ዩኒቨርሲቲዎች ወይስ “መንደርሲቲዎች”


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ዩኒቨርሲቲዎች ወይስ “መንደርሲቲዎች”
አዲስ ዘመን
ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በውጭ አገር ሰዎች ጭምር ይመሩ ነበር። በኋላ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ለመሆን ዋነኛው መስፈርት የአካባቢው ተወላጅ መሆን ሆነ።

ብዙዎች የተሻለ ሰው ሳይታጣ የአካባቢው ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ አዲስ ሹፌር ሆነው አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን የመሾፈሩ ዕድል ገጠማቸው።

ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል መንግስት ስር ናቸው። ይሁን እንጂ በተለይ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ሲመሰረቱ ግልጽ ማስታወቂያዎች ወጥተው ብቁ መምህራንን ለመቅጠር የተፈለገ አይመስልም።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በተከፈቱበት አካባቢ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የኮሌጅ መምህራንን ወስደው ስራ ጀመሩ። እርግጥ ነው እነዚህ መምህራን በሂደት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ እንዲማሩ ተደርጓል።

ዕድል “ቀንቷቸው” ወደእነዚህ ዩኒቨርሲ ቲዎች የተላኩ ተማሪዎች ብዙ ነገሮች ባልተሟሉባቸው ግቢዎች ውስጥ ጎዶሎ ቀናትን አሳልፈው ሙሉ ሆናችኋል ተብለው ተመርቀው ወጥተዋል።

እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ቀርቶ ሌክቸረር ለመሆን ሰቃይ ተማሪነት ብቻውን በቂ አይደለም። የአካባቢው ተወላጅ መሆን ግድ ይላል። አራት ነጥብ ዘግቶ በአንደኝነት ያጠናቀቀ ተማሪ እያለ ፣ ሶስት ነጥብ ሰባት አምጥቶ ሶስተኛ ደረጃን ያገኘ ተማሪ ሌክቸረር ሆኖ ይቀጠራል።

አንዳንድ መምህራን ደግሞ የአካባቢያቸው ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎችን ለይተው የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣሉ። ለመንደራቸው ተማሪዎች ያልደከሙበትን ውጤት የሚያሸክሙ መንደርተኛ መምህራንም አሉ። የለየላቸው ጥቂቶች ደግሞ ያለሀፍረት በአደባባይ ወገንተኝነታቸውን ያሳያሉ።

ይህን ስል እንግሊዝኛን በአማርኛ የሚያስተምሩን የዩኒቨርሲቲያችን መምህር ትዝ አሉኝ። እኒህ መምህራችን ክፍል በገቡ ቁጥር “የሸዋ ሰው አልወድም” እያሉ ከአዲስ አበባ የሄድነውን ተማሪዎች ያሳቅቁን ነበር። በበኩሌ ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል መስፈርቶችን የሚያሟሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መንደርሲቲዎች ብያቸዋለሁ።

የመንደርሲቲ ምሁራን ሚዲያዎች ላይ ቀርበው የሚሰጧቸው ትንታኔዎች ሚዛናዊነትን፣ ጠያቂነትን፣ መርማሪነትን ፣ ታሪክን መፈተሽንና አመክንዮን ገንዘቡ ካደረገ ምሁር የሚመነጩ ዓለማቀፋዊ ሳይሆኑ መንደርን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። እያንዳንዱ አካባቢ የኔ የሚለው የብቻው ምሁር አለው።

ዛሬ የመንደርተኝነት ስሜት በፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ቅጥ ያጣ ቅስቀሳ ይበልጥ ጦዟል። በጥፋት ኃይሎች ረብጣ ዶላር በሚቀርብ ማገዶ በሚገባ በስሏል። ተማሪዎች በክልላችን በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ካልተማርን ብለው ሰልፍ እስከመውጣት ደርሰዋል።

ወደተመደቡበት የትምህርት ተቋም ሲሄዱም ክፍል ውስጥ ለመሳተፍ ጭምት የሆኑ ተማሪዎች ሳይቀሩ በየጊዜው በሚነሱ ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ባደረጉ ግጭቶች ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ይሆናሉ። የክልል መንግስታትም ባለፉት ዓመታት ግጭት በተከሰተ ቁጥር ተማሪዎቻቸውን ከያሉበት ጠርተው በራሳቸው ክልል እንዲማሩ ለማድረግ ላይ ታች ሲሉ ተመልክተናል።

አገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴርም ለችግሩ መባባስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የክልል ትምህርት ቢሮዎች ለሚያቀርቡት “ተማሪዎቼ በክልሌ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይመደቡልኝ” ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ መደራደርን መርጠዋል። በቅርቡ የአንድ ክልል ዩኒቨርሲቲ በሌላ ክልል የተመደቡ ከሁለት ሺ በላይ ተማሪዎቼ ቁጥር ይቀነስልኝ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ወደ 600 ዝቅ እንዲልለት ተደርጓል።

አገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ከሚፈጽሙት ያልተገባ ተግባር በተጨማሪ ተማሪዎችን የሚመደቡበት መንገድ ችግር ያለው ይመስላል። በአንድ ክልል ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የሚመደቡት ተማሪዎች አርባ በመቶ በክልሉ ኗሪ ሲሆኑ፤ ስልሳ በመቶዎቹ ደግሞ ከሌሎች ክልሎች የተወጣጡ ናቸው። መመደቢያ መንገዱ በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በክልሉ ኗሪ የሆኑ ተማሪዎች ከፍተኛ ቁጥር እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ ማለት ከ10 ሺ ተማሪዎች አራት ሺ ያህሉ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት ክልል ተማሪዎች ይሆናሉ ማለት ነው። በሌላ አባባል የተቀሩት የአገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአማካኝ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ 600 ተማሪዎች ብቻ ይኖሯቸዋል።

በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ተማሪዎች በተመጣጠነ መልኩ እንዲመደቡ ቢደረግ የአንድ ወገን የበላይነት አይኖርም። ዩኒቨርሲቲዎችም በይበልጥ ሕብረ ብሔራዊነት ይንጸባረቅባቸዋል።

የትምህርት ፖሊሲውም መንደርተኝነት እንዲያብብ በማድረግ ረገድ የራሱን ሚና ተጫውቷል። ስራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ተማሪዎች በሥነ-ምግባር የታነጹ እንዳይሆኑ የሚያደርግ፤ ትምህርቶች በጥልቀት የማይሰጡበት ፤ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮች የማይደረጉበትና በድንገቴ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተጥለቅላቂ እንደሆነ የሚስማሙበት በርካቶች ናቸው።

የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ “አሁን በትምህርት ላይ የሚታየው የይድረስ ይድረስ አቀራረብ በራሳቸው የማይተማመኑና የተቀባይነት መንፈስ የተጠናወታቸው ዜጎችን እያወጣ ነው።

የዝቅተኝነት መንፈስ ደግሞ በራስ የመተማመን አቅም የጎደላቸው ዜጎችን ማፍራቱ አይቀርም።” ብለዋል። ዶክተሩ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ምዕራባውያን የተጋፈጡት መጥፎ ክስተት ኢትዮጵያ ደጅ መቆሙን ጠቁመው ነበር። ለዚህም ጆርጅ ኢለየት የተባሉት ባለቅኔና ሃያሲ የተናገሩትን ተከታዩን ሀሳብ በአስረጅነት ጠቅሰዋል።

“አውሮፓና አሜሪካ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ትምህርት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ፖሊሲ ቀርፀው ተንቀሳቅሰው ነበር። የዘመቻው ተልዕኮ ተሳክቶ በሀገራቸው የነበረውን የመጀመሪያ ደረጃ ማይምነት ድል አደረጉ።

ነገር ግን ፖሊሲው የተመረኮዘው ሽፋን (ቁጥር) ላይ እንጂ ጥራት ላይ ስላልነበረ ወዲያው አይበገሬ የሆነው ሁለተኛ ደረጃ ማይምነት ብቅ አለ። አውሮፓና አሜሪካ ከጋዜጣ ርዕስ በላይ የማያነቡ ፤ የታሪክ እና የስነፅሁፍ መጽሐፍ የማይፈልጉ ፤ ከስፖርትና አልባሌ ወሬዎች ውጭ መወያየት የማይሹ ፤ በራሳቸው የማይተማመኑ በአጠቃላይ ፀረ-ቀለም የሆኑ ዜጎችን አፈሩ።

“የመጀመሪያውን ማይምነት ማሸነፍ ቀላል ነበር። ሁለተኛውን ማሸነፍ ግን እጅጉን ከባድ ነው። የመጀመሪያውን ደረጃ ማይምነት ማሸነፍ ቀላል የሆነው አለማወቃቸውን የሚያውቁ ስለሆኑ ፤ ተማሩ ሲሏቸው ስለሚማሩ ነው። ሁለተኛውን ማይምነት አስቸጋሪ ያደረገው ተምራችኋል፤ አውቃችኋል ተብለው የተለያየ የአዋቂነት ምስክር ወረቀት ወይም ዲግሪ መቀበላቸው ነው።”

እኛንም የምንገኝበት ሁኔታ ላይ ያደረሰን ለሰላሳ ዓመታት የተጓዝንበት መንገድ ነው። ዛሬ በመንደርሲቲዎች ውስጥ እየተከሰቱ ያሉት ችግሮች ለዓመታት ሳንታክት በሰራናቸው ስራዎች ያገኘናቸው ውጤቶች ናቸው። እናም የዘራነውን እያጨድን ነው።

ችግሮቹን መቅረፍ የምንችለው የዕድሜያቸውን ያህል ጊዜ ወስደን የማያቋርጥ ስራ መስራት ስንችል ነው። የችግሮቹን ጥልቀት ከግምት ያስገባ ጥናት ሳይደረግ እዚህም እዚያም በደመነፍስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለጊዜው ግጭት እንዲቆም ለማድረግ ያግዙ ይሆናል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያስገኙም።

በዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ አንድ ሻለቃ ጦር ማቆምና የደህንነት ካሜራዎችን መትከል ከችግሩ ጋር ለመክረም እንደ መወሰን ይቆጠራል። ግቢ ውስጥ ላለ ችግር አጥር ማጠር መፍትሄ የሚሆነው ችግሩ ከግቢ እንዳይወጣ ለመከላከል ብቻ ነው። መፍትሔ መልኩ ሁለት ነው። አንድም ከህመም ይፈውሳል፤ አንድም ያላምዳል።

ሁነኛው ገላጋይ ግን ፈውስ ነው። ፈውስ ከተመረጠ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ቀደመ ስማቸው ተመልሰው “ዩኒቨርሲቲዎች” ይባላሉ ፤ መላመድ መፍትሔ ከሆነ ግን መንደርሲቲዎች ሆነው ይቀጥላሉ።

ምንጭ አዲስ ዘመን