ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የተሰማሩ ፖሊሶች ተገደሉ

በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ አዱላላ ቦኩ በሚባል ቀበሌ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪን ለመያዝ የተሰማሩ ሁለት የዞኑ የፖሊስ አባላት መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ “ፖሊሶች ወደ ቀበሌው ሄደው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲሉ ‘ለምን ይያዛሉ?’ በሚል ረብሻ ተነስቶ የአከባቢው ሰዎች በፖሊስ አባሎቻችን ላይ ጉዳት አደረሱ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች የተቃጣው ጥቃት የሁለት የፖሊስ አባላቶችን ህይወት ከመቅጠፉም በላይ አንድ ሲቪል ህይወቱ ያለፈ ሲሆን በሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ደግሞ ጉዳት ማድረሱን ኮማንደር ሽፈራው ተናግረዋል።

ረቡዕ ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ላይ በተፈጠረው ክስተት ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ የፖሊስ አባላት ሆስፒታል ተኝተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።

የተፈጠረው ምን ነበር?

ረቡዕ ጠዋት የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አባላት ሃሰተኛ መስክርነት በመስጠት የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ወደ አዱላላ ቦኩ ቀበሌ ያመራሉ።

“ከዚህ በፊት ሶስቱ ግለሰቦቹ ‘ሰው ገድሏል’ በማለት በሃሰት መሰከሩ። የክስ መዝገቡ ምረመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በድጋሚ ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። የሰጡት ምስክርነት የሃሰት መሆኑ ሲታወቅ ፍርድ ቤት ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ። የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም ፖሊሶች ወደ ስፍራው ከተሰማሩ በኋላ ነው ይህ የሆነው” በማለት የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ያስረዳሉ።

ፖሊሶቹ ወደ ስፍራው ካቀኑ በኋላ ሶስቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋ ሲጥሩ ከአከባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ እንደደረሰባቸው እና በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ያስረዳሉ።

ፖሊሶቹ በወቅቱ የጦር መሳሪያ ታጥቀው እንዳሉ ይህ አሰቃቂ ጥቃት እንድተሰነዘረባቸው የፖሊስ አዛዡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የወጣንበት የራሳችን ማህብረሰብ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ተግባር በመፈጸሙ በጣም ነው ያሳዘነን” ያሉት ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ፤ በፖሊስ ባልደረቦቹ ላይ ለተፈጸመው ወንጀል እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ እንደሌለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ወንጀሉ የተፈጸመበት አካባቢ ሰላም መሆኑን እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ ምረመራ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።