“ቴዎድሮስ የሠሯት እና ያሰቧት ኢትዮጵያ ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት ነበረች፡፡” ምሁራን


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“ቴዎድሮስ የሠሯት እና ያሰቧት ኢትዮጵያ ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት ነበረች፡፡” ምሁራን

ዛሬ የአንድነት አባት፣ የጽናትና የጀግንነት ምሳሌው ንጉሠ ነገስት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘውድ የጫኑበት ቀን ነው፡፡

(አብመድ)  – ወቅቱ አሸናፊ በሌለው የመሳፍንቱ የእርስ በርስ ሽኩቻ ሀገር የምትተራመስበት ነበር፡፡ በንግስ እሽቅድድም ውስጥ የሚራኮቱት መሳፍንትና መኳንንት የእራሳቸውን ድንኳን እየተከሉ በደጉ ገበሬ ላይ የግፍ ፅዋን ሁሉ ይፈጽሙ ነበር፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ የመከፋፋል አደጋ ተጋርጦባት ነበር፡፡ ይህን ያዩ የውጭ ሀገር ወራሪዎች ደግሞ ቀደምቷን ምድር ለመውረር ጉዞ ጀምረዋል፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የጠላት ጦር ለመግባት አሰፍስፏል፡፡ በወቅቱ በየቦታው የሚገኙት መሳፍንትና መኳንንት የእራሳቸውን ግዛት ከማስፋት ባለፈ ስለውጭ ጠላት ግድ የሰጣቸው አይመስሉም፡፡

Image may contain: 1 personሃገር በመፍረስ ቋፍ ላይ ሳለች አንድ ልጅ በቋራ ሻርጌ ተወለደ፡፡ አባቱ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ እናቱ ደግሞ አትጠገብ ወንድወሰን ይባላሉ፡፡ ወላጆቹ ካሳ ሲሉ ስም አወጡለት፡፡ ‹‹ስምንም መልዓክ ያወጣዋል›› እንዲሉ የዘመኑ መካሻ የመልካም ስርዓት መነሻ ሆነ፡፡ የዚያ ዘመን ፍጻሜ የኢትዮጵያ የአዲስ ምራዕፍ ጀማሪ ያ ህጻን እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ፊደል ቆጠረ፣ ዳዊት ደገመ፣ በመጻሕፍትም ላይ ተመራመረ፡፡ በዚህ ጊዜም ግዕዝ፣ አማርኛና የአረብኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መናገርን ተካነ፡፡ ከሀይማኖታዊ ትምህርቶች በተጨማሪ የአስተዳደር ስርዓትንም ይማር እንደነበር ታሪክ ያወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር የሚወርደውን ግፍ ሲያይ አደገ፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ስጋት ላይ መውደቅም አስተዋለ፡፡ ታላቅ ርዕይም ሰነቆ ሃገርን አንድ አድርጎ ለማቆም በልቡ ቆረጠ፡፡ ልጅ ካሳ ፈረስ ግልቢያ አዋቂ፣ የጦር ፊት አውራሪ፣ የጠላትን ምሽግ ሰባሪ እንደነበረም ይነገርለታል፡፡ የጦር ጀብደኛ እንደነበር ቢወሳም ካሳ ጦርነትንም አጥብቆ ይጠላ እንደነበር ይነገራል፡፡ አባቱ በልጅነት ስለሞቱ የልጅነት እድሜውን ከአጎቱ ከደጃች ክንፉ ጋር ነበር ያሳለፈው፡፡ በዚህ ጊዜም በጠላት ወገን ሁሉ ያስወደሱትን የጦር ሜዳ ገድሎች ፈጽሟል፡፡ ከደጃች ክንፉ ጋር ተጋጭቶ ወደ ጎጃም በመሻገር ከደጃዝማች ጎሹ ጋር አስደናቂ ገድሎችንም ፈጽሟል፡፡

ከዚህ ቆይታ በኋላ ነው ታሪከኛው ልጅ ህልሙን መኖር የጀመረው፡፡ ቋራ ሄዶ የእራሱን ጦር ማደራጀት ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜም ቋራን ተቆጣጠረ፡፡ ልጅ ካሳ ቋራን ሲቆጣጠርም አጼ ዮሀንስ ሦስተኛን፣ ባለቤታቸውን እቴጌ መነንና ልጃቸው ራስ አሊን ስጋት ውስጥ ከተተ፡፡ ተይዞ ወደ ቤተመንግስት እንዲመጣም በወንዲራድ የሚመራ ጦር ተላከበት፤ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ በጋብቻ ሊታረቁት ስለፈለጉ እንደርሱ ሁሉ ብልህ የነበረችውን መልካም ሴት ተዋበችን ዳሩለት፡፡ በጋብቻ አስረው ያቀዘቀዙት ይምሰላቸው እንጂ እነርሱስ ሳያስቡት የህልሙን በር ቁልፍ መክፈቻ ነበር የዳሩለት፡፡

የበለጠ እንዲጀግን በዓላማው እንዲጸና ጥንካሬ ትሆነው ጀመር፡፡ የደጅ አዝማች ማዕረግም ተሰጠው፡፡ በወጣትነት እድሜው በነበረው ታላቅ የአመራር ጥበብና የውጊያ ስልት የዘመነ መሳፍንት ፍጻሜ የአዲስ ስርዓት ጅማሬ ሆነ፡፡ ጠንካራ ገዢ አጥታ የነበረችውን ኢትዮጵያንም አንድ ንጉሥ ብቻ እንዲኖራት አደረገ፡፡ ደጃች ካሳ በወርሃ የካቲት በ1847 ዓ.ም በተወለደ በ36 ዓመቱ በአቡነ ሰላማ እጅ ቅብዓ ንግሥናን ተቀብቶ በደረስጌ ማሪያም ዘውድ ጫነ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ተባለ፡፡

ንግስና ስለጫኑበት ቀን ምሁራን የተለያየ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አጼ ቴዎድሮስ ዘውድ የጫኑት የካቲት 5 /1847 ዓ.ም በእለተ እሁድ ነው ይላሉ፡፡ እንደ ታሪክ ምሁሩ ገለጻ የካቲት 3/1847 ዓ.ም አርብ ምሽት ከደጃች ውቤ ጋር ተዋጉ፤ ቴወድሮስም አሸነፉ፡፡ የተዋጉበት ስፍራም ድል ተራራ አካባቢ ነበር፡፡ ደጃች ውቤ ሁለት የደረሱ ልጆች ነበሯቸው፤ ደጃች እሸቱና ደጃች ጓንጉል፡፡ ደጃች እሸቱ ከአባቱ ጋር ቴዎድሮስን ገጥሞ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ቅዳሜ የካቲት አራት ደግሞ ከደጃች ጓንጉል ጋር ገጠሙ፤ እርሱንም አሸነፉ፡፡ የካቲት 5/1847 ዓ.ም ደጃች ካሳ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብለው በደረስጌ ማርያም ነገሱ፡፡ ስለቀኑ አለቃ ዘነበንና አለቃ ወልደ ማርያም የጻፉት ይሄን ታሪክ ነውም ብለው አስረድተዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ታያቸው ደግሞ ቴዎድሮስ የነገሱበት ቀን በውል ለማወቅ አሻሚነት አለው ብለዋል፡፡ የውጭ ሀገር ፀሃፊዎችን መሠረት ስናደርግ ቴዎድሮስ የነገሱበት ቀን የካቲት ሁለት ወይም ሦስት ሊሆን ይችላል በማለት ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ቴዎድሮስ እንደነገሱ እሳት ለኩሶ ኢትዮጵያን ሊያቀጣጥል ሲያሰፈስፍ የነበረው ሁሉ ህልሙ ቅዠት ሆነበት፡፡ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን አንድ ከማድረግ አልፎ እስራኤልንም ከግብጽ ባርነት ለማውጣት አስቀድሞ አቅድ ነድፈው የነበረ ሩቅ አሳቢ ባለርዕይ ነበሩ ይባላል፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ወደ ንግሥና የመጡበት ዓላማ በዘመኑ እንደነበሩት ደስታና ተድላ ለማትረፍ ሳይሆን በመሳፍንቱ የስልጣን ሽሚያ የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያ አንድነቷን ማጠናከር ነበር፡፡ ጠረፎቿን የያዙት ጠላቶች አባርሮ የቀደመ ታላቅነቷንና ኃያልነቷን መመለስና ማደስ፣ ከውጭ ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠርና በኢትዮጵያ ምድር ዘመናዊ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም አልመው ነበር የተነሱት፡፡ እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ማብራሪያ አጼ ቴዎድሮስ ከ67 ዓመታት በላይ የነበረውን አስቸጋሪ ስርዓት የሻሩና ሀገር የሚባለው እንዲዘመር ያደረጉ ንጉሥ ነበሩ፡፡

መቋጫ የሌለውን የመሳፍንት የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆሙና ስርዓት ያጣውን የወታደር ባሕሪ ያስተካከሉ ሰው ነበሩም ብለዋል፡፡ ቴዎድሮስ እርሳቸውን ተከትለው ለመጡ ነገስታት መልካም ስርዓትን ያስጀመሩ፣ ለሕዝቦችም አንድነት ያለባትን ኢትዮጵያ ያመጡ፣ ለተከታዮቹ መሪዎች መልካም ስርዓትን የፈጠሩ ንጉስ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አንድነት ያለባትን ኢትዮጵያ ለማስረከብም ቀን ከሌት ከጠላት ጋር እየተዋጉ መላ ዘመናቸውን ለሀገራቸው ሰጥተዋል፡፡

“ቴዎድሮስ የፈጠሯት እና ያሰቧት ኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባት ናት” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ቴዎድሮስን አርዓያ የሚያደርግ ሁሉ አንድነትን መማር እንዳለበት መክረዋል፡፡ በተለይም በዚህ ዘመን ነገሥታትን ለአንድ ወገን ብቻ ሰጥቶ በተሳሳተ ትርክት መንጎድ አግባብ እንደሌለውም አስገንዝበዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማም አጼ ቴዎድሮስ ከንግሥና ዘመናቸው በፊትም መልካም የሚያስቡ፣ ለሕዝብ ጥቅም እራሳቸውን የሚሰጡ እንደነበሩም አንስተዋል፡፡

ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ለውጦችን በማምጣት አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመሠረቱ ናቸውም ብለዋል፡፡ “በዚህ ዘመን ያለው ወጣት ለአሉቧልታ የተጋለጠ ነው” ያሉት ምሁሩ ደጋፊ ለማፍራት ጥረት የሚያደርጉ ፖለቲከኞች የተዛባ ትርክት ከመናገር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ቀደምት የተንሰራፋውን የባሪያ ንግድ ስርዓት የሻሩ፣ ባሪያ መሸጥም ሆነ መለወጥ እንዲሁም ማጓጓዝን የሚያግዱ ብዙ ድንጋጌዎችን በማወጅ ቀደምት የባርነት ስርዓት ተቃዋሚ እንደነበሩም ነው ምሁራኑ ያወሱት፡፡

በአዲሱ ስርዓት መሠረት የግብር እና የፍርድ ባለስልጣናት ከማዕከላዊ መንግስት ደመወዛቸውን እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በየቦታው የነበሩ ባላባቶችን የመዋቅር፣ የስነ ምግባርና የትጥቅ ለውጥ እንዲያደርጉም ሠርተዋል፡፡

ዛሬ የአንድነት አባት፣ የጽናትና የጀግንነት ምሳሌው ንጉሠ ነገስት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘውድ የጫኑበት ቀን ነው፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ዛሬም ድረስ መልካም መንገድ የጠረጉ፣ ዘውዳቸውን ያላወለቁ፣ ከክብራቸው ያልጎደሉ ንጉሥ ተደርገው በዚህ ትውልድ ሳይቀር ይወሳሉ፡፡