" /> የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኞች በአሶሳ በቁጥጥር ሥር ዋሉ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኞች በአሶሳ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

BBC Amharic : ሁለት የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኞች ለሥራ ባቀኑበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለእስር መዳረጋቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።

ለእስር የተዳረጉት የአማርኛ ክፍል ባልደረቦች ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና የካሜራ ባለሙያው በኃይሉ ውቤ መሆናቸውን ኤጀንሲው ገልጿል።

ኤጀንሲው በአሶሳ ከተማ በሚካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ላይ ሽፋን እንዲሰጥ በቀረበለት ጥሪ መሠረት ሁለቱ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው መላካቸውን የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ በቀለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጋዜጠኞቹ ቅዳሜ ዕለት ነው የሄዱት፤ እሁድና ትናንት ሲዘግቡ ውለው፤ ትናንት ጥር 4/2012 ዓ.ም ምሽት 3፡00 አካባቢ ካረፉበት ሆቴል ፖሊሶች መጥተው ወሰዷቸው” ሲሉ የተያዙበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባየታ በአሶሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በኩል የተያዙ ጋዜጠኞች መኖራቸውን አረጋግጠው፤ የተያዙበትን ዝርዝር ምክንያት ግን እንደማያውቁ ገልጸዋል።

የአሶሳ ከተማ አስተዳዳር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እስማኤል አስፒክ በበኩላቸው “ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደብዳቤ ይዘው ስላልተገኙ ነው” ብለዋል።

ዋና ኢንስፔክተር እስማኤል፤ ሁለቱ ጋዜጠኞች የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትን ለመዘገብ ከኤጀንሲው አዲስ አበባ ቅርንጫፍ መላካቸውን እንደነገሯቸው ጠቅሰው፤ ጋዜጠኞቹ ወደ አሶሳ ሲመጡ ደብዳቤ ባለመያዛቸው እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለ ሁለቱ ጋዜጠኞች ወደ ክልሉ መምጣት የሚያውቀው ነገር ባለመኖሩ መታሰራቸውን ይናገራሉ።

ጋዜጠኞቹ መጡበት ወደተባለው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢደውሉም ገና ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ ስለ ጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና ወደ ከተማው ፖሊስ በተደጋጋሚ ቢደውሉም ማብራሪያ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ጉዳዩንም ለክልሉ መንግሥት እንዳሳወቁና የክልሉ መንግሥት እየተከታተለው መሆኑን አክለዋል።

ጋዜጠኞች በመሆናቸው ያለ ደብዳቤ በመታወቂያ መሥራትና በነፃነት መንቀሳቀስ አይችሉም ወይ? ያልናቸው ኢንስፔክተሩ፤ “አሠራሩ እንደዚያ ነው፤ አንድ የመንግሥት ሰራተኛ ወይም ለአንድ ሥራ ወደ አንድ ቦታ የተንቀሳቀሰ ሰው ‘ለሥራ ጉዳይ ነው የመጣው’ የሚል ደብዳቤ መያዝ አለበት ነው የሚለው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በጉዳዩ ላይ ከመገናኛ ብዙኃኑ ጋር ያደረጉት የመረጃ ልውውጥ ስለመኖሩ የተጠየቁት ዋና ኢንስቴክተሩ፤ ፖሊስ ኮሚሽን ከትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ ካለው ቅርንጫፍ ጋር በጉዳዩ ላይ በስልክ እየተነጋገረ መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።


የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US