቀጾች ላይ የውሳኔ ሐሳብ እንዲሰጥባቸው ለሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መመራታቸውን ተከትሎ አጣሪ ጉባኤው ለውሳኔ እንዲረዳው ይህን መድረክ ማዘጋጀቱ ፕሬዝዳንቷ አስታውሰዋል።
አጣሪ ጉባኤው ይህ ጥያቄ ሲደርሰው የጥያቄውን ግዝፈት እና የእድምታውን ትልቅነት እና የወቅቱን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህገ መንግስቱ በሚያስቀምጥለት ማእቀፍ ውስጥ ጉባኤውን የነበረውን አሰራር በማስፋት ባለሙያዎች ሀሳብ የሚሰጡበትን ሁኔታ በመፍጠር ሶስት ቀናት የፈጀ የውይይት መድረክ አከናውኗል።
ጉባኤው፣ ጉዳዩን ለማየት የተከተለበት ሂደት አንደኛው ባለሙያዎች እና የተቋማት ሙያዊ አስተያየት መስማት ሲሆን በተነሳው ጉዳይ ላይ ዋንኛ ባለድርሻ የሆኑት የጤና ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማዳመጥ ሂደት አከናውኗል።
ባለሙያዎች እና ተቋማትን ከመስማት ጎን ለጎን በቅርብም ይሁን በሩቅ ያሉ ባለሙያዎች በተለይም በሕገ መንግስት ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉ፣ በዳኝነት ወይም በጥብቅና የሰሩ ባለሙያዎች በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ በጽሁፍ የህግ ትንታኔ እንዲያደርጉ ተደርጓል።በቡድን የተዘጋጁት ጽሁፍ ጨምሮ 22 የጽሁፍ አስተያየቶች ቀርበዋል።
አብዛኛው አስተያየቶች ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜዎች የሚወስዱ ናቸው፤ በጣት የሚቆጠሩት አስተያየቶች ደግሞ ወደ ተለየ ድምዳሜ የሚያሳዩ ሆነው ቀርበዋል ሲሉ የአጣሪ ጉባኤው ሰብሰቢ ተናግረዋል።
በአብዛኛው የቀረቡ የጽሁፍ አስተያየቶች በህገ መንግስቱ ማአቀፍ ትንተና ውስጥ ሆነው ነገር ግን ጥቂት አስተያየቶች ጉባኤው ስልጣን የለውም፤የህገ መንግስት ትርጉም የሚያሰጡ ጥያቄዎች አልቀረቡም የሚል መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።እነዚህ ጥያቄዎችን እና የቀረቡ ትንተናዎችን ተከትሎ አጣሪ ጉባኤው መልስ ወደፊት የሚሰጥበት ይሆናልም ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።
Source -EBC


መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV