" /> ኤርትራ በረራዎችን በሙሉ አገደች | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ኤርትራ በረራዎችን በሙሉ አገደች

ኤርትራ 3 ተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ማግኘቷን ተከትሎ ከዛሬ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ የመንገደኛ በረራዎችን ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች።ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 12፣2012 በኤይር አረቢ ተሳፍረው ከዱባይ አሥመራ የገቡ 3 መንገደኞች ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ በዛሬው ዕለት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አረጋገጡ፡፡ ሦስቱ መንገደኞች በኤርትራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎችን ቁጥር ወደ 4 እንዳሳደገው ተነግሯል፡፡
የሀገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ሦስቱም ሰዎች የሀገሪቱ ነዋሪ ኤርትራውያን መሆናቸውን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ጽፈዋል፡፡ሦስቱ የኮሮና ቫይረስ ህሙማን በተሳፈሩበት አውሮፕላን ወደ አሥመራ የመጡት መንገደኞች በሙሉ እና በተለይ ከታማሚዎቹ ጋር አካላዊ ንክኪ የነበራቸው መንገደኞች በሙሉ በለይቶ ማቆያ መቀመጣቸውን የኤርትራ ጤና ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡
ሦስቱም ህሙማን አሥመራ በሚገኘው ቪላጂዮ ሆስፒታል አስፈላጊው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን እና ጤንነታቸውም በአመርቂ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ኤርትሪያን ፕሬስ ጠቅሷል፡፡ይህን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ከዛሬ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ወደ አሥመራ የሚገቡም ሆነ ከአሥመራ የሚነሱ የመንገደኞች በረራዎችን ማገዱን የጠቀሰው የዜና ምንጩ፣ እገዳው ተጨማሪ ማስታወቂያ እስኪነገር ለ2 ሳምንታት እንደሚዘልቅም ጽፏል፡፡
ኤርትሪያን ፕሬስ

 


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV