የተጠናከሩ ተቋማት ባሌሉበት የመደመር ሐሳብን መተግበር አይቻልም ተባለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የመደመር እሳቤ ውጤታማ እንዲሆን ተቋማዊ መሰረቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

(ኤፍ ቢ ሲ) ከሀገሪቱ ተጨባጭ ችግሮች ተነስቶ ሀገር በቀል የመፍትሄ አማራጮችን ያቀረበው የመደመር እሳቤ ውጤታማ እንዲሆን ተቋማዊ መሰረቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን እንዳሉት፥ እሴቱ ሀገራዊ አንድነትን ማስቀደሙና ለዜጎች ክብርና ብልጽግና ትኩረት መስጠቱ የተሻለ ያደርገዋል።

ሆኖም በፍላጎትና አቅም መካከል ያለውን ልዩነት ለማስታረቅ መፍትሄ አለማስቀመጡ የእሳቤው ክፍተት መሆኑንም ያነሳሉ።

የምጣኔ ሀብትና የፕሮጀክት አስተዳደር ባለሙያው አቶ ሁሴን አሊ ከቀደሙት ርዕዮተ አለሞች አንጻር ይህ እሳቤ ለእኩልነትና ነጻነት መታረቅ ቅድሚያ ይሰጣል ይላሉ።

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ውብሸት ታደለ ደግሞ የመደመር እሳቤ ከተጨባጭ ችግር የመነጨ በመሆኑ፥ ከብቸኝነት ጉድለት ወደ ተግባራዊነት ለሚለው ሀሳባዊ መዳረሻ የተጨባጭነትነት ሚናው የላቀ ይሆናል ባይ ናቸው።

የመደመር እሴቱ ሀገራዊ አንድነትን በማስቀደም ለዜጎች ክብርና ብልጽግና ቦታ ይሰጣል የሚሉት አቶ ሁሴን፥ ጸሀፊው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ የለያቸው ችግሮች ገለልተኝነት የታየበት መሆኑንም አንስተዋል።

ምክንያቱም ኢህአዴግ ላለፉት 28 አመታት መስመሩ ከሆነው ርዕዮተ አለም አንጻር፥ ችግሮቹን ያሳየና መሻገሪያ መፍትሄውን የተመለከተበት መሆኑንም ያስረዳሉ።

የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች የፈጠሯቸውን ጫናዎች የሚዳስሰው እሳቤው በተለይ የገበያ ጉድለትን ለመሙላት በመንግስት ሊወሰድ ስለሚገቡ አማራጮች ያስቀመጣቸው መፍትሄዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ውብሸት ታደለ ናቸው።

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ የመደመር ኢኮኖሚያዊ ምልከታዎቹ ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ ጥራቱን ማስጠበቅ ከተቻለ ጥሩ መሸጋገሪያ ይሆናል ነው የሚሉት።

እውቀት መር እሳቤ ስለመሆኑ የሚያስረዱት ምሁሩ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር መፍጠን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ባይ ናቸው።

ምሁራኑ የመደመር እሳቤ አሁን በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል የመፍትሄ አማራጮችን የያዘ ቢሆንም፥ ውጤት እንዲያመጣ ግን ተቋማዊ የአሰራር ስልቶች እንዲጠናከሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።