የፌዴራል ፖሊስ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በማይተገብሩ ዜጎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ

(ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል መንግስት ያወጣቸውን መመሪያዎች በአግባቡ በማይተገብሩ ዜጎች ላይ የፌደራል ፖሊስ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ከዛሬ ጀምሮ መውሰድ እንደሚጀምር ገለጸ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግስት ዜጎች መጨባበጥን እንዲያቆሙ፣ ርቀትን እንዲያስጠብቁና ስብሰባ እንዲያቆሙ መመሪያ ቢያወጣም በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም የፌደራል ፖሊስ በቅድሚያ የመምከርና የማሳወቅ ይህም አልፎ ካልተተገበረ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ የምሽት መዝናኛ ቤቶች በወጣው መመሪያ መሰረት ስራ እንዲያቆሙ እያደረገ ቢሆንም አሁንም በመደበኛ ስራ ላይ የሚገኙ በመኖራቸው የበለጠ ተደራሽ በመሆን የመዝጋት እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እተወሰደ ባለው እርምጃ ክልሎችን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ 5 ሺህ በሚደርሱ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ፣ ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ እና የንግድ ፈቃዳቸውን የመሰረዝ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።
ቫይረሱን በተመለከተም ህብረተሰቡን የሚያደናብሩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በሚነዙ ግለሰቦች ላይ ኮሚሽኑ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ሃሰተኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ ብሎገሮች ላይም እርምጃ ለመውሰድ መረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ የፌደራል ፖሊስ ራሱን ከቫይረሱ ጠብቆ የህብረተሰቡን ጤንነት ለማረጋገጥ በቂ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።