በኦሮሚያ ክልል የሁለት ወር ህፃን ከሞት አስነሳለሁ በማለት መቃብር ያስቆፈረችው ‘ፓስተር’ በማጭበርበር ተቀጣች


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

BBC Amharic : በኦሮሚያ ክልል ቦሰት ወረዳ ወለንጪቲ ከተማ ከሞተ ሁለት ሳምንት የሆነውን የሁለት ወር ህፃን “ከሞት እንዳስነሳ ራዕይ ታይቶኛል” በማለት መቃብር ያስቆፈረችው ‘ፓስተር’ በማጭበርበር መቀጣቷን ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።

ህጻኑ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሞተ በኋላ ራዕይ ታይቶኛል ያለችው ሴት፤ የህጻኑን እናት እና አንዲት ሌላ ሴት በመያዝ ወደ መቃብር ሥፍራ በመሄድ ቆፍረው ማውጣታቸውን የቦሰት ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ ደምሴ ገልጸዋል።

”ግለሰቧ እንደ ለቅሶ ደራሽ በመሆን ወደ እናት ቤት በመሄድ ልጅሽ አልሞተም፤ በሕይወት ነው ያለው፤ ከሞት እንዳስነሳውም ራዕይ ታይቶኛል” ትላታለች። መቃብር ሥፍራም ሄዳ ጸሎት ማድረግ እንደምትፈልግ ትነግራታለች። እናትም እውነት መስሏት ተያይዘው ወደ መቃብር ሥፍራው ሄደዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ እንዳሉት መቃብር ሥፍራ ከደረሱ በኋላ ህጻኑን ቆፍራ አውጥታ እዛው ስትቀመጥ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተመልክተው ለፖሊስ ጥቆማ አደረሱ። ከዚያም ፖሊስ በቦታው ደርሶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ህብረተሰቡን አስተባብረው አስክሬኑ እንዲቀበር አድርገዋል።

ፖሊስ ጉዳዩን ሲከታተለው ቆይቶ ግለሰቧ ለፈጸመችው ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርባ ተገቢውን ቅጣት እንዳገኘች ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ ደምሴ ነግረውናል። በብይኑ መሰረትም ጥፋተኛ መሆኗ ስለተረጋገጠ በ2000 ብር ተቀጥታለች።

‘ፓስተሯ’ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላት ኃላፊነት ምን ነበር? ያልናቸው ኢንስፔክተሩ፤ ” ከታሪኳ እንደምንረዳው አማኝ ነች እንጂ፤ አገልጋይም ወይም ሌላ ነገርም አይደለችም” ብለዋል።

ከተቀበረ ሁለት ሳምንታት የሞላውን ህጻን ፈጣሪ ራዕይ አሳይቶኛል በማለት አስክሬኑ ተቆፍሮ እንዲወጣ መደረጉ የአካባቢውን ነዋሪ በጣም ያስቆጣና የተከበረውን የመቃብር ቦታ ክብር የሚነካ እንደሆነ ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ ገልጸዋል።

ፍርድ ካገኘችው ‘ፓስተር’ በተጨማሪ እናት እና ‘ፓስተሯን’ ይዛት የመጣች አንዲት ሌላ ሴት በወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን ሁለቱ ጥፋተኛ አለመሆናቸው ስለተረጋገጠ በነጻ ተሰናብተዋል።

እናትም ለፖሊስ በሰጠችው ቃል “‘ፓስተሯ’ ልክ እንደ ማንኛውም ለቅሶ የሚደርስ ሰው ወደ ቤት ከመጣች በኋላ ‘ራዕይ ታይቶኛል፤ ልጅሽን አስነሳለሁ’ ብላ በመጀመሪያ ቤት ውስጥ ጸሎት ካደረገች በኋላ ወደ መቃብር ሥፍራው ሄደን አስክሬኑን አወጣነው። ያው የእናት አንጀት ሆኖብኝ አመንኳት” ብላለች።

‘ራዕይ ታይቶኛል’ ያለችውን ‘ፓስተር’ ወደ ቤት ይዛት የመጣችው ሌላኛዋ ሴት ከልጁ አባት ጋር በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው እንደሚሰሩም ዋና ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል።

አስክሬኑ ተቆፍሮ በወጣበት ወቅት “እንዴት አንድ ጤናማ ሰው ከተቀበረ ሁለት ሳምንት የሆነውን አስክሬን አውጥቶ፤ ይዞ ይቀመጣል?” በሚል የአካባቢው ነዋሪ በመረበሹ ግርግር ተፈጥሮም እንደነበረ ዋና ኢንስፔክተሩ አክለዋል።