በወጣቱ ዘንድ የተዘነጋው ኤችአይቪ በወረርሽኝ መልክ ተከስቷል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኢትዮጵያ ከሦስት ክልሎች ውጪ ኤችአይቪ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፌደራል ኤች አይቪ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ ገለፀ።

BBC Amharic : ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ቤንሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በኤችአይቪ ወረርሽኝ ውስጥ መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ዳይሮክተሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዳንኤል በትረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቫይረሱ በወረርሽኝ ደረጃ የማይገኝባቸው የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሕግ መሰረት ይላሉ አቶ ዳንኤል፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከአንድ በመቶ በላይ በበሽታው ከተያዘ እንደ ወረርሽኝ እንደሚቆጠር በመግለጽ እነዚህ ክልሎች ወረርሽኝ ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ዳንኤል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የስርጭት መጠን ሲታይ ወረርሽኝ ላይ ነው ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

በወጣቱ ዘንድ የተዘነጋው ኤችአይቪ

የፌደራል ኤች አይቪ መከላከልና መቆጠጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት አክሎም በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚታይ አስታውቋል።

በየዓመቱ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ይያዛሉ ያለው ጽህፈት ቤቱ፤ ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች እየሞቱ መሆናቸውን ገልጿል።

ይህ ቁጥር ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይህ ግን እንደ ሀገር “መዘናጋትና ቸልተኝነትን ፈጥሯል” በዚህ ምክንያት ኤችአይቪ እስከመኖሩም የረሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ጨምረው ይናገራሉ።

ይህም በተለይ ወጣቶች ላይ በይበልጥ እንደሚስተዋል ተናግረው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ፣ በልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች፣ በአበባ ልማት ላይ፣ በስኳር ፋብሪካ የአገዳ ቆረጣ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች መዘናጋቱ በስፋት ከሚታይባቸው ሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

መንግሥት ይህንን በማስተዋል ቀደም ሲል ለውጥ ካመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ አደረጃጀቶች፣ የመገናኛ ብዙኀንና ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአገር አቀፍ ኤድስ ምክር ቤት ጉባዔ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን በማንሳትም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በድጋሚ ማስጀመራቸውን ይናገራሉ።

ይህንን ተከትሎም በክልሎች ምክር ቤቱ እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኤች አይ ቪ ስርጭት በአገር አቀፍ ደረጃ

ኤች አይ ቪ በአገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱን አቶ ዳንኤል በተር ያስረዳሉ። ይህንንም በቁጥር ሲያስቀምጡ 0.91 አካባቢ ነው በማለት “በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ ደረጃ ነው” እንደማይባል ተናግረዋል።

የኤች አይቪ ስርጭት በክልል ደረጃ ሲታይ ግን ከአገር አቀፉ የስርጭት መጠን ከፍ ያለ የተመዘገበባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ይጠቅሳሉ።

የጋምቤላ ክልል 4.8 በመቶ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 3.4፣ የትግራይና የአማራ ክልል በበኩላቸው 1.2 የስርጭት ምጣኔ እንዳላቸው በመጥቀስ ኤች አይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

እንዲሁም የድሬዳዋ፣ የሐረር፣ የአፋርና የቤንሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች ኤች አይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።

ዝቅተኛ የስርጭት ምጣኔ ያለባቸው ክልሎች ደግሞ ሶማሌ (0.01) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (0.04) መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደ አገር በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለው የስርጭት ምጣኔም እንደሚለያይ በማንሳት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር አንደሚይዙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም 23 በመቶ መሆኑን በማንሳት፤ ባሎቻቸውን በሞት ካጡ ሴቶች መካከልም ያለው የስርጭት ምጣኔ 19 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል።

በረጅም ርቀት አሽከርካሪዎችና በታራሚዎች በኩል ያለው የስርጭት ምጣኔ በአንጻራዊነት ከአገራዊው አሃዝ ከፍ ብሎ እንደሚታይ አቶ ዳንኤል ጨምረው አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ወሲብ የመጀመሪያ እድሜው ዝቅ ማለቱ ይታያል

አቶ ታሪኩ ሞላ በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የክትትልና ግምገማ ባለሙያ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት በአዲስ አበባ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት በአገር አቀፍ ከተጠናውና ከተገኘው ውጤት ጋር የተዛመደ ነው።

በአገር አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ስርጭት በከተሞች ከፍ እንደሚል በገጠሩ አካባቢ ደግሞ አነስተኛ መሆኑን ጥናቱ እንደሚያሳይ አስታውሰው፤ ከጋምቤላ ክልል በመቀጠል አዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ስርጭት ከፍ ያለበት መሆኑን ይናገራሉ።

ጽህፈት ቤታቸው በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ስርጭት ሁኔታና በከተማዋ ኤች አይ ቪ እንዲስፋፉ ያደረጉ ምክንያቶች ላይ ጥናት ማድረጉንም ይጠቅሳሉ።

ይህ ጥናት በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ለኤች አይ ቪ መስፋፋት ይበልጥ ምቹ ሁኔታ ያለባቸው አካባቢዎችን የለየ ሲሆን እነዚህም ቡና ቤቶች በስፋት የሚገኙባች፣ ግሮሰሪዎች፣ ፔኒሲዮኖች፣ የእንግዳ ማረፊያ በሚል የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ሺሻ ቤቶች፣ የውጪ ቱሪስቶች የሚያዘወትሩባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን ባለሙያው ይናገራሉ።

እነዚህ ስፍራዎች በአስሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችንና ሰፈሮች ጭምር መለየታቸውን የሚጠቅሱት አቶ ታሪኩ የመከላከል ሥራውም እነዚህ ላይ ያተኮረ ይሆናል ይላሉ።

ምንም እንኳ እነዚህ ተቋማት በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቢሆኑም በብዛት ተስፋፍተው የሚገኙባቸው ግን አራዳ፣ አዲስ ከተማ፣ ቦሌና ቂርቆስ ናቸው።

ለቫይረሱ መስፋፋት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ባህሪያትን በማንሳትም በከተማዋ ጥንቃቄ የጎደለው የወሲብ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን በጥናቱ ውስጥ መታየቱን ይናገራሉ።

ይህም ከትዳር ውጪ እንዲሁም በወሲብ ንግድ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀምን ያካትታል ይላሉ።

ኮንዶም አጠቃቀም ላይም በተደረገው ጥናትም፤ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኮንዶምን በአግባቡና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ መጠቀም ላይ ያላቸው ልምድ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቱ እንደሚያሳይ ባለሙያው ገልፀዋል።

አደንዛዥ ዕፅና አደገኛ ዕጾችን የመጠቀም ሁኔታ በከተማዋ በስፋት ይታያል የሚሉት አቶ ታሪኩ፤ በአዲስ አበባ ወሲብ የሚጀመርበት እድሜ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

ቀደም ባሉ ጊዜያት ወሲብ የሚጀመረው በአማካይ በ17 እና 18 እድሜ ላይ አንደነበር በማንሳት፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በአስራዎቹ መጀመሪያ ግፋ ሲልም ከአስር ዓመት በታችም ወሲብ ሲጀምሩ ይታያል ብለዋል።

ይህም ታዳጊና ወጣት ልጃገረዶች ለኤች አይ ቪ ያላቸውን ተጋላጭነት እንደሚያባብስ ይታመናል ይላሉ። አልፎ አልፎም ድንግልናን የመሸጥ ሁኔታ በከተማዋ እንደሚታይ ገልፀዋል።

በከተማዋ ካለው የወሲብ እንቅስቀሴ አንጻር ለትዳር አጋር ታማኝ የመሆን ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ያደረገው ጥናት እንደሚያሳይ ይናገራሉ።

ወጣቶች የወሲብ ጓደኞቻቸውን የመቀያየርም ሆነ የመቀያየር (መለዋወጥ) ባህሪያቶች ተስተውሎባቸዋል በማለት፤ ሰፊ ግንዛቤ በኤች አይ ቪ ላይ ተፈጥሯል ተብሎ በሚታመንበት በዚህ ወቅት አሁንም ለኤች አይ ቪ የተሳሳቱ እምነቶችና አመለካከቶች በስፋት መኖራቸውን በጥናቱ ማግኘታቸውን ይገልፃሉ።

ለኤች አይ ቪ ይበልጥ በከተማዋ ከተጋለጡት መካከልም በግንባር ቀደምትነት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችና ደንበኞቻቸው፣ የተፋቱና የትዳር አጋሮቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች፣ ወሲብን ለገንዘብና በገንዘብ የሚጠቀሙ ሰዎች፣ የቀን ወይም ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች፣ ረዥም ርቀት ተጓዥ መኪና አሽከርካሪዎች፣ አደገኛና አነቃቂ መድሃኒት ተጠቃሚዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችና ሌሎችም ከማህበረሰብ አንጻር በተለየ ሁኔታ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቷል ብለዋል።

አማራ ክልል

በአማራ ክልል አዲስ በኤች አይ ቪ የሚያዙ ሰዎችም ሆነ በዚህ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ምላሽ ማስፋት እና ማጠናከር የማህበረሰብ ንቅናቄ አስተባባሪ የሆኑት አቶ በቃሉ ዳኜ በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የክልሉ የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት ጉራማይሌ ነው የሚሉት አስተባባሪው “በአጠቃላይ ህረተሰበቡ ዘንድ ያለው ስርጭት 1.2% ወይንም ከአንድ ሺህ ውስጥ 12ቱ ሰዎች ቫይረሱ ደማቸው ይኖራል ተብሎ ይታሰባል” ብለዋል።

በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ ነው በማለትም ከአንድ ሺህ ሰዎች እስከ 41 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይኖራል ተብሎ ይታሰባል ሲሉ ያብራራሉ።

“የአማራ ክልል የኤች አይቪ ስርጭት ሁኔታ ከአገሪቱ የስርጭት ሁኔታ አንጻር ከ30 በመቶ በላይ ድርሻ ሲሆን አዲስ ከሚያዙት ደግሞ የ29 በመቶውን ድርሻ ይወስዳል። ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ ከሚሞቱት ደግሞ 32 በመቶ ደርሻ አለው” ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ 66 ከተሞች ከፍተኛ ስርጭት አለባቸው ተብለው የተለዩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ስድስት የሚሆኑት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል አቶ ዳኜ።

ስለኤች አይቪ/ኤድስ ያለው እውቀት ማነስ፣ አድሎ እና ማግለል፣ መከላከል ላይ የሚደረገው ሥራ መቀዛቅ እና የአመራር ቁርጠኝነት መቀነስ “ተመልሶ እንዳያገረሽ ዋስትና የሚሰጥ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ 178 ሺህ ሰዎች (0.67 በመቶ) ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ለቢቢሲ የተናገሩት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል የስርጭት መጠኑ ከገጠር ይልቅ በከተማ እንደሚሰፋ ገልፀው፤ ይህም በከተሞች ያለውን የስርጭት ምጣኔ 3 በመቶ እንደሚያደርሰው በማንሳት ቁጥሩ ቀላል የሚባል አለመሆኑን ያስረዳሉ።

በኦሮሚያ ከተሞች የሚገኙ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች፣ ሺሻና መጠጥ ቤት የሚሰሩ ሴቶች፣ የረዥም ርቀት መኪና አሽከርካሪዎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

በክልሉ እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ያሉ ወጣቶች ለኤች ኤይ ቪ ተጋላጭነታቸው በስፋት ይታያል ያሉት አቶ ነጋሽ፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ጥናት በኦሮሚያ የሚገኙ 76 ከተሞች የኤች አይ ቪ ስርጭት በብዛት የሚታይባቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከእነዚህ 76 ከተሞች መካከልም በቀዳሚነት አዳማ፣ ሞጆ፣ አሰላ፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምቴ፣ ጂማ፣ ባሌ ጎባ እና ሻኪሶ ይገኙባቸዋል ብለዋል።

ፌስቡክን ኤች አይቪ ለመከላከል

የፌደራል ኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዳንኤል በአገር አቀፍ ደረጃ ስርጭቱን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራ ከፍ ሊል የሚችልበት እድል መኖሩን ይናገራሉ።

“መዘናጋቱን መቀልበስ ካልተቻለ እንደ አገር ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል” በማለትም ይህ ደግሞ ከሚያሳድረው የሥነ ልቦና፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ተጽዕኖም አለው ብለዋል።

አቶ ዳንኤል ባለፈው ዓመት እንኳ ቢታይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት ምጣኔው 1.18 ነበር ብለው ከዓመት ወዲህ በተሰራው ሥራ መቀነስ መታየቱን በማንሳት “እንደ አገር ስጋቱን የመቀልበስ አቅም ላይ ነው ያለነው” ይላሉ።

በመላ አገሪቱ ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ለመስራት ዘመኑ የሚጠይቀውን የተግባቦት ዘዴ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ለዚህም ጽህፈት ቤታቸው ማህበራዊ መገናኛ ብዙኀንን ለመጠቀም ማቀዱን ይናገራሉ።

ሬዲዮ፣ ጋዜጣና ቴሌቪዥን ዳግም የመጠቀም ፍላጎት መኖሩን አንስተው፣ ነገር ግን ወጣቶችን ለማግኘት የሚረዱ የመገናኛ ብዙኀን አይነቶችን ቅድሚያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ኤች አይ ቪ በደማቸው ያያለ ግለሰቦች፣ ማህበራት፣ ጥምረቶች አሁንም መኖራቸውን በማንሳትም ከእነርሱ ጋር የሚሰሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል።