ሰው በማገት ወንጀል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተከሰሱ ተቀጡ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሰው በማገት ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

(ኢዜአ)  – በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ሰው በማገት ወንጀል እጅ ከፈንጅ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች በአመስት ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የወረዳው ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የጭልጋ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አራጋው መንግስቱ እንደገለፁት የወረዳው ፈርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ሶዎችን አግተው 300 ሺህ ብር ማስለቀቂያ በጠየቁት ድንቁ አበበና አለሙ ተሾመ ላይ እያንዳንዳቸው በአመስት ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

ግለሰቦቹ በፅኑ እስራት የተቀጡት የካቲት 2ቀን 2012 ከንጋቱ 11ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ከአዘዞ ወደ መተማ እንጨት ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረውን ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ በወረዳው አይከል ከተማ ቀበሌ 02 ሲደርስ በጥይት መምትተዉ በማስቆም ሾፌሩንና ረዳቱን በማገታቸው ነው።

ሾፌሩንና ረዳቱን ኩሻይና በተባለ ስፍራ አግተው እያንዳንዳቸው 300 ሺህ ብር ካልከፈሉ እንደማይለቀቁ በማስጨነቅ ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም የክስ መዝገባቸው ያብራራል ።

ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈፀማቸውን በችሎቱ በማመናቸው ተጨማሪ ምስክር ማድመጥ ሳያስፈልግ በዓቃቢ ህግ ክስ መሰረት ውሳኔ እንደተሰጠም ዳኛው ተናግረዋል ።

ከዚህ በፊት በስማቸው የወንጀል ሪከርድ አለመኖሩ ፣ በአለማወቅና በአለመማር የፈፀሙት መሆኑን በወንጀል ማቅለያነት መያዙንም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በመሳሪያ ታጥቀው በቡድን ወንጀል መፈፀማቸው ደግሞ የቅጣት ማክበጃ ተደርጎ መያዙን ሰብሳቢ ዳኛው አስታውቀዋል።

ሁለቱም ግለሰቦች በፈፀሙት የእገታ ወንጀል ጥፋተኞች ሆነው በመገኘታቸው የወረዳው ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ5 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል ።