" /> የነቀምት ከተማ የደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ተገደሉ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የነቀምት ከተማ የደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ተገደሉ

BBC Amharic : የነቀምቴ ከተማ የቀድሞ የአስተዳደር እና የደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ዛሬ ከሰዓት መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።የነቀምቴ ከተማአቶ ተሾመ ገነቲ መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በጥይት ተመተው መገደላቸውን ጉዳዩን ከሚያውቁ ሰዎች ማወቅ ተችሏል።

ነገር ግን የነቀምቴ ከተማ የአስተዳድር እና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊን ማን እንደገደላቸው እስካሁን አልታወቀም።

የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ግን አቶ ተሾመ “በጥይት መመታታቸው ሰምቻለሁ ከዚህ በተጨማሪ ሌላ መረጃ የለኝም” ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ከከተማው እና ከክልሉ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አቶ ተሾመ በ2007 እና በ2008 የነቀምቴ ጨለለቂ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ሆነው አገልገለዋል። ከዛ በኋላም የከተማዋ የማህበራዊ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ካገለገሉ በኋላ የነቀምቴ ከተማ የአስተዳደር እና የደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆኑ ተሹመው ነበር።

ከአንድ ወር በፊት ግን ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው ሌላ የሥራ ምደባ እየተጠባበቁ እንደነበረ መረዳት ችለናል።

እድሜያቸው ከ35-40 ይገመት ነበረው አቶ ተሹመ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ በምዕራብ ኦሮሚያ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች ሲፈጸሙ መቆየታቸው ይታወሳል።

 


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV