አስመላሽ የጨው ፋብሪካ ባለቤት ነው የሚል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰጠ አደናጋሪ መግለጫ እንደሆነ ይገባኛል። – አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“ሕወሃት እንደራሴ እየመደበ ያሠራቸው ነበር ከተባለ የተካደው ሕወሃት ሳይሆን ታሪክ ነው” – አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የህወሃት ስራ አስፈፃሚ አባል

የጨው ፋብሪካ ባለቤት ነው አስመላሽ የሚል ከሆነ ይህ መንግሥት የሰጠው መረጃ ነው የሚሆነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰጠ አደናጋሪ መግለጫ እንደሆነ ይገባኛል። ይህ የሚደረገው አፍ ለመዝጋት ነው! በዚህ የሚዘጋ አፍ የለም! በጥይትም አንዘጋም በዚህ ይቅርና! አልገባቸውም እነዚህ ሰዎች! ይሄ ፍጹም ውሸት ነው። ይሄ የምትለው ነገር ውሸት ነው። ይምጡ እኮ ነው እያልኩህ ያለሁት። ይህ እኮ ግልጽ ነው። ማን ማናቸው በዝርዝር ይምጣ። የዘረፈ የኦሮሞ ባለሥልጣን የለም? የዘረፈ የአማራ ባለሥልጣን የለም? የዘረፈ ባለሥልጣን በተለያየ ክልል የለም? እስቲ አስቡት! ምን እየተሠራ እንደነበር ሕዝቡ ያውቃል።

አሁን እየሆነ ያለው እንዴት አድርገን ይሄንን ኃይል እንምታው? እንዴት እናጥላላው? በሐሳብ ግን ፊት ለፊት መጥተው አይሞግቱም። የትኛው ነው ትክክል? የትኛው ነው ትክክል ያልሆነው? አሁን ለምሳሌ አፋር ያለ ጨው በሞኖፖሊ በማን እንደተያዘ ለምን አታጣሩትም? ማጣራት እኮ ይቻላል። ሕጋዊ ከሆነ ችግር የለውም። ግን ምን እየተሠራ እንደሆነ ማለቴ ነው። ሲፈልጉ እኮ እያንዳንዳችን ቢሊየነር ያደርጉናል። ስታየው ግን የለም።

የአዲስ አበባን ሕንጻዎች የእነሱ ነው ይላሉ። ቀላል እኮ ነው። እዚህ መዘጋጃ ቤት ይታወቃል፤ ካርታው አለ፤ ማጣራት ይቻላል። የት የት ያሉ ናቸው? ለአንድ ሰው ዐሥር ትላልቅ ሕንጻ ፈልገው ይሰጡታል። በጣም የሚገርም ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ከሙስና ፣ ከህገወጥነት አኳያ ታህሳስና መጋቢት 2010 የገመገምነው እንደዚያ አይልም።

በእርግጥ የተገመገሙ ነገሮች አሉ በግልጽ ወጥተው። እነዚህ ሁሉ ወጥተው ተጣርቶ እርምጃ የሚወሰዱበትን መውሰድ ነው። ካልሆነ ግን ሜቴክ 38 ቢሊዮን ጠፍቷል ብሎ ነው የተናገረው መግሥት የሚያፍር መንግሥት እኮ አይደለም፤ እየዋሸ አያፍርም። ይህንን ነው እያየን ያለነው። ከደቂቃ በኋላ ይዋሻል፤ አሁንም ከደቂቃ በኋላ ይዋሻል።… የውሸት ሰንሰለት ነው የተፈጠረው እዚህ ሀገር። ሂትለር ያደርገው የነበረውን የፕሮፓጋንዳ ዘይቤ ነው እየተደረገ ያለው። በጣም አደገኛ የሆነ ነገር ነው።

የተወለዱት በትግራይ ክልል በቀድሞው አድዋ አውራጃ እንዳአባ ጽህማ ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ትጥቅ ትግሉ ቢገቡም ከድል በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት ቀጥለው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በሕግ ክፍለ ትምህርት ተመርቀዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የህወሃት ስራ አስፈፃሚ አባል ናቸው። አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ (ዓባይ ነፍሶ) ይባላሉ። ከእሳቸው ጋር ወቅታዊ የአገራችንን ጉዳይ በተመለከተ ዘመን መፅሄት ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዳ ቆይታ አድርጋለች። የውይይቱ የመጀመሪያው ክፍል የሚከተለውን ይመስላል። (ሙሉ ቃለ ምልልሱን በአንድ መፅሄት ማስተናገድ ስላልቻልን የውይይቱን ቀጣይ ክፍል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዘን እንቀርባለን። እንዲሁም ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በድርጅታችን ማለትም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድረ ገፅ (www.press.et) ላይ ማግኘት እንደምትችሉ በትህትና እናሳውቃለን።)

ዘመን፡- ኢሕአዴግ ገነባሁት የሚለው ፌዴራሊዝም ምን አስገኘልን?

አቶ አስመላሽ፡- የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ዘርፈ ብዙ ጥቅም አስገኝቷል። በመጀመሪያ ደረጃ በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የኅብረተሰብ እንቅስቃሴ ሲነሳ የነበረውን ከብሔር ጭቆና የመላቀቅና የብሔር ጥያቄን ከመመለስ አንጻር ትርጉም ያለው ሁሉም ብሄር ብሔረሰቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ በዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲሰባሰቡ ያደረገ ውጤት አለው። ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ የብሔር ጥያቄን መልሷል። ሁሉም ብሔሮች እኩል እንደሆኑ፣ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ከዚያ ባለፈም በሀገራዊ ጉዳዮች ሚዛናዊ ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው አድርጓል። እንደ ሕውሃትና እንደ ቀድሞ ኢሕአዴጎች ግምገማ ይሄ ተግባራዊ ሆኗል። እያንዳንዱ ብሔረሰብ ከዚህ ፌዴራላዊ ሥርዓት በፊት ማንነቱ አይታወቅም። ባህሉን የሚያሳድግበት ሁኔታ አልነበረም። ታሪኩም እንደዚያው። እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ብዙ ነበሩና ይህንን የፈታ ነው። እያንዳንዱ ክልል ወይም ብሔር ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የቻለበት፣ እየወደቀ እየተነሣም የተለማመደበት እራሱን ለማልማት ብዙ ርቀት የሄደበት የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በሀገር አቀፍ ደረጃም በየክልሎቹም የተገነባበት ነው።

ከልማት አኳያም ብዙ ነገሮችን ማንሣት መዘርዘር እንችላላን። ከሰላም አኳያም ባለፈው 27 ዓመታት ተነጻጻሪ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ነበረች። ከ1983 ዓ.ም ሀገሪቱ ልትበተን ትንሽ ነበር የቀራት። እስከ 17 የሚደርሱ የታጠቁ የብሔረሰብ ድርጅቶች ነበሩ። ይህ ጥያቄ ሲመለስ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሲመጣ ሁሉም የሄደው ወደ ልማት ነው። ስለዚህ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከልማት፣ ከዴሞክራሲ፣ ከሕግ የበላይነት፣ ከሰላም አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሠርተውበታል። ነገር ግን ጊዜው አጭር ከመሆኑ የተነሣ ውስንነቶች ነበሩ። ችግሮቹ ከሕገ መንግሥቱና ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ አወቃቀር የመነጩ ሳይሆን ከአፈጻጸም የመነጩ ችግሮች ነበሩ። የሁሉም ልምድ አንድ አይደለም፤ በብቃትም ይለያያል። የተለያዩ ስልቶችም ማስቀመጥ አልተቻለም፤ ለምሳሌ የበይነ መንግሥታት ክልል ከክልል፣ ክልል ከፌዴራል የሚያገናኝ ሕግ አቶ ካሳ ተክለብርሃን እያሉ የተጀመረ ቢሆንም ይሄ ሕግ ስለዘገየ በዚህ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም አልተገኘም። ስለዚህ ውስንነቶች ቢኖሩም በመሠረታዊ መመዘኛው ሲታይ ግን የዚህ ሀገር ሕዝቦች ጥያቄ የፈታ፣ የተዋጣለት ፌዴራላዊ ሥርዓት ነበር ብለን እንወስዳለን።

ዘመን፡-ሕወሃት በውክልና ያስተዳድረን ነበር የሚሉ የክልል አመራሮች ግን አሁን በነጻነት እየተናገሩ ነው፤ ይሄንን ቅሬታስ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ግንባታው አንጻር ችግሮች እንደነበሩ አያሳይም?

አቶ አስመላሽ፡- እንደዚህ ሲባል እሰማለሁ፤ ግን ይሄንን ጉዳይ ሕወሃትና ለትግሉ መስዋዕትነት የከፈሉ የብሔር ብሔረሰብ ታጋዮችን ብቻ መካድ ሳይሆን በጥቅሉ ታሪክን መካድ ነው የምለው፤ ታሪክ ነው የተካደው፤ሕወሃት አይደለም የተካደው። የትግራይ ሕዝብ አይደለም የተካደው፤ የተካደው ታሪክ ነው። በዐፄዎቹና በደርግ ጊዜ የነበረውን ሥርዓት የሚያሞካሽ ከዚያ በኋላ የመጣውን መሠረታዊ ለውጥ የሚያንኳስሱ ሰዎች የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው። ተጨባጩን እውነታ ስናየው ግን በሕወሃት እንደራሴ እየተመደበ የሚያስተዳድር ክልል የትኛው ክልል ነበር?

ዘመን፡- አሁን በእስር ቤት ያሉት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አመራር የሚላከው ከማእከላዊ መንግሥት ነው፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሚመሩት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ይላክ ነበር ብለዋል። አቶ አብዲ ኢሌ የሰጡት መግለጫ ይፋዊ ነበር። የእሳቸውን ማንሳት አንችልም?

አቶ አስመላሽ፡- ይሄ በጣም ነጭ ውሸት ነው፤ ለምን መሰለህ፤ እንደውም ታጋይ ጌታቸው አሰፋ የደኅንነት ኃላፊ እያሉ በሶማሌ ክልል የነበረው ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አያያዝ የሚቃወሙ ሰው ነበሩ። ይሄንን የኢሕአዴግ ምክር ቤት እና ሥራ አስፈጻሚ ያውቀዋል፤ በወቅቱ በ2008 እና በ2009 ‹በሶማሌ ክልል ያለው አንዳንድ ሰብአዊ አያያዝ ትክክል አይደለም፤ የሚጠየቅ ሰው መጠየቅ አለበት› ብለው አቶ ጌታቸው አሰፋ ሲከራከሩ የተቃወመው ቁጥር አንድ ማነው? ደመቀ መኮንን ነበር። የተቃወመው ሰው ማነው? ኃይለማርያም ደሳለኝ ነው።

ዘመን፡- ምን ብለው ነው የተቃወሙት?

አቶ አስመላሽ፡- አልተቀበሉትም ፤ ‹የምትለው ነገር ትክክል አይደለም ነው› ያሉት። አሁን ሁሉም ነገር ተቀያሮ እንደውም በከፋ መልኩ አቶ ጌታቸው ይመድብልን ነበር ይላሉ፤ አቶ ሙስጠፌም ታሪኩን አያውቁትም ወይም ማደናገር ስለፈለጉ ሊሆን ይችላል።

ዘመን፡- አቶ አስመላሽ ይሄ ቅሬታ እኮ ቤኒሻንጉል ክልልና ጋምቤላም ይሰማል?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ሰምቼአለሁ፤ ልምጣልህ! በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ክልሎች በሕዝብ የተመረጠ የራሳቸው ሕግ አውጪ አካል ነበራቸው? አልነበራቸውም? ነው ጥያቄው፤ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ ክልል፣ ሁሉም ክልሎች የራሳቸው የምርጫ ክልል አላቸው። የሚወዳደረውም የሚመርጠውም የዚያው ክልል ተወላጅ ነው። እንደውም በነበረው የምርጫ ሕግ ስንወስድ የዚያን ክልል እና አካባቢ ቋንቋ የማያውቅ ሰው በሁሉም ደረጃ ባለ ምክር ቤት አይወዳደርም። የእነሱ የራሳቸው ነው። ሕግ የሚያወጣው፣ በጀት የሚያጸድቀው፣ የሚሾመው የበላይ የክልሉ አካል የሆነው ይሄ (ምክር ቤት) ነው። ሁለተኛ ሕግ አስፈጻሚውን ብትወስድም እንደዚያው ነው፤ ከርእሰ መስተዳድሩ ጀምሮ ስብጥሩ የካቤኔው ከዚያው ነው። የዳኝነት አካሉም ከዚያው ነው። እነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት ሕወሃት እንደ መንግሥት እንደራሴ እየመደበ ያሠራቸው ነበር የሚል ነገር ካለ የተካደው ሕወሃት ሳይሆን ታሪክ ነው። የነበረው አመጣጥ ግን እንደዚያ ነው። ሕዝቡ ለምን አይጠየቅም? አንድ ጊዜ አቶ አባተ ኪሾ ‹ወያኔ ያሰፋልንን ጥብቆ ስንለብስ ነበር› ብለው ሲናገሩ ሰማኋቸው። የሚገርም አገላለጽ ነው። አቶ አባተ ኪሾ 1993 ዓ.ም ምንድነው ያሉት? ኢሕአዴግ ክልሎች ችግር ውስጥ ናቸው፤ ጸረ ዴሞክራሲ፣ ሙስና፤ የትምክህትና የጠባብነት ችግር አለ፤ በአጠቃላይ ኪራይ ሰብሳቢነት አለ። ከዚህ አደጋ ኢሕአዴግ መውጣት አለበት ተብሎ ወደ ተሐድሶ ሲገባ አቶ አባተ ኪሾ ‹እነዚህ ችግሮች የሉም፤ በጥሩ ሁኔታ ነው ሀገሩ እየተዳደረ ያለው፤ ክሊንተን ከሚመራው አሜሪካ ይልቅ ዴሞክራሲ እና ሀገር አለን› ብለው ተናግረዋል። ይሄን የሚጠይቃቸው ሰው ግን አሁን የለም። እንደዚያ ብለው ተናግረው ሲያበቁ ሌላውን ተዉትና ምን እንደሚለብሱ ራሱ እየተከታተለ ሕወሃት የሚያለብሳቸው ከነበረ ታሪክ መካድ ነው።

ዘመን፡- እሺ! አጋር የተባሉ ድርጅቶች የሚያሰሙትን ድምጽ ይተዉትና የራሳችሁ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም እኮ በድርጅትና በመንግሥት ሚናቸው ውስጥ በነጻነት ይሠሩ እንዳልነበረና ʻየህወሃት የእጅ አዙር ቁጥጥር ነበርʼ እያሉ ነው፤ ስለእነሱስ ምን ሊሉ ነው?

አቶ አስመላሽ፡- አሁን እኮ! ሁሉም አሽከር ነበርኩ እያለ ነው፤ አሽከር መሆኑን እየሰማን ያለነው አሁን ሲናገር ነው። ግን እነዚህ ዜጎች በኢትዮጵያ ባህል ስለሀገር ነጻነት ላቅ ያለ ሰብእናና ማንነት ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተፈጠሩ ዜጎች ናቸው ወይ? በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ሰዎች ሕወሃት ያለንን ነበር ስንሠራ የቆየነው ሲሉ ምን ዓይነት ሰብእና ሲኖራቸው ነው? ምን ዓይነት ሰዎች ሲሆኑ ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በእኛ እምነት የጋራ ፕሮግራም የጋራ እቅድ የጋራ ሕገ ደንብ ይዘን ለጋራ ዓላማ ስንሠራ ነበር ብለን ነው የምናስበው። ተላላኪ ሆነው፣ ያልናቸውን ሁሉ እየፈጸሙ ይሄዳሉ የሚል ነገር አይሠራም። የኢሕአዴግ አደረጃጀት ራሱ አይፈቅድም። ሠላሳ ስድስት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አለ። ከእነዚህ ውስጥ ሕወሃት ያለው እኮ ዘጠኝ ነው። በድምጽ ለምን አይሆንም አይሉም። በምክር ቤትም እንደዚያው ነው። አርባ አምስት፣ አርባ አምስት ሰው ነው ያለው። አብዛኛው የእነሱ ሰው ነው። ስለዚህ ተላላኪ ነበርን እያሉ ያሉት ለስልት ነው፤ አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ተቀይሯል። እንደገና ጥላቻና ቅሬታ፣ ደጋግመህ በመዋሸትና ያንን በማስረጽ አንዱን በማጥላላት የጥሎ ማለፍ፣ የጥገኛ፣ የኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብ ነው። እነዚህ ሰዎች ከዚህ ሊወጡ ከሆነ ከደሙ ንጹህ ነን ማለት አለባቸው። እንጂ ታህሳስ 2010 መጋቢት 2010 የገመገምነው የጋራ ሰነድ እኮ አለ። እሱን ማየት ይቻላል። እሱን ተገደው ነው ያደረጉት…

ዘመን፡- አቶ አስመላሽ ይሄን ነገር በድርጅቶቹ አመራሮች አሳበን ብናልፍ እንኳን በሌላ መልኩ የሚገለጽ ተቃውሞ እኮ አለ፤ በተለያዩ ክልሎች በአደባባይ በተደረጉ የህዝብ ተቃውሞዎችም ‘Down Down TPLF ‘የሚለው ድምጽ እኮ ጎልቶ ይሰማ ነበር። ለምን በድርጅቶችስ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ ይታሰባል?

አቶ አስመላሽ፡- ቅሬታው በተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሰረጸ እናውቃለን። ይሄም ከመሆኑ በፊት እኮ ስማችን ይታወቃል። ʻገንጣይ አስገንጣይʼ ይባል ነበር። 1983 በኋላ ህዝቡን በማወያየት እንደ እዚያ እንዳልሆነ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በ1983 በኋላ ደግሞ የደርግ ወታደር የነበረው፣ ኢሠፓ የነበረው፣ ትምክህትና አሐዳዊነትን የሚወክለው ልሂቅ፣ ከ1983 ጀምሮ በሚጻፉ ጋዜጦች፣ ከውስጥም ከውጪም የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ‹ሕወሃት ሁሉን ነገር ነው የሚያደርገው፣ ራሱ በውክልና እንደሚያስተዳድር፣ ፍትሐዊ ያልሆነ ሀገር እንደገነባ፣ ትግራይ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነች ይናገሩ ነበር። አንድ ሰው እንደውም ከአራት አምስት ዓመት በፊት ምን አለ? ‹ትግራይ ያሉ መንገዶች መስተዋት ናቸው› አለ። መስተዋት መኪና እንዴት እንደሚሸከምም አላውቅም። ይሄንን ያህል ውሸትና ፈጠራ ነው ያለው። ይሄ ሕዝብ (የትግራይ ሕዝብ) እኮ! ከዐፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ‹ከሃዲ› ነው የሚባለው። የትግራይ ሕዝብ ግን ከሃዲ አይደለም። እንደ ሕብረተሰብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዋጋ ከፍዬአለሁ የሚል እንደ ትግራይ ሕዝብ ያለ በኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም። የአድዋ ጦርነት እኮ አንድ ሁነት ነች። ከአድዋ ጦርነት በፊት እኮ የውጪ ወረራን ሲከላከል የነበረ ሕዝብ ነው። በኋላም እንደዚያው ነው። ስለዚህ ብዙ ነገር ተጽፎበታል። ይሄ የትምክህት ልሂቃን የሦስት መንግሥታት ልምድ አለው። የዐፄ ኃይለሥላሴ፣ የደርግ የምኒልክ። ይሄ ልምድ ተሰብስቦ፣ የመማር ዕድል አምጥቷል፤ የቢሮክራሲ ችሎታ አለው፤ የዲፕሎማሲ ችሎታ አለው። እነዚህን ሁሉ ተጠቅሞ በሥራ አጥነት ፣ በዴሞክራሲ በሰላም የተቸገረን ሕዝብ ምንጩ ሕወሃት ነው ብሎ ቢያደናግር ምን ኃጢአት አለው። ግን ሕዝቡ በራሱ አመለካከት የያዘው አቋም አይደለም። የትውስት አመለካከት ነው። ይሄም ሆኖ አንድ ምሳሌ ላቅርብላችሁ፤ 2010 ከመጋቢት በተለይ ከሰኔ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሲናገሩ፣ የባህርዳር ሰልፍ ሲደረግ እነ ደመቀ መኮንን 27 ዓመት ጨለማ ነበር፤ ቆሻሻ ነበር እያሉ ሲናገሩ በየቦታው ሕዝቡ ሰክሮ ነበር። ‹የቀን ጅብ ይመጣል፤ ፀጉረ ልውጥ ይመጣል። የተደራጀ ዘራፊ ይመጣል። ከሃዲ ይመጣል፤ በዘር በጎሳ ከፋፍሎ ሀገርን…› ይባል ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረው የሀገሪቱ ሁኔታ አዲስ አበባን ጨምሮ ለትግራይ ሕዝብ፣ ለሕወሃትም አስቸጋሪ ነበር። አሁን ግን ይሄ እውነታ አለ? ገምግሙት። አይመስለኝም። ለምን ህዝቡ ከተግባርና ከተሞክሮ እየተማረ ይሄዳል። የአርሶ አደር አመለካከት አይደለም፤ የከተማ መካከለኛ ገቢ ያለውም ህዝብ አመለካከት አይደለም። የዝቅተኛው ምሁር አመለካከት አይደለም። ይሄ አመለካከት የትምክህትና የአሕዳዊነት ልሂቃኑ አመለካከት ነው።

ዘመን፡- በኃይል አጠቃቀም ደረጃም ቢሆን ሕወሃት ይዞት የመጣውን የበላይነት ተጠቅሞ ረጅም ጊዜ የስልጣን ቁጥጥር በማድረግ ጫና ፈጥሯል። ለዛም ነው የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ውስጥ እየወደቀ የመጣው። እነ አባተ ኪሾ፣ እነ ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ ሌሎች በየክልሉ ለመብታቸው ይጮሁ የነበሩ አመራሮች ታስረዋል አለፍም ሲል የተገደሉም እንዳሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። ሕወሃት የማይፈልገው ነገር በተፈፀመ ቁጥር ያስፈራራ፣ ያስር፣ ይገድል እንደነበር በርካቶች ምስክርነት እየሰጡ ይገኛሉ። እነዚህ ድርጊቶች ፖለቲካዊ ጫና በማድረግ አልተፈፀሙም? በዚህ ደረጃ ሕወሃት ንፁህ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ አስመላሽ፡- ምን መሰለህ ህወሃት እንደዚህ ያደርጋል ብለህ ስትናገር እነሱ የሚሉህን ነገር ተቀብለህ አምነህ ነው እየተናገርህ ያለኸው። እኔ በዛ እንደማልስማማ ብዙ ጊዜ ገልጫለሁ። ሕወሃት እየተቆጣጠረ፣ እንደራሴ እየመደበ ያስተዳደረው አገር የለም። አሁን ያለው ሁኔታ አይብስም እንዴ? ይሄ መንግስት የሶማሌ ክልል ፕረዚዳንትን ኃይል አስገብቶ አይደል የቀየረው? አፋር በጫና አይደለም እንዴ የፈረሰው? ቤኒሻንጉል በጫና አይደለም እንዴ ፕሬዚደንት የቀየረው? ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ተማሪዎች ሰብስቦ፤ ባለፈው ዓመት እኮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዛ ብለው ገልፀዋል።

ዘመን፡- ጥያቄው ሕወሃት የተጠቀሱትን ወንጀሎች አልፈፀመም?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ! ቆይ! ልንገርህ። አሁን ያለው ነገር ምን እየተሠራ እንደሆነ፣ እዚህ ኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት አጋሮችን ሰብስቦ ምን አይነት መግለጫ እንደሚሰጡ እየተፃፈ እየተሰጣቸው ነው። ከዚህ ሁሉ ለእያንዳንዱ አጋር ክልል ከሦስቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የተመደቡ ሰዎች አሉ። እንዴት እንደሚሄዱ እንትን እየተደረገ።

ዘመን ፡- እስኪ ይሄንን በአጭሩ እንዝጋውና ሕወሃት ከነበረው ግንባር ቀደም ሚና…

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ቆይ ልንገርህ። የታሰሩ ሰዎች ግን አጥፍተዋል በወቅቱ የሚታዩ ተጠርጣሪ ብለህ ነው የምትይዘው። ወንጀለኛ ብለህ እርግጠኛ ሆነህ የምትከሰው ሰው የለም። በተጠርጣሪነት ግን የተከሰሰ ሰው አለ። አባተ ኪሾና የጠቀስካቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም የታሰሩት። ከትግራይ አመራሮች የታሰሩ የሉም እንዴ? ሁሉም ሰው የሚያውቀውን እውነታ እየተካደ ነው ያለው። ሁልጊዜ ህወሃት ይገድላል፣ያስራል፣እንደዚህ ያደርጋል የሚለው ተረት የትም አያደርስም። ጉሙዞችን አትጠይቁም? ሁለት መቶ ምናምን በጅምላ ተገደልን እያሉ አይደለም እንዴ! ቅማንትን ለምን አትጠይቁም? የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመብን ነው እያሉ አይደል እንዴ!

ዘመን፡- የማንነት አሊያም የክልል ጥያቄ ያነሱ

አካላት ላይ የዘር ማጥፋት የሚመስሉ ወንጀሎችን ሕወሃት ፈፅሟል የሚሉ በርካቶች አይደሉም እንዴ?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ! በድሮው ኢህአዴግ ጊዜ እንደዚህ ተደርጎ አያውቅም። እንደዚህ ያለ ታሪክ ካለ አምጣ፤ የለም።

ዘመን፡- በ1996 ዓመተ ምህረት በጋምቤላ ክልል የአኝዋክ ብሄር እንዲጨፈጨፍ ያደረገው ሕወሃት መሆኑን የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚደንት ገልፀዋል እኮ…

አቶ አስመላሽ፡- የጋምቤላው ጉዳይ በወቅቱ ተጣርቷል። በ1996 ዓመተ ምህረት ድርጊቱ ተፈፅሞ ተጣርቶ እርምጃ ተወስዷል።

ዘመን ፡- የትግራይ ተወላጆችም ሆኑ የአማራ ወይም የኦሮሞ አሊያም የሌላ ብሄር ከሕወሃት መስመር የወጣ መዋያው እስርቤት፣ አለፍም ሲል እስከ መገደል ያደርሰው እንደነበርም ይገለፃል..

አቶ አስመላሽ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የሕወሃት መስመር የሚባል ነገር የለም። ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር፣አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ጠንክሮ የተያዘው በሕወሃትና በትግራይ ሊሆን ይችላል። ይህ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር የኛ ነው ብሎ ፕሮግራሙን ህገ ደንቡን ተቀብለው የገቡ ግን ሁሉም ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች ናቸው። አጋር ድርጅቶችም ጭምር ማለት ነው። ስለዚህ ይሄ አስተሳሰብ የሕወሃት መስመር ነው፤ የኛ መስመር ማለት ይችላሉ አሁን። በፊት ግን በዚህ መስመር ነው፤ በምርጫ ቦርድ ህግ አውጥተው፣ ተመዝግበው፣ ህዝቦቻቸው አካባቢ ክልል ተወዳድረው አሸንፈው መንግስት ሆነው ሲሄዱ የነበሩት። የህወሀት መስመር የተቃወመ እያንዳንዱን የብሄሩን ህዝብ መጠየቅ ይቻላል። በኦሮሚያ ሲያስተዳድር የነበረው ኦህዴድ ነው፤ እናንተ ‹ኦህዴድ ተላላኪ ነው› ብላችሁ ከደመደማችሁ፤ እኛ ግን እንደዛ አንልም።

ዘመን ፡- እንደዛ አላልንም።

አቶ አስመላሽ፡- እነሱ ካሉ ደግሞ ፖለቲካው ስለተበላሸ ነው። እንደዛ ካሉ ግን ለምሳሌ አሁን ያለው የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ምንድን ነው የሚለው? ሁለት ነገሮችን ያነሳል። አንደኛ የኢህአዴግ ድርጅታችንን ጥንካሬ በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እንሄዳለን ይላል። ሁለተኛ በኢህአዴግ ድርጅታችን ፕሮግራምና በጋራ አላማ እህት ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች በየክልላችን ይህን አላማ ለማሳካት ስናደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ስለሆነ ይሄን እንደ መነሻ እንወስዳለን ይላል። እንደዚህ ብለው ካመኑ ‹ኢህአዴግ የሚባለውን አናውቀውም፣የነበረን ፕሮግራም ፌክ ነው፣ ፌዴራሊዝሙ የውሸት ነው› እና የመሳሰሉትን ማለት ተገቢ አይደለም።

ዘመን፡- ኢህአዴግን አናውቀውም ሳይሆን ኢህአዴግ የተሳሳታቸው ስህተቶች ነበሩ። ስልጣን በሕወሃት በሚመራው ማእከላዊ መንግስት በየክልሉ እየተመደበ መሄዱ ከስህተቶቹ አንዱ ነው። ይህንን በማረም የኢህአዴግን ጠንካራ ጎኖች አጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል ነው….

አቶ አስመላሽ፡- እኔ በሕወሃት በማእከላዊ መንግስት የሚመደብ ባለስልጣን አላውቅም። ኢህአዴግ ማዕከላዊውን መንግስት ሲመራው ነበር ማለት ምን ማለት ነው? ለምሳሌ የስልጣን የበላይ አካል ማን ነው? የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይደለም? መቶ ሰማኒያ አምስት ወንበሮች ያለው ኦሮሚያ ነው።

ዘመን፡- ምክር ቤቶች ላይም የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። እስካሁንም ከተደረጉ ምርጫዎች ውስጥ የተወሰነ ተአማኒነትን ያተረፈው አንዱ ምርጫ ብቻ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር አይደል?

አቶ አስመላሽ፡- ስለተአማኒነት እሱን ተወው። ማዕከላዊ መንግስት ማለት ግን ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ሕወሃት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አዲስ አበባን ጨምሮ አርባ ሶስት ወንበሮች ብቻ ነው ያለው። በህዝብ ብዛት ነው የመጣው። ሚዛናዊ ውክልና ማለት ይሄ ነው። በፌዴሬሽን ምክር ቤትም ብታየው እንደዛው ነው።

ዘመን፡- የተወካዮቹ ቁጥራቸው መብዛት ብቻ ሳይሆን ከተፅእኖ በጸዳ መልኩ ንቁ ተሳታፊዎች ነበሩ ማለት ይቻላል?

አቶ አስመላሽ፡- ጠይቀኽኛል እኮ! ይቅርታ ጌታዪ! ስልጣን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እያስረዳሁ ነው።

ዘመን ፡- እሺ ይቀጥሉ።

አቶ አስመላሽ፡- በሚኒስትሮች ምክር ቤትም ስትመጣ እንደዛው ስብጥር ነው። ከትግራይ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ የሚባል ከሆነ ከሰማኒያ ብሄረሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው አንድ ነው። የድሮ ኢህአዴጎችና ሕውሃቶች የምንለው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄን ሀገር በትክክል መርተዋል፣ አልመሩም ነው? በትክክል መርተዋል አልመሩም የሚለውን እንጂ ብሄራቸው ከየትኛውም ይሁን ትርጉም የለውም። ህልፈተ ሞታቸው ሲሰማ በመላ አገሪቱ ከጫፍ ጫፍ ሕዝቡ ሲያለቅስ የውሸት አልነበረም። ስለእሳቸው ስለሰጡት አመራርና የተወሰደው ግምት ነው። ስለዚህ ማዕከላዊ መንግስት ዳኝነትም ብትለው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከሰባ እስከ ሰማኒያ በመቶ የሚደርሰው የአማራ ተወላጅ ነበር። ፌዴራል ሲቪል ሰርቫንቱ ከሰባ እስከ ሰባ አምስት በመቶ የአማራ ክልል ተወላጅ ነው። ይሄ ስለሆነ ምን እንበለው። አማራ ነው የበላይ ብለን እንግለፅ? ስለዚህ ማዕከልም በጋራ ነበር የምንመራው። ተቋማትን በጋራ ነበር የመራናቸው። እዚህ ላይ አቶ መለስ በነበራቸው ብቃት የእሳቸው ሃሳብ የበላይነቱን አግኝቶ ሊሆን ይችላል። የሕወሃት የበላይነት ከተባለ። የመለስ ሃሳብ ለኢህአዴግ ነው እንዴ? በዓለም ደረጃ የሚወዳደር፣በዓለም ደረጃ ምርጥ የአዕምሮ ብቃት ያለው /ወርልድ ክላስ ማይንድ/ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው የፃፉትና ያመጡት ሀሳብ ነው። አሳምነው ከሄዱ አሳምኖ መሄድ ነው። ወደ ሃሳብ እንጂ ለምን ወደ ብሄር ይኬዳል? ይሄ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ትግራይ ነው የተፈጠረው? ባለቤትነቱ የትግራይ ነው እንዴ? የጋራ እኮ ነው።

ዘመን፡- እርስዎ እንደጠቀሱት የአማራም፣ የኦሮሞም፣ የትግራይም የሁሉም ብሄር የህግ ባለሙያዎች ነበሩ። እነዚህ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች አስፈፃሚ አካላት ብቃታቸውም ሆነ በህብረተሰቡ ተአማኒነታቸው የሳሳ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት ታየ እንጂ የምክር ቤት አባላትም ለተመረጡበት ህብረተሰብና አካባቢ ሳይሆን በበላይ ሆኖ ለሚያዛቸው፣ ለሚቆጣጠራቸው አካል ብቻ የሚሰሩ እንደነበሩ አልታየም?

አቶ አስመላሽ፡- ምን አይነት መነቃቃት ነው በቅርብ ጊዜ የመጣው ?

ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የመረጣቸውን ህዝብ ያማከሉ ጥያቄዎችን ማንሳት፣ አስፈፃሚ አካላትን በትክክል መቆጣጠር፣ ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶችን መገምገም እና እንዲስተካከል አቅጣጫ መስጠት የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው። ትክክል አይደለሁም?

አቶ አስመላሽ፡- አይደለህም። የምክር ቤቱን ጉዳይ ለኔ ተውልኝ። ፓርላማውን እኔ በደምብ ስለማውቀው ለኔ ብትተወው ይሻላል። አንደኛ ብቃትና የስልጣን ባለቤትነት ይለያያል። የስልጣን ባለቤትነት ማለት ስልጣን አመንጪው ማነው? አንደኛው ፍትሃዊ ውክልና ምን ይመስላል? ሁለተኛ ራሱ በራሱ የመተዳደር መብት አለወይ? ከእነዚህ ነው የምትነሳው። የስልጣን ባለቤትነት ስለጠየከኝ ነው። ማዕከላዊ መንግስት በሕወሃት ስር ነበር ሕወሃት በእንደራሴ አደራጅቶ አገሪቱን ሲያስተዳድር ነበር የሚለው ከዚህ አኳያ ሲመጣ አይሰራም። ብቃት የተለያየ ሊሆን ይችላል። እኔ ከአንዳንድ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብ ባለስልጣናት ዝቅ ያለ የህሊና ንቃት ሊኖረኝ ይችላል። እንደዛ ብዪ አምናለሁ። ሁሉንም እበልጣለሁ ብዪ አላስብም። ሌላውም እንደዛው። በሕወሃት ውስጥም ያሉ ሰዎች ሁሉ እኩል ብቃት የላቸውም። መለስን የሚያክል ብቃት ያለው ሰውን ያህል ሌላ ነበረ ብለን አንወስድም። ይህንን ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። የብቃት ልዩነት መኖር ግን ከስልጣን ባለቤትነት፣ ከገዢ መሆን አለመሆን ጋር እንዴት ነው የሚያያዘው? ለምሳሌ ያልካቸው ሰዎች ፓርላማ መጥተው እንዳይከራከሩ፣ ሃሳብ እንዳያቀርቡ፣ ህዝቡን እንዳይወክሉ ብቃታቸው እንደፈለጉ ፈጣን ተሳትፎ እንዳያደርጉ ሊገድባቸው ይችል ይሆናል እንጂ በተሰጠ ውክልና ለመስራት እንዴት አድርጎ ይገድባል?

ዘመን ፡- ከዚህ ቀደም በምክር ቤት የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው መልኩ ይነሣ ነበር?

አቶ አስመላሽ፡- ይነሣ ነበር። እንደውም የማይነሳው በአሁኑ ሰአት ነው። ምክር ቤቱ ከመጀመሪያው አንስቶ እኩል አካሄድ ነበረው ብዬ አልወስድም። ምክር ቤቱ ብዙ ችግር ነበረበት። ጫናም ነበረበት። በራስህም ቀመር (ካልኩሌሽን) ውስጥ ትገባለህ። እንዲህ ብዬ ካልኩኝ ምደባዬ ምን ይሆናል? እነ እገሌ ፓርቲ እንዴት ያዩኛል? አድር ባይነት የምንለው ማለት ነው።

ዘመን፡- ታዲያ አድር ባይነቱ ከምን መነጨ? ከፍርሃት አይደለም?

አቶ አስመላሽ፡- አድር ባይነቱ የሚመጣው አንደኛ ራስን ከመውደድ ስልጣን፣ ክብር፣ ጥቅም ስትፈልግ ነው። የህዝብና የአገር ጥቅም ማስቀደም ትተህ ራስህን ጥቅም ስታስቀድም የሚመጣ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይሄን የሚያባብስ ደግሞ ከባቢው (ድባቡ) ፀረ ዴሞክራሲ ሲሆን ነው። የፓርቲ ዴሞክራሲ ችግር ካለበት ማለት ነው። በመናገርህ፣ በመከራከርህ ምክንያት የምትገለል፣የምትጠቃ ከሆነ አድር ባይነት ይኖራል። ይህ ነበረ። ሶስተኛ የራስህ የሆነ ገቢ ደግሞ የለህም። በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በሙያም የተሟላ ጥንካሬ ካለህ እና የትም ቦታ ሰርቼ አድራለሁ ካልክ የፈለገው ጫና ቢኖር ትታገላለህ። ዋናው ግን መጀመሪያ ያስቀመጥኩት ምክንያት ነች። ህይወትህን ጭምር የምትከፍልበት ማለት ነው። ፍርሀት፣ መሸማቀቅ ትተህ ህይወትህን ጭምር የምትከፍልበት ከራሴ ይልቅ አገሬንና ህዝቤን አስቀድማለሁ የሚል የህዝብ ውግንና ካለህ ምንም ነገር አይበግርህም። በስልጣንም አትታለልም። ችግሩ ከዚህ የመነጨ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች የፓርቲ ዲስፕሊን ያነሳሉ። የፓርቲ ዲሲፕሊን ለፖሊሲ ብቻ ነው የሚያገለግለው። ፖሊሲና ፕሮግራም አምነህ ተቀብለህ ከገባህ እሱን ፈፅም ነው። ይሄ ማለት ደግሞ ህዝቡ ጋር ስትወዳደር አሸንፈህ ስልጣን ስትይዝ ይሄን ፖሊሲ እና ይሄን ፕሮግራም እፈፅምልሀለሁ ትለዋለህ ለህዝቡ። ይሄንን የምትፈፅምልኝ ከሆነ ብሎ በአመኔታ ይመርጥሀል። ይሄንን በዲሲፕሊን ፈፅም ማለት ለህዝቡ ተገዢ መሆን ማለት ነው። ለህሊናህም፣ ለህገ መንግስቱ ተገዢ መሆን ማለት ነው። በአፈፃፀምና በፕሮግራም ግን የፓርቲ ዲስፕሊን የለም። ልዩነትም መፍጠር መከራከርም ትችላለህ።

ለምሳሌ 2008 ዓመተ ምህረት አካባቢ የነበረው ሁኔታ የተሻለ ንቅናቄ ነበር። ጥሩ ፓርላማ የምለው 2008 እና 2009 የነበረውን ነው። ትንሽ ከ1998 ጀምሮ እስከ 2000 ዓመተ ምህረት ድረስ በርከት ያሉ ተቃዋሚዎችም ገብተው የነበሩበት ወቅት ስለነበር። ፓርላማውን አንድ ሶስተኛ የሚያክል ተቃዋሚዎች በመኖራቸው መነቃቃት ነበር። የኢህአዴግ ሰዎች ብቻቸውን ወንበር በያዙበት ወቅት ግን 2008 እና 2009 የነበረው ደህና ነበር። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ሳይሰሩ ተሰርተው ጠፍተዋል የተባሉ ፎቆች ነበሩ፤ በአንዳንድ የሜቴክ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ተነሱ ሀሳቦች እና እንደዚህ የሚዘረዘሩ በርካታ ጥሩ የሚባሉ ስራዎች ተሰርተዋል። እነዚህ በተፈለገው መጠን ሄደዋል ወይ ስትል አልሄዱም። መጨረሻ ላይ በአስፈፃሚው አካል ጫናዎች መጥተዋል። ጫናውን ተቋቁሞ እስከ መጨረሻ አልሄደም። እንደዚህ ብለን የምናስቀምጣቸው ጉዳዮች አሉ። እንዲህ አይነት ነገር አልነበረም እያልኩህ አይደለም። ነገር ግን አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ስታወዳድረው ያ ሁሉ ህዝብ ተፈናቅሎ፣ በየቦታው ህገ መንግስት ተጥሶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በወታደር ስልሳ በመቶው የአገሪቱ አካባቢዎች በዚህ አዋጅ እየተዳደረ፣ በጅምላ ህዝብ እየተገደለ፣ መንገድ ተዘግቶ፣ እስኪ እንደኢትዮጵያውያን አስቡት! የትግራይ መንገድ ከተዘጋ ሁለት ዓመት ሆነው። ማንን ነው እየጎዳ ያለው? ድሀ አባት፣ድሀ እናት፣ድሀ ተማሪ በአፋር ዞሮ ለመሄድ እኮ ከሁለት መቶ ብር በላይ ተጨማሪ ክፍያ እየከፈለ እየሄደ ነው ያለው።

ዘመን፡- በእርግጥ እየተዘጋ ያለው የትግራይ መንገድ ብቻ አይደለም እኮ?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ! እንደዛ አታዳላ። ያ ሁሉ ነገር ሆኖ እያለ ፓርላማው አልጠየቀም። የደብረ ብርሃንና የጎጃም መስመር ሲዘጋ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ሲቀርቡ ነው ጥያቄ የቀረበላቸው። እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ? የሚል ጥያቄ ነው ያነሳሁት። ለምን ? ሁለት ዓመት ሙሉ የተዘጋ የትግራይ መንገድ ጥያቄም ሲቀርብ እየታፈነ እንቅስቃሴ አልተደረገም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የመለሱት የደብረ ብርሃን እና የጎጃም መንገድ መዘጋትን ነው። ስለትግራይ መንገድ መዘጋት ይፈልጉታል የሚል ነገር እንሰማለን። በጀት እንቆርጣለን፣ አንዳንድ ጊዜ እኮ እብድ መንግስት ነው የመጣው ያስብላል። እንዴት አድርጎ ነው የትግራይ በጀት የሚቆረጠው? እንዴት አድርጎ ነው ስልክ የሚቆረጠው? እንዴት አድርጎ ነው መብራት የሚቆረጠው? እንዴት አድርጎ ነው ወደ መቀሌ የሚደረገው የአውሮፕላን በረራ የሚቀነሰው? የትግራይ መንግስት፣ የትግራይ ክልል እኮ የፌዴሬሽኑ አካል ነው። የፌዴራሉ አካል እስከሆነ ድረስ ማንም ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፈልግ የሚሰጥህ ሲፈልግ የሚከለክልህ አይሆንም። እንደዛ ከተባለ በትግራይ ህዝብ ጦርነት እንደታወጀ ነው የሚቆጠረው። ገንዘቡ የሚመጣው ከብሄር ብሄረሰቦች ለክልል በቀመር ይከፋፈላል። እናም እስከዚህ ድረስ የማይሆን ነገር እየሰማን ነው። ተመለሱ እያበዳችሁ ነው የሚል የምክር ቤት አባል የለም። በአሁኑ ሰአት አዋጆቹ ሲፀድቁ የትኛው ክልል ነው የሚማከረው? ምርጫ ህጉም ሆነ ሌላ ህግ ፀደቀ ለክልሎች አልተላከም። አልታተመም/ፕሪንት አልተደረገም/።

ዘመን ፡- ሕወሃት በሌሎች ክልሎች ጉዳይ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አልነበረውም፣ እንከን የለሽ ነበር ? የፌዴራል ሥርዓቱን በማዋቀርና በትጥቅ ትግሉ ግንባር ቀደም ሚና ቢኖረውም በተፈጠሩ ውስንነቶች ግን ይቅርታ የሚያስጠይቀው ምንም ጉዳይ የለም ብለው ነው የሚያምኑት ?

አቶ አስመላሽ፡- ይሄንን እንዴት እናየዋለን መሰለህ! መጀመሪያ አካባቢ 1983 ዓመተ ምህረት ደርግ ከተወገደ በኋላ በስምምነት በየክልሉ የሚሰማሩ ካድሬዎች ነበሩ። ብዙዎቹ ከሕወሀት ናቸው። ትንሾቹ ደግሞ በዚያን ጊዜ ኢህዴን በኋላ ብአዴን በአሁኑ አዴፓ ከሚባለው ድርጅት የሚሰማሩ ካድሬዎች ነበሩ። የእነዚህ ካድሬዎች ተልእኮ ግልፅ ነበር። ሕወሃት በትግሉ የተሻለ የህዝብ አደረጃጀት እና የህዝብ ግንኙነት እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም በአስተዳደር ስራም ልምድ አለው። ከሕወሃት ቀጥሎ ኢህዴን ከዛም ኦህዴድ እያለ ይሄዳል። ይሄ ልምድ በየክልሎች እንደየተሞክሯቸው ልምድ ሆኖ እንዲያዝ የተሰማሩ ካድሬዎች ነበሩ። እነዚህ ካድሬዎች ተሰማርተው ብዙ አጋዥ ስራ ሰርተዋል። የህዝብ አደረጃጀት ልምድ እንዴት ይሰራል፣ አስራ ሰባት ዓመታት ልምድ አለ። የህዝብ ግንኙነት ስራም የፖለቲካ እና የቅስቀሳ ስራ እንዴት እንደሚሰራ ልምድ አካፍለዋል። ስለ አባል ምልመላ፣ ስለአባል መረጣ፣ ስለ ድርጅት ስራም እንደዚሁ። ይህንን ስራ ለማገዝ በየክልሉ ሄደዋል።

ዘመን፡- ተጠይቃችሁ ነው?

አቶ አስመላሽ፡- አዎ! እንደ ኢህአዴግ እነዚህ ሰዎች ሄደው ሲሰሩ አልፎ አልፎ በተወሰኑ ሰዎች ደረጃ በፖሊሲ ባይሆንም አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት አልነበረም ብቻ ሳይሆን በ1993 ዓመተ ምህረት በተደረገው ተሃድሶ እንቅስቃሴ ገምግመነዋል። ይሄ ነገር ከሚገባው ጊዜ በላይ ቆይቷል። ከአሁን በኋላ የልምድ ልውውጡ እና ሌላው ነገር በቂ ነው፣ በሂደት የሞግዚት አስተዳደር ሊፈጥር ስለሚችል መቆም አለበት ተብሎ ተገምግሟል። ይህንን አቶ ደመቀ መኮንንን፣ አቶ አባ ዱላ ገመዳን እና ሌሎች አመራሮችን ጠይቁ።

ዘመን፡- ከግምገማው ከ1993 በኋላ ባሉት ዓመታት ተስተካክሏል? ጣልቃ ገብነት አልነበረም?

አቶ አስመላሽ፡- ገምግመን በብዙ መንገዱ ተስተካክሏል። ከአራቱ ድርጅቶች አራት አራት ሰዎችን መመደብ እስካሁን ድረስም ቀጥሏል። አሁንም አለ። ተመድበው የሚያግዙ ማለት ነው። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን እየሆነ መጥቷል፤ በተለይ ከ1993 ዓመተ ምህረት ግምገማ ከተደረገ በኋላ የግምገማው ሰነድ አለ ማሳየት እችላለሁ በብዙ መንገድ ተስተካክሏል። ይሄ ነገር የተደረገው ለማገዝ ነው። አንዳንዱ ለምሳሌ በደቡብ 1993 በኋላ የቀጠለ አይመስለኝም። በኦሮሚያም በፊት ነበር። አሁን የለም። አጋር ድርጅቶች ያሉበት ክልሎች ነው የቀጠለው። ልምድ፣ ተሞክሮ ልውውጥ ያስፈልጋል በሚል የቀጠለ ነው። ይሄ የሞግዚት አስተዳደር የሚባል ግን በኢትዮጵያ ለመጣ ፌዴራሊዝም ለመጣው ለውጥ እንዴት አድርገን እናደርገዋለን። አሁን እያያችሁት ነው። ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን የሚቃወም አሁን አለ? ለምን አይቃወሙትም? ስምምነት ስለተፈጠረ ነው። ህዝብ ስላጣጣመው ነው። ራስን ማስተዳደርና ሚዛናዊ ውክልና። ይህንን አፈርሳለሁ የሚል ኃይል ካለ አይሆንም። ወደ ምኒልክ፣ ወደ አፄ ኃይለስላሴ፣ወደ ደርግ ሥርዓት ይመልሳል። ይህንን ይፈልጋታል፣ይቃዣታል እንጂ አያደርጋትም። ይህ የተፈጠረው ለምንድን ነው? ስላጣጣመው ነው። ራሱን በራሱ ስላስተዳደረ ነው። ይሄ ባይሆን ኖሮ ህዝቡ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ገደል ይግባ ለምን አይልም? ኢዜማ ሳይቀር ብዙ ጊዜ ሲቃወም፣ ሳይናገር ቆይቶ አሁን እየተናገረ ነው። በሁለት ምክንያት ይመስለኛል። አንደኛ ነሃሴ አካባቢ የፌዴራል ሃይሎች በመሰብሰባቸው፤ ሁለተኛ በዋናነት ጀዋር አካባቢ የነበረችው ንክኪ የኦሮሚያ ህዝብና ወጣት ከጫፍ እስከ ጫፍ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም አይነካም ሲል ሁሉም ግልብጥ ብሎ ህብረ ብሄር እያለ ነው ያለው። ይህ የሚያሳየው የሞግዚት አስተዳደር አሐዳዊነት ተብሎ ሊወሰድ አይችልም ብዬ አስባለሁ።

ዘመን፡- የጠቀሷቸው አራት ሰዎች በቋሚነት በየክልሉ ተመድበው የሚሰሩ ከሆነ ተሞክሮ ማካፈል በቋሚነት ያስመድባል? የተመደቡት ሰዎች የሞግዚት አስተዳዳሪ የማይሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ፡- የማይሆኑበት ምክንያት ምን መሰለህ! በምክር ቤቱ የሚደረገው ውሳኔ፣ ውይይት እጃቸውን አያስገቡም። ካቢኔው ከርእሰ መስተዳድሩ ጀምሮ የሚወስነው በራሱ ጉዳይ ነው የሚሄደው። ዳኝነትም እንደዛው ነው የሚሄደው። እነሱ የሚያግዙት ከላይ በጠቀስኩልህ አግባብ ነው። በክልሎቹ ጥያቄ በራሳቸው በጀት ያሰማሯቸው ሰዎች አሉ፤ ሌላው ይቅርና…..

ዘመን፡- የምክር ቤት ስብሰባ ከመደረጉ ቀደም ብሎ የተመደቡት አራት ሰዎች ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጋር ይወያያሉ፣ ያማክራሉ፣ የሚነሱ አጀንዳዎችን ይሰጣሉ በመሆኑም ወደ ምክር ቤት ውይይት የሚገባው በእነዚህ ሰዎች የተወሰነ ውሳኔ ተይዞ አልነበረም ?

አቶ አስመላሽ፡- ይህንን አላውቅም።

ዘመን፡- አሁን ደግሞ «ፌዴራል ሥርዓቱን እንታደግ፤ ሕገ መንግሥቱ ይከበር» የሚል እንቅስቃሴ ለማድረግ መቀሌ ላይ በተጠራውም ጉባኤ ሕወሃት ግንባር ቀደም ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ተባባሪ እንዲሆኑ ከጠየቃችኋቸው ድርጅቶች በተነጻጻሪ ተሰሚነት አላቸው የሚባሉ ድርጅቶች በእናንተ ጉባኤ ለመገኘት የሕወሃትን ይቅርታ መጠየቅ ቅድመ ሁኔታ አድርገዋል፤ ሕወሃት በዚህ ደረጃ ይቅርታ እንዲጠይቅ ግፊት እየተደረገበት አይደለም?

አቶ አስመላሽ፡- ይሄን እኔ አልሰማሁም። እንደገናም ሕወሃት ለብቻው ያስተዳደረው ሀገር የለም። ደግ ደጉን ትወስድና መጥፎ መጥፎውን ለሕወሃት ነው። ቀደም ብለህ እንዳነሣኸው ለምሳሌ የኢህአዴግን በጎ ነገር እንወስዳለን፤ መጥፎ መጥፎ ነገር ግን ለምሳሌ ሕውሃት በየቦታው እንደራሴ እየላከ ሞግዚት የነበረውን እናስተዳድራለን ብሏል ብልጽግና ባልከው እንዲህ ዓይነት ነገር ነው እየሆነ ያለው። ስለዚህ ሕውሃት ችግር ኖሮ እንደ ችግር ገምግሞ ይቅርታ ለማለት እኮ የሚያፍር ድርጅት አይደለም። በደርግ ጊዜም ጭምር በረሃ እያለም፤ በነበረን የሬዲዮ ተደራሽነት፣ የጋዜጣ ተደራሽነት ችግር ውስጥ ሆነንም ገምግመናል፤ 77 ዓመተ ምህረት። የ10 ዓመት ጉዞ ገምግመን 1፣ 2፣ 3 ብለን ቆጥረን በግልጽ ይሄ ድርጅት በዚህ ችግር ተዘፍቆ ነበር ፤ በዚህ፣ በዚህ እንወጣለን ብለን አውጀናል። በየጊዜው የነበረው ችግር ማለቴ ነው። የ1993ቱን ብትወስዱትም እንደዚያ ነው።

ዘመን፡- ከ1993 በኋላስ?

አቶ አስመላሽ፡- 1993 ያደረግነው እንደ ኢህአዴግ ነው። 2010ም እንደ ኢህአዴግ ገመገምን አይደለም፤ መጀመሪያ ሕውሃት 35 ቀን ቁጭ ብሎ ሲወያይ፤ ሲገመግም በትግራይ ውስጥ የነበረውን ችግርም ይሁን በሌላ የፈጠረውን ችግር የለያቸው፤ በራሱ ባስተዋጽዖው ነው የመዘነው። የራሴ አስተዳደር ምናምን ብሎ ሳይሆን፤ በዚያ ልክ የ2010 ሕዳር ላይ የነበረው መግለጫ ማየት ትችላላችሁ። ችግሩን እንዴት አድርጎ፤ ራሱ እንዴት አድርጎ ዕርቃኑ ወጥቶ ማለት ነው። እዚህ ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ሲመጣም በርቃኑ ነው የገባው። ችግሬ እነዚህ ናቸው ብሎ ቆጥሮ። እንደ ሕውሃት ቆጥሮ የመጣ ድርጅት አለ እንዴ? የለም እኮ። ብሬክ ስሩ /እመርታ ያለው/ ነው የሕወሃት ግምገማ። በዚያን ጊዜ እኛንም ያስተምረናል ነው እኮ ያሉት ሰዎቹ። ይሄንንም ‹ፈርተን ነበር› ካሉ ምንም አታደርገውም እንጂ። ከዚህ አኳያ ስታየው ታህሳስ የአሥራ ሰባቱ ቀናት በኋላ የአራቱ በብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በድርጅት ወጥተው ለጥፋቱም ለችግሩም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል። በዚያ የሚታቀፍ ከሆነ እንደዚያ ነው።

ዘመን፡- አሁን እንግዲህ የኢሕአዴግ አመራር ሦስት ዐሠርት ዓመታት ያህል አሳልፏል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግሥቱም የተቀመጠው አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የተያዘውን ውጥን አሣክቷል ብለው ያስባሉ?

አቶ አስመላሽ፡- አዎ።

ዘመን፡- አሁን ከተፈጠረው ውጥንቅጥ አንፃር አስተያየት ይስጡበት!

አቶ አስመላሽ፡- በድሮው ጤናማው ኢህአዴግ እና በሕውሃቶቹ ግምገማ ብዙ ነገር አሳክተናል ብለን እንወስዳለን። ለምሳሌ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ማለት ምን ለማለት ነው? አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ማለት አንድ የጋራ ገበያ መፍጠር ማለት ነው። አንድ የጋራ ገበያ መፍጠር ማለት አንዱ ጫፍ ያለው የኢትዮጵያ ክፍል ከሌላው ጫፍ፤ አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ሳይተሳሰር፤ ሳይገበያይ መኖር የማይችልበት ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። ረቂቅ ነገር አይደለም። ከዚህ አኳያ ስታየው ኢትዮጵያ ከጫፍ ጫፍ በመንገድ አልተያያዘችም? በዚህ 27 ዓመት ከ 120 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እኮ ነው የተሠራው። ስንት ኤር ፖርት ነው ያለው እዚህ ሀገር? የሥልክ መሥመሩስ ከተማ ብቻ ነው ያለው? ገጠሩም ጭምር እኮ ነው ዲጂታል ዲቫይድ የሚባል ነገር እኮ አስቀርቷል። ገጠር እና ከተማው እንዲገበያይ፤ እንዲተሳሠር። መብራትም ብትወስድ እንደዚያ ነው። ከተማ ለከተማ የሚታደል ነው? አይደለም። ገጠሩም ጭምር ነው። ትምህርት ብትሄድም እንደዚያው፤ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በእያንዳንዱ ቀበሌ በኢትዮጵያ ሙሉ። በጤና ጤና ኬላ፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል። በአሁኑ ሰዓት ስንት ዩኒቨርሲቲ፣ የተማረ የሰው ሃይል አለ? የተማረ የሰው ሃይል ሲኖር ነው ገበያ የሚኖረው። የኢንቨስትመንት ፍሰቱ የሰመረ ለማድረግ ተችሏል። የጋራ የሆኑ ፕሮጀክቶችም እንደዚሁ። 27 ዓመት የትም፣ የትም በዚህ መንገድ ያደጉ ሀገሮች ብትጠይቅ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለማምጣት ከሚገባ በላይ ተሠርቷል። ቦረና ያለው ከሰሜን ጫፍ፤ ምሥራቅ ያለው ከምዕራብ ጫፍ ይገናኛሉ እኮ በአጭር ሰዓት። በሥልክም በለው፣ በመንገድም በለው፣ በአውሮፕላንም በለው ነፃ ገበያ የሚሉት ምዕራብ አውሮፓ ያደገበት መንገድ እንደዚህ ነው። ከዚህ አኳያ ስታየው ብዙ ተሠርቷል።

በፖለቲካ የተኬደበት አለ። አሁን በፖለቲካ በሕገ መንግሥቱ በሆኑ ፖሊሲዎች የጋራ መግባባት ፈጥረናል አንልም። በአንዳንዶቹ ፈጥረናል፤ ለምሳሌ ኅብረ ብሔራዊ

ፌዴራሊዝም። አንድ ጊዜ ስጠየቅ ያልኩት ነገር ነበር፤ ለምሳሌ ‹ፌዴራሊዝም ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አያስፈልግም› የሚል ካለ ያለ ማደንዘዣ የሰው ጥርስ እንደመንቀል ይቆጠራል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በድሮው ኢህአዴጎች እና ሕውሃቶች በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል። ሌሎቹ ጊዜ ይፈልጋሉ። አሁን ያለው ውጥንቅጥ ያልከው እንዳውም እኔ ከዚህ በተቃራኒው ነው የማየው። ሦስት አራት ዓመት እኮ በዚህ ሀገር በልማት ምን ተሠራ? እስኪ ንገረኝ። ባለፈው 27 ዓመታት የሠራናቸው ነገሮች ካፒታል እኮ ነው እየበላን ያለነው። እየበላን እየበላን ጨርሰን እኮ ነው ያለነው። መኪና በፍጥነት ይሄድ የለ ነዳጅ ሲያገኝ፤ ፍጥነት ከነበረው ነዳጅ ጨርሶም ይሄዳል ።

ዘመን፡- የወቅቱን ውጥንቅጥ ሕውሃትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመስማማት ያመጣው አይደለም?

አቶ አስመላሽ፡- ያለመስማማት ውጤት አይደለም። እንደዚያ እንዳትወስዱት።

ዘመን፡- እና ምን ሊባል ነው?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ። አለመስማማት እና መበሻሸቅ ልዩነት አለው። ልዩነት የለንም። መበሻሸቅም አይደለም። የአሰላለፍ ጉዳይ ነው። 1993 ኢህአዴግ? ምንድን ነው የገመገመው አሁን ያለው የሕዳሴ ጉዞ ሊቀለበስ ይችላል፤ የሚቀለበሰው ደግሞ በውጭ ሳይሆን በኢህአዴግ በራሱ ነው። ይህን ሀገር የሚጎዳው ኢህአዴግ ውስጥ ያለው አመራር የተሰጠውን ሕዝባዊ አደራ፣ ሥልጣንን ለኅብረተሰብ ለውጥ ማዋል ትቶ ለራሱ ጥቅም፣ ለራሱ ክብር፣ ለራሱ ሥልጣን የሚያውልበት ሁኔታ ሲኖር፤ በውስጡ የመበስበስ፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ሙስና ሲስፋፋ፣ የተለያዩ አመለካከቶች እየጎሉ ሲመጡ በኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጠር ኃይል ነው የሚል ግምገማ በ1993 ተገምግሟል። የሆነው ቢሆንም የሥርዓቱን አደጋ ለይተናል፤ ምክንያቱን አስቀምጠናል፤ መፍትሔውንም አስቀምጠናል፤ መፍትሔውን ይዘን ምክንያቱን እና ችግሩን ለመፍታት ያደረግነው ትግል ስላልተሳካ ይሄ ችግር ተፈጥሯል። እልህ አይደለም፤ መበሻሸቅ አይደለም። አሁን የተፈጠረው ችግር ይሄ ነው። ትግራይም ሊፈጠር ይችላል፤ የትም ሊፈጠር ይችላል። የብሔር እንትን የለውም። አመለካከቱ አሰላለፉ ነው የሚወስነው። እና መነሻው ይሄ ነው።

ዘመን፡- የሕወሃት አመራሮች የማንነትና የክልል ጥያቄ ተመልሷል የሚል ድምዳሜ ላይ የደርሳችሁ ቢመስልም አሁን ግን እንደ አዲስ እያገረሸ ይገኛል። እንደ ሲዳማ ያሉ ብሄሮች ከመነሻው ጀምሮ ጥያቄ ቢያነሱም የሰማቸው አካል ሳይኖር ቆይቶ አሁን ምላሽ አግኝተዋል። ታዲያ! ʻይሄንን የቤት ሥራ እናንተ ናችሁ አፍናችሁ የቆያችሁትʼ ለሚሏችሁ ሰዎች ምን መልስ ትሰጣላችሁ?

አቶ አስመላሽ፡- የታፈነ የብሔር ጥያቄ የለም። የዚህ ፍሬም ወርኩ ሕገ መንግሥቱ ነው። ሕገ መንግሥቱ መደጋገም እንዳይሆንብኝ ቀደም ብዬ ያስቀመጥኩዋቸውን ጥያቄ መልሷል። እስከ አንቀጽ 39 ጭምር ማለት ነው። ራስህን ታስተዳድራለህ፤ በጋራ ጉዳይ ደግሞ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማለት ነው። ፌዴራሊዝሙ የተደራጀው ቋንቋን፣ ባህልህን፣ ታሪክን ወዘተ. አካባቢውንም እንደዚሁ በብሔር መልክ አሰፋፈር እንደዚያ ነው። ይሄ ነገር ካልተስማማህ፣ በደል እና ጭቆና በዝቷል እና እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታየሁ ነው ብለህ ካመንህ ደግሞ ባሪያ ሆነህ መቀጠል ስለማትችል እስከ መገንጠል መብት ይኖርሃል ብለናል። ከዚህ አኳያ ስታየው ዋናው ነገር ኢትዮጵያን ያቆያት ይሄ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ጭቆና እንዳይመለስ ዲዛይን ተደርጓል የሚለው በሕገ መንግሥቱ እንደዚያ ነው። ነገር ግን ይሄ ዴሞክራሲያዊ የሆነው ሁኔታ እየተበላሸ እየተበላሸ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ መንግሥት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሁኔታ ከተፈጠረ ግን የብሔር ጭቆና እንደገና ሊያገረሽ ይችላል። ይሄ እየነገርኳችሁ ያለ የመቼ ነው? በ1993 በተጻፈ ሠነድ ያለ ነው። ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ከመጣ ብሔራዊ ቅራኔ እና ብሔራዊ ጭቆና እንደገና ሊያገረሽ ይችላል። አሁን እየታየ ያለው ይሄ ነው። አሁን የሲዳማን አንስተሃል፤ እነዚህ 56 ብሔር ብሔረሰቦች በፍላጎታቸው አንድ ላይ ከተሰባሰቡ የተሻለ ገበያ ይኖራቸዋል። የተሻለ ድምጽም ይኖራቸዋል። ከዚህ አኳያ አንድ ላይ ቢሰባሰቡ ይሻላል፤ የሚል አቋም ተይዞ ኢህአዴግም ይሆን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ድርጅቶች ባደረጉት እንቅስቃሴ ይሄ ክልል ተፈጥሯል (ተመሥርቷል)። በመሃሉ ሲዳማ የእኔ ክልል፤ ሌላው የእኔ ክልል የሚል ነገር ነበረ። ውይይት ሲደረግ ነበር ። ሕዝቡን እኮ አታፍነውም። ሕዝቡ የራሴን ክልል እመሠርታለሁ ካለ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ግልጽ ነው። የክልሉ ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ይወስናል፤ ምክር ቤቱ ደግሞ በአንድ ዓመት የሕዝበ ውሳኔ ያዘጋጃል። በአብላጫ ድምጽ የወሰነው ይሆናል። ወዲያውኑ የፌዴራሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴሬሽኑ አባል ይሆናል ነው የሚለው ክልሉ። በዚህ ሕገ መንግሥት ነው የተፈጸመው። አዲስ የመጣ ሕገ መንግሥት አይደለም፤ የነበረ ነው። አፈፃፀሙ ላይ ሲዳማ ብዙ ጊዜ ጠይቋል፤ ውይይት ሲደረግ ነበር፤ እንግዲህ ሕዝቡ ሳያምን ሳይቀበል ቆይቷል ማለት ነው። ሳይቀበል ሳያምን ከቆየ የነበረውን አካሄድ ለግምገማ ክፍት ልታደርገው ትችላለህ።

ዘመን፡- ሕዝብ ጠይቆ ወደ አደባባይ ወጥቶ ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች ሞተዋል?

አቶ አስመላሽ፡- እንደዚህ ዓይነት ነገር ነበረ፤ አዎ። ይሄ ነገር ግን ወጥቶ መቀስቀስ ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ እኮ ወጥቶ ተወያይቶ በቀበሌ እንዳልኩህ አሁን እንደተደረገው ተደርጎ ተወያይቶ ሊሄድ ይችል ነበር። ይሄ ነገር በመሠረቱ የሚከለክል ነገር ነበር ወይ? ባያያዙ ባካሄዱ ግን ቅድም ያልኳችሁ እነዚህ 56 ባንድ ላይ ቢሆኑ የራስ ብሔራዊ ድርጅቶች እኮ ናቸው። በዚህ ዓይነት አደረጃጀት ነው የቀጠለው። አሁን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ይፈታ ሲባል ድሮ ያላደረገውን የሚያስብል ነገር አይደለም። አንደኛ 2010 የገመገምነው የተለያየ የሕዝብ ጥያቄዎች ሕዝብ በፈለገው መንገድ ሄዶ፤ ቢሳሳትም እንኳ ተሳስቶ፤ ከተሞክሮው ተምሮ የሚፈጽምበት ሁኔታ በመፍጠር ከሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አያያዝ፣ ከተቋም ዴሞክራሲያዊ አያያዝ፤ ከፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲ፣ ከሚዲያ ነፃነት የመሳሰሉ ችግሮች በዝርዝር ገምግመናል። የዚሁ አካል ሆኖ ሊወሰድ ይችላል እንደ ኢህአዴግ ማለት ነው። ሕውሃት ወሳኝ ነበር የሚል ነገር ስለያዛችሁ፤ ደጋግማችሁ እየጠየቃችሁ ነው እንጂ፤ እንዲህ ዓይነት ነገር አይደለም።

ዘመን፡- እዚሁ ላይ እንዲያነሡት ሕወሃት በራሱ ክልል ያሉ የማንነት ጥቄዎችን ሳይመልስ በአማራ ክልል የቅማንት የማንነት ጉዳይን እያነሳ እየሰራ ነው የሚል አለ?

አቶ አስመላሽ፡- መቼ አነሳን? ቆይ ልንገርህ፤ የቅማንት የማንነት ጥያቄ እኛ አላነሳንም ። አንስተንም አናውቅም። እዚያ የተለያየ በደል ሲደርስባቸው ግን ሚዲያው ተደራሽ ነው። እንደ ኢቢኤስ፣ እንደ ፋና፣ እንደ ዋልታ ካላፈናችሁ ካልተባለ፤ በእሱ አናምንም። ምንም ነገር ይወጣና ይስተካከላል። ምክንያቱም 2010 ታህሳስ እና መጋቢት የገመገምነው እኮ አንዱ የሚዲያ ነፃነት ነው። ሚዲያው የፈለገው ሀሳብ ያንፀባርቅ በሚል ነው እንጂ፤ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ሕውሃት አላነሳም። ራሳቸው ናቸው ያነሱት።

ትግራይ ውስጥ ማንሣት ያለበት እዚያው የሚኖር ሰው ነው። እንግዲህ የማንነት ጥያቄ ማለት የመሬት ጥያቄ ማለት አይደለም። የግዛት ጥያቄ ማስፋፋት ማለት አይደለም። ይሄ የዱሮ የዐፄዎቹ አመለካከት ነው። እንዳይመለስ ተቀብሯል። የማንነት ጥያቄ ማለት አንድ ሕዝብ የእኔ ቋንቋ ይሄ ነው፤ የእኔ ታሪክ፣ የእኔ ባህል ይሄ ነው። ስለዚህ ታሪኬ፣ ቋንቋዬ እና ባህሌ በሚፈቅደው ልደራጅ ብሎ የማንነት ጥያቄ ሲያነሳ ነው፤ ያ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱም የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሕጎችም የሚሉት ማለት ነው። በዚህ መልክ በወልቃይት የተነሳ ጥያቄ የለም። በዚህ መልክ በኢሮብ የተነሳ ጥያቄ የለም፤ ኢሮብ በክልሉ ስላለ። በዚህ መልክ በራያ የተነሳ ጥያቄ የለም። ከትግራይ ውጭ ግን …

ዘመን፡- በራሳችን ቋንቋ እንማር አላሉም?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ። ከትግራይ ውጭ ግን የተለያዩ አስመላሽ ኮሚቴዎች አሉ። እናውቃለን። እንግዲህ አዴፓዎቹ ‹በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር ሦስተኛ ወገን አለ› ብለው በሕወሃት ላይ ጣታቸውን ሲቀስሩ እነሱ ግን መዓት/ብዙ/ አስመላሽ ኮሚቴ እያንጋጉ ሦስተኛ ወገን የሚባለው ለእነሱ አይመለከትም? ትግራይን እየበጠበጡ ያሉና ለመበጥበጥ የሚሞክሩት እነሱ ናቸው። አስመላሽ ኮሚቴ ጎንደር ሆኖ፤ ባህር ዳር ሆኖ፤ ሌላ ቦታ ሆኖ አዲስ አበባ ሆኖ አስመላሽ ኮሚቴ ብሎ ሲጨፍር እንሰማለን። ይሄ ምን ማለት ነው? ወልቃይት ያለው ሕዝብ ሲጠይቅ እኮ ነው፤ ከቀበሌ ጀምረህ የወረዳ ምክር ቤት አለ፤ ቃፍታ ሁመራ አማራ ነኝ ካለ ፤ ወልቃይት አማራ ነኝ ካለ፤ ሰቲት ሑመራ አማራ ነኝ ካለ፤ ፀገዴ አማራ ነኝ ካለ፤ /በፀገዴ አሁን ስለተጀመረ ነው አይነሳም ነበረ፤ አሁን ጀምረውታል።/ የወረዳው ምክር ቤት ከቀበሌ ጀምሮ እየተወያየ፤ የማንነት ጥያቄ አለኝ ብሎ ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄውን ያቀርባል። ክልል እንደሚመሠረተው ዓይነት አንድ ዓይነት ነው።

ዘመን፡- የወልቃይት ነዋሪዎች አልጠየቁም?

አቶ አስመላሽ፡- አላደረጉም። በፍፁም።

ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በሕጉ መሰረት ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ያላገኙ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ይሄ እንደሆነ ነው የሰማነው?

አቶ አስመላሽ፡- በል አምጣው እና ይንገረኝ። ነጭ ውሸት ነው ይሄ። አቶ ካሣ፤ ማን ነው የነበረው? ከመጀመሪያው ጀምሮ አፈ ጉባዔዎች ሁሉ ጀምረህ ልትጠይቅ ትችላለህ። እንደዚህ የሚልህ ሰው ካለ ስህተት ነው። እየነገርኩህ ነው። ትግራይ ውስጥ የትግራይ ምክር ቤት ለምን አትጠይቁም? ወልቃይት ያልከው ቃፍታ ሑመራ ፣ የወልቃይት፣ የፀገደ ወረዳ ምክር ቤቶች አሉ፤ የአላማጣ ወረዳ ምክር ቤት አለ፤ መጠየቅ እኮ ይቻላል። ነገር እኛ ሕውሃት እና የድሮው ኢህአዴጎች የታገልነው እኮ ለሕዝብ ማንነት ነው።

ዘመን፡- ኮለኔል ደመቀ ዘውዴ የሚያስተባብሩት ኮሚቴ ጥያቄውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ወስዶ አልጠየቀም?

አቶ አስመላሽ፡- እነሱ እኮ አስመላሽ ኮሚቴ ናቸው። አስመላሽ ኮሚቴ ማለት ምንድን ነው? በውጭ ሆነህ መሬቱ የአማራ ነውና ወደ አማራ ይምጣ ብሎ በገንዘብ ተገዝተው የሚሠሩ ሰዎች ናቸው።

ዘመን፡- ኮሚቴው ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በቂ ቁጥር ያለው ፊርማ አላሰባሰበም?

አቶ አስመላሽ፡- ሕጉ የሚፈርመው የማን ነዋሪ ነው ይላል?

ዘመን፡- ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው የፈረሙት?

አቶ አስመላሽ፡- አዎ! ነዋሪ ያልሆኑ ናቸው የፈረሙት። ይህ ማለት ምን መሰለህ በወልቃይት በእያንዳንዱ ቀበሌ የሚኖሩ ሰዎች፤ እዚያ መታወቂያ ያላቸው፤ እዚያው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው መፈረም ያለባቸው። ወረዳም እንደዚያ ነው። እንደዚያ ከፈለጉ እኮ የደመቀ መኮንን/ ዘውዴ ማለታቸው ይሆን?/ ማንነት አባቱ በትግራይ ፣ በድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን ሰምተሃል መቼም ሲረግሙት። እንደዚያ እኮ ነው! አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተበላሽቷል። ገበያ ሆኑዋል እኮ፤ ፖለቲካ መነገጃ ሆኑዋል እኮ። ገንዘብ ይፈሳል፤ ትታደላለህ፤ ትናገራለህ፤ ትጮኻለህ መኪና ይሰጥሃል፤ የሕዝብ ሀብት ራሱ በሙስና መልኩ ነው ለግለሰቦች እየተሰጠ እየዋለ ያለው። ሕዝቡ እኮ አንድ ጊዜ ይጠይቃል። አሁን ባይጠይቅም። መዐት ገንዘብ እየፈሰሰ እኮ ነው ያለው። መዐት ገንዘብ፤ ለገንዘብ እና ለጥቅም የሚያድር ሰው አንስቶታል። እንዲህ ያለ ነገር ነው የምናየው።

ዘመን፡- በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ፌዴራል ሥርዓቱ የተናጠው በተለይ የሕወሃት ነባር አመራሩ በየክልሎቹ ጣልቃ የሚገቡት በሆቴል ንግድ፣ በጨው ንግድ ወዘተ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ስለነበራቸው ነው። በመሆኑም ቁጥጥሩ ቀጥሎ የሚፈልጉትን ለማሾም ለማሸለም ፍላጎት አላቸው የሚል አስተያየትም ይነሳል። በዚህ ጉዳይ ላይስ ምን ይላሉ?

አቶ አስመላሽ፡- ይሄን ሁሉ ሰምቼዋለሁ፤አሁን ሕወሃት በተለያዩ ክልሎች ጣልቃ እየገባ የነበረው ጥቅም ለማጋበስ ብሎ ነው የሚባል ነገር አለ። በጣም የሚገርመኝ ነገር ምክንያታዊ የሚባሉ ምሁራን በጣም ውስን ናቸው። ልሂቃን ምክንያታዊ ካልሆኑ ረጋ ብለው አያስቡም። ይሰክራል፤ በስሜት ይነጉዳል። ውጤቱ ግን ሀገር ማጥፋት ነው። ረጋ ብለው ቢያስቡ ግን ብዙ ነገሮች ውሃ የሚቋጠሩ ነገሮች አይደሉም ብዬ ነው የማስበው። ለምሳሌ ያነሣሃቸው የጨውም በለው የሆቴል ወይም ሌላ እንዴት ነው ሲሠራ የነበረው የሚለው ለማጣራት ለምን አንድ ገለልተኛ ኮሚቴ አይቋቋም ። የሕወሃት ሰዎች እኮ 2008 ፣2009 ጀምሮ የሙስና ጉዳዮች እንዴት እንደሚጣሩ ለአቶ ኃይለማርያም የቀረበ ፕሮፖዛል አለ። አሁንእኮ ዝም ብሎ ግፋ በለው ነው ያለው። ለምሳሌ የእኔን ልንገራችሁ፤ ባለፈው አንድ ቅጥረኛ አክቲቪስት ከኢትዮ ፎረም ጋር ቃለ መጠይቅ ስላደረግሁኝ ለሚዲያው ያልኩት ዴሞክራሲ እኛ ሕወሃቶችና ጤነኛ ኢሕአዴጎች የሚገባን፤ ሐሳብ ታነሣለህ ፤ ሐሳቡን ለይተህ ትቀጠቅጠዋለህ። ሰውና ሐሳቡን ለይተህ። አሁን አንድ ነገር ግን በተናገርክ ቁጥር ከዚያም ከዚያም አምጠተህ በውሸት ለመደብደብ የሚደረግ ሙከራ አለ። እውነታ ስለሌለ ነው። ያልከው ለምሳሌ አቶ አስመላሽ በባለቤታቸው በኩል አፋር የጨው ፋብሪካ አላቸው ተባለ። ይሄ እኮ ቀላል ነው፤ ሕዝቡን ለምን አይጠየቅም። አቶ አስመላሽ ጨው እየነገደ ከሆነ በሕጋዊና በሥርዐት ከሆነ መብት ነው። ግን የተባለው ነገር ከሆነ ቀላል እኮ ነው፤ ኢንቨስትመንት ፈቃድ የሌለው ሥራ አለ እንዴ? የንግድ ፈቃድ የሌለው ሥራ አለ አንዴ? ንግድ ፈቃድህ የት አለ? ኢንቨስትመንት ፈቃድህ የት አለ ብሎ መጠየቅ ነው።

ዘመን፡- ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከሆነ የሚነቀፍ ነገር አይደለም። እየተባለ ያለው እኮ……

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ እንጂ …..

ዘመን፡- አይ አይደለም፤ እየተባለ ያለው ለምሳሌ አፋር ላይ ሆቴል እንገነባለን ተብሎ ያለቀረጥ ብረታ ብረት እና ሌሎች ግብዓትን አስገብቶ ለሌላ ጉዳይ መጠቀምና መሰል እንቅስቃሴዎችን ነው…

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ቆይ ልንግርህ … የጨው ፋብሪካ ባለቤት ነው አስመላሽ የሚል ከሆነ ይህ መንግሥት የሰጠው መረጃ ነው የሚሆነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰጠ አደናጋሪ መግለጫ እንደሆነ ይገባኛል። ይህ የሚደረገው አፍ ለመዝጋት ነው! በዚህ የሚዘጋ አፍ የለም! በጥይትም አንዘጋም በዚህ ይቅርና! አልገባቸውም እነዚህ ሰዎች! ይሄ ፍጹም ውሸት ነው። ይሄ የምትለው ነገር ውሸት ነው። ይምጡ እኮ ነው እያልኩህ ያለሁት። ይህ እኮ ግልጽ ነው። ማን ማናቸው በዝርዝር ይምጣ። የዘረፈ የኦሮሞ ባለሥልጣን የለም? የዘረፈ የአማራ ባለሥልጣን የለም? የዘረፈ ባለሥልጣን በተለያየ ክልል የለም? እስቲ አስቡት! ምን እየተሠራ እንደነበር ሕዝቡ ያውቃል። አሁን እየሆነ ያለው እንዴት አድርገን ይሄንን ኃይል እንምታው? እንዴት እናጥላላው? በሐሳብ ግን ፊት ለፊት መጥተው አይሞግቱም። የትኛው ነው ትክክል? የትኛው ነው ትክክል ያልሆነው? አሁን ለምሳሌ አፋር ያለ ጨው በሞኖፖሊ በማን እንደተያዘ ለምን አታጣሩትም? ማጣራት እኮ ይቻላል። ሕጋዊ ከሆነ ችግር የለውም። ግን ምን እየተሠራ እንደሆነ ማለቴ ነው። ሲፈልጉ እኮ እያንዳንዳችን ቢሊየነር ያደርጉናል። ስታየው ግን የለም። የአዲስ አበባን ሕንጻዎች የእነሱ ነው ይላሉ። ቀላል እኮ ነው። እዚህ መዘጋጃ ቤት ይታወቃል፤ ካርታው አለ፤ ማጣራት ይቻላል። የት የት ያሉ ናቸው? ለአንድ ሰው ዐሥር ትላልቅ ሕንጻ ፈልገው ይሰጡታል። በጣም የሚገርም ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ከሙስና ፣ ከህገወጥነት አኳያ ታህሳስና መጋቢት 2010 የገመገምነው እንደዚያ አይልም። በእርግጥ የተገመገሙ ነገሮች አሉ በግልጽ ወጥተው። እነዚህ ሁሉ ወጥተው ተጣርቶ እርምጃ የሚወሰዱበትን መውሰድ ነው። ካልሆነ ግን ሜቴክ 38 ቢሊዮን ጠፍቷል ብሎ ነው የተናገረው መግሥት የሚያፍር መንግሥት እኮ አይደለም፤ እየዋሸ አያፍርም። ይህንን ነው እያየን ያለነው። ከደቂቃ በኋላ ይዋሻል፤ አሁንም ከደቂቃ በኋላ ይዋሻል።… የውሸት ሰንሰለት ነው የተፈጠረው እዚህ ሀገር። ሂትለር ያደርገው የነበረውን የፕሮፓጋንዳ ዘይቤ ነው እየተደረገ ያለው። በጣም አደገኛ የሆነ ነገር ነው።

ዘመን፡- ግለሰብ ዘራፊዎች የትኛውም ብሔር ላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይተወቃል፤ ነገር ግን ሌላውን ትተነው ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች የኤፈርት ድርጅቶች የመጡበት መንገድ፣ እየሄዱበትም ያለው ሂደትን ሀገር የመዝረፍ ያህል እንደሆነ ያነሳሉ፤ የመንግሥት ድርጅቶች ሁሉ ተዳክመው በሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ የሚመሩት የኤፈርት ድርጅቶች ከሌሎች ክልሎች ጥሬ ዕቃ እየወሰዱ ሌሎችን እየጎዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አልተደረጉም?

አቶ አስመላሽ፡- ለምን ስለጥረት አትጠይቀኝም?

ዘመን፡- የካፒታል አቅማቸውና ተጽዕኗቸው አይለያይም?

አቶ አስመላሽ፡- እሺ እንግዲያው ልንገርህ ጥሩ ጥያቄ ነው። ኤፈርት የትግራይ መልሶ ማቋቋም የተመሠረተው በትግል ጊዜ በተሰባሰበ ሀብት ነው። በትግል ጊዜ የተሰበሰበው ሀብት ሲባል ከውስጥም ከውጭም በተለያየ መንገድ ሀብት ነበረው ሕወሃት ። 17 ዓመታት ሲታገል በትንሽ አቅም ይነሳ እንጂ ወደ መጨረሻ ጊዜ እንደ ትልቅ ኃይል የተለያየ አቅም ነበረው። ስለገንዘቡ ትተህ ሚሳኤል የታጠቀ ድርጅት እኮ ነው የነበረው። ከውጭ እኮ በሳተላይት በዘመናዊ ስልክና ፋክስ የሚገናኝ ድርጅት እኮ ነው የነበረው። የተደራጀ አቅም ነበረው። ከዚያ በትግሉ በተሰባሰቡ ገንዘቦች ላይ መጨረሻ ደርግ ሲወገድ የቀረቡት አማራጮች ሁለት ናቸው፤ አንደኛ ለታጋዩ ለጉዳተኞች አንድ መቶ ሺህ ያህል ጉዳተኞች ና ሌሎችም ታጋዮች ነበሩ …

ዘመን፡- እነሱ ግን በደንብ ሲረዱ ቆይተዋል?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ አታቋርጠኝ።… ለእነዚህ ታጋዮች ገንዘቡን ማከፋፈል አንዱ ሐሳብ ነበር፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ገንዘቡ ከሚበታተን በመንግሥትም በግል ባለሀብትም መሟላት ያልቻሉ ሥራዎችን እንዲሞላ ወደዚያ የሚያደርስ አቅም እንዲሄድ የተለያዩ ፋብሪካዎች ብናቋቁም በንግድ ሥራ ብንሰማራ ፣ ምንጭም እየተገኘ እንደገና እየተስፋፉ እንዲሄዱ ለትግራይ ክልል ልማት አጋዥ እንዲሆኑ ብናደርጋቸው ፣ ሲቋቋሙም በኢንቨስትመንትና በሕግ እንዲመሩ ብናደርጋቸው፤ ለምሳሌ ልንገርህ መስፍን ኢንዱስትሪ ሲቋቋም በሼር ካምፓኒ መጀመሪያ የዚያኛው መሥራች ነበርኩኝ እኔም ፤ ሲመሰረት በታጋዮች ስም ነው የተመሠረቱት አቅማቸው በጣም ትንሽ ነበር። በኋላ በታጋዮች ስም በሼር ካምፓኒ የተመዘገቡ ኩባንያዎች ዞሮ ዞሮ ሰው ነንና አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል ተብሎ ሁላችን የነበረን ሼር መልሰን ለዚህ ለተቋቋመ ተቋም ተሰጠ። ይሄ ተቋም የሠራው የልማት ሥራ ነው። ዓላማውን ስናየው ልማቱን ያፈጥናል፤ እርሱ የያዘው ሥራ ሌላ ባለሀብት በሚይዝበት ጊዜ እየለቀቀ ይሄዳል ። ከዚያ በሚገኘው ገቢ ደግሞ እያስፋፋ ሌላ የተለያየ ችግሮች ይፈታል።

ዘመን፡- ሌሎች ባለሀብቶችን ግን አላቀጨጨም?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ! ቆይ! ልንገርህ። ለተለያዩ አካል ጉዳተኞች፣ ለታጋዮች፣ ለሰማእታት ቤተሰብ እርዳታ እያደረገ ነው። የዘንድሮውን እንኳን ብትወስድ ለዚሁ ጉዳይ ለማህበራዊ ስራ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለሰማእታት ቤተሰብ፣ ለታጋዮች፣ ለአካል ጉዳተኞች 8 መቶ ሚሊዮን ገደማ ነው የመደበው። አብረው ለታገሉ አጎራባች ክልሎች በማህበራዊ ጉዳይ እገዛ እያደረገ ነው። አፋር፣ አማራ አካባቢ ያሉ አገው፣ ዋግምራ አብረውን የታገሉ ታጋዮች ናቸው። ይሄ ድርጅት እንደፈለግነው አድጓል ወይ ብትለኝ በእኛ በትግራይ ክልል ያለው ግምገማ እንደተፈለገው አላደገም ነው የምንለው። የተቋሙ ድርጅቶች ከዚህ በላይ መሄድ ነበረባቸው። ነገር ግን ከባንክ ብድር ተበድረው እየመለሱ፣ አትርፈው ለመንግስት በስነ ሥርዓት ግብር እየከፈሉ፣ በውስጥም ሆነ በውጭ ኦዲተር ኦዲት እየተደረጉ፣ በራሳቸው ምክር ቤትና ቦርድ እየተገመገሙ፣ ባለፈው አመት ደግሞ ተጠሪነታቸው ለትግራይ ምክርቤት እንዲሆኑ መደረጉ እና በጀታቸው እቅዳቸው በምክር ቤቱ እንዲታይ እየተደረገ ነው። ስለዚህ እነዚህ ተቋማት የዘረፉት ነገር የለም። በህግና በህግ ነው የሄዱት። እንደገናም በትጥቅ ጊዜ ያሰባሰብነው ገንዘብ ብቻችንን ትግራይ ብቻ እንዲለማ አልወሰንም። ለጥረት ማቋቋሚያ ገንዘብ ሰጥተናል፣ ኦሮሚያ ለነበረው ተመሳሳይ ድርጅት መቋቋሚያ ገንዘብ ተሰጥቷል። ደቡብ ለነበረ ድርጅት መቋቋሚያ ተሰጥቷል። ለሁሉም ነው ያከፋፈልነው። እነሱም የሚመሰክሩት ነገር ነው።

ዘመን፡- ከላይ ያነሷቸው እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቀ ሆኖ ከኤፈርት ድርጅቶች ውስጥ የሚታወቁ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው ያልመለሱ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ኦዲት ሳይደረጉ የቆዩ የሉም?

አቶ አስመላሽ፡- ተበድረው ያልመለሱ እየመለሱ ይሄዳሉ። የሚከፈለውም በጊዜው ነው። ኦዲትም ሁል ጊዜ ይደረጋሉ። በየጊዜውም እየተደረጉ ነው። አሁን የፌዴራል መንግስት የሚያነሳቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ዝምድና ያላቸው ተቋማት በኦዲት ምክንያት ብዙ እንግልት በማድረግ በጉቦ እየተስፈራሩ እየተንገላቱ እያየን ነው። ይሄ አገርን ለማፍረስ እንጂ አገርን ለማቅናት አይደለም። ለዚህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ የሚንበረከክ ህዝብ የለም። ለአንድ ቀንም አንበረከክም። ባለሀብቶችን ቀጭቷል ላልከው ግን ትግራይ ኢንቨስትመንት በመፈለግ ላይ ያለ ክልል ነው። ባለሀብቱ ኢንቨስት አላደረገም። ብዙ ጊዜ እየሰበሰብን በትግራይ ኢንቨስት አድርጉ እያልን ነው ያለነው። የትኛው ኢንቬስተር ነው ትግራይ መጥቶ ኢንቨስት እንዳያደርግ የተከለከለው!

ዘመን፡- በዚህ ረገድ ትግራይ ክልል ከሌሎች ክልሎች አንፃር ሲታይ ተጠቃሚ አይደለም ? በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ትግራይ ክልል በኢፈርት በኩል የሚያደርገው ተሳትፎ ከልኩ አያልፍም? ሌሎቹ ላይ ጫና አላደረገም ወይ?

አቶ አስመላሽ፡- ከልኩ አላለፈም። ጫና አላደረገም። ተገቢ ስራ ነው እየሰራ ያለው። ጥረትን ለምን እንደዚህ አታዩትም። በአማራ ክልል ጥረት ብዙ ነገር እየሰራ አይደለም እንዴ?

ዘመን፡- አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ተቋማት አሉ። ሌሎች መሰል ተቋማት በኢፈርት ደረጃ ተሳትፎ ነበራቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ አስመላሽ፡- ቆይ ልንገርህ። በትግል ጊዜ የነበሩ መነሻ ሀብቶች አራቱ ክልሎች ተከፋፍለው እንዴት እነደተሰራ ነግሬሀለሁ። በሌሎች ክልሎች በዛ መልክ አድርገናል አልልህም። ለምን እንዋሻለን፤ አላደረግንም እንደዛ። በልማት በኩል ብትመጣ ግን እንደኤፈርትና እንደ ጥረት የመሳሰሉ ተቋማት ከሌሉ አትለማም የሚባል ነገር አይደለም። ይሄ በነበረው ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ የተገኘ መነሻ ካፒታል ነው። በዋናነት እያንዳንዱ ክልል የመልማት እድል ተሰጥቶታል። ይሄ እኩል የመልማት እድል ተጠቅሞ ሲሄድ ደግሞ ተመጣጣኝ ያልሆኑ እድገቶች ወደፊትም ይኖራሉ። እኩል የሆነ እድገት በማንኛውም ክልል ይኖራል የሚል ቅዠት የለንም። አንዋሽም አናጭበረብርም። አሁን እኮ በእያንዳንዱ ክልል አሽከር ነበርኩኝ እንደዚህ ነበርኩኝ ብሎ እየቀባጠሩ ያሉት ተሹሞ ከራሱ ፍላጎት አንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ትሆናለህ፣ አንዱን እንትን ትሆናለህ እየተባሉ የሌለ ነገር እየተዋሸ ሲነገረው ይሄ ነገር አገኛለሁ ብሎ ስለሚሄድ ነው አሁን እየሆነ ያለው። እኛ እንደዚህ አንዋሽም።

ምንጭ፦ ዘመን መጸሄት ታህሳስ 2012 ቁጥር 85