በፓርቲዎች መካከል አድሏዊ አሰራር ይታያል ተባለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አዲስ ዘመን  – አሁን ባለው የአባላት ምዝገባ ቅስቀሳና አሰራር ላይ በፓርቲ መካከል ልዩነት ያለው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያነጋገርናቸው ፓርቲዎች ሲገልጹ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ከህግና መመሪያ ውጪ የተፈጸመ ነገር እንደሌለ አስታውቋል።

ከህውሓት ፓርቲ እንደመጡ የገለጹት አቶ ዳኛው በለጠ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሚናገሩት፤ ብልጽግና ፓርቲን ህጋዊ ያደረጉበት መንገድ ለአንዱ ያደላ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው።ምክንያቱም ውሳኔው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይደረግ፣ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ሳይመርጥ፣ ኢህአዴግን ቢያንስ በአስቸኳይ ጉባኤ ሳያፈርስ የተደረገ ነው።ይህ ደግሞ ድጋፉም ሆነ እውቅና መስጠቱ አድሎ እንዳለበት ያሳያል።

የፓርቲዎች ምዝገባና እውቅና አሰጣጥም ላይ ቢሆን ብዙ ልዩነቶች እንዳሉ የሚያነሱት አቶ ዳኛው፤ ከሦስት ቀን በፊት ነው ለምዝገባ ያዘጋጀነውን ሁሉ ማስገባት የቻልነው ይላሉ።ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ይህንን ልዩነት በአስቸኳይ እያጠፋ መሄድ ካልቻለ የምርጫው ፍትሀዊነት ያሰጋል ብለዋል።በድጋፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ምንም አይነት ነገር እየተደረገ ባለመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

‹‹ከ200 በላይ ጽህፈት ቤቶች ቢኖረንም ከመንግስት ዋና ጽህፈት ቤት እንኳን አላገኘንም›› የሚሉት የአብን ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ ብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዋና ጽህፈት ቤታቸውን መንግስት በሰጣቸው ቦታ ላይ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።‹‹የእኛ ፓርቲ ግን ይህ አልሆነለትም፡፡›› በመሆኑም በመንግስት ደረጃ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ልዩነት ያለው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባሉ ዶክተር ጌታሁን ካሳ በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ በህግና በመመሪያ መሰረት ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ተቋም ነው።ህጉ እስካለ ድረስ በህግ መገዛት ግዴታ ነውና ህጉ በሚያዘው መሰረት አንዱን ከአንዱ ሳይለይ መደረግ ያለበት ነገር ሁሉ ይደረጋል።ይህንን ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ከመጡ ማስተናገድ አይቻልም።በዚህም የማያስማሙ ነገሮች ይፈጠራሉ ብለዋል።

‹‹የሀሳብ ልዩነት ማለት አብሮ አለመስራት ማለት አይደለም›› የሚሉት ዶክተር ጌታሁን፤ ሆኖም የተጠየቀው ሁሉ በአንድ ጊዜ መልስ ሊሰጥበት አይችልምና እየተመካከሩ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።ለዚህም ምርጫ ቦርድ ተራርሞ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።