ኤርትራና ኳታር የቃላት ጦርነት ጀምረዋል።


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

– ኳታር የተለያዩ የሽብርና የተቃውሞ ተግባራት በኤርትራ ውስጥ እንዲፈጸሙ የማስተባበር ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን እንደደረሰበት የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

– የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር “ከክስና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመጠቀም ይልቅ እውነታዎችንና የችግሮቹን ስር መሰረት መለስ ብሎ እንዲመረምር” የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።

BBC Amharic : ኳታር የተለያዩ ኃይሎችን በመጠቀም የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመግደል ዕቅድ እንዳላት እንደደረሰበት የኤርትራ መንግሥት ይፋ አደረገ።

የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ኳታር የተለያዩ የሽብርና የተቃውሞ ተግባራት በኤርትራ ውስጥ እንዲፈጸሙ የማስተባበር ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን እንደደረሰበትም አስታወቀ።

ለዚህም ተግባር ጎረቤት ሱዳንን እንደ ድልድይ በመጠቀም የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ ተግባራት በኳታር ደጋፊነት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

ኳታር ከፍተኛ ባለስልጣኖቼን ለመግደል ዕቅድ አላት በማለት ኤርትራ ያቀረበቸውን ክስ የኳታር መንግሥት አጣጣለው።

በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል ለወጣው ክስ አዘል መግለጫ ኳታር በሰጠችው ምላሽ “ሐሰት” በማለት ክሱን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጋዋለች።

የኤርትራ መንግሥት በተጨማሪም ኳታር ተቃዋሚ ቡድኖችን በመደገፍ በኤርትራ መንግሥት ላይ አመጽና ተቃውሞን ለመቀስቀስ መጣሯን በክሱ ላይ አመልክቷል።

ኳታር ባወጣችው መግለጫ የኤርትራ መንግሥት ከጠቀሳቸው የትኛውም አንጃ ሆነ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት በመግለጽ “ይህንንም የኤርትራ መንግሥት በደንብ ያውቀዋል” ብላለች።

‘ኳታርና ተላላኪዎቿ’ እብደታቸው እያደገ ነው ብሎ የሚጀምረው መግለጫው “ኳታርና ሸሪኮቿ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ወጣቶችን በመቀስቀስ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና ተቃውሞ እንዲያስነሱ ተዘጋጅታለች” ሲል ይከሳል።

መግለጫው “ሙስሊም የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶችን በመስበክ በኤርትራ ሕዝብ መካከል የብሔር ጥላቻ በመዝራት፣ ሙስሊሞች በሌላው ሕዝብ ላይ እንዲነሱ የሐሰት ወሬ እያሰራጨች ነው” ይላል።

በተጨማሪም በኤርትራ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ቪድዮዎችን በማዘጋጀት ተቃውሞና አድማዎች እንዲካሄዱ በማበረታታትና የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ የኤርትራ መንግሥት ኳታርን ይከሳል።

በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ላይ ጥቃት እንዲፈጸምና ውድመት እንዲደርስ እንዲሁም አስፈላጊ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የመንግሥት ባለስልጣናትን ለመግደል ስልጠና እየሰጠች ነው ይላል።

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚታወቁትን ሌሎች ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መንገዶችን ከመጠቀም ይልቅ” በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በወጣው መግለጫ ግራ መጋባቱን ጠቅሷል።

የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ከዚህ ቀደም ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበረውና ለዚህም የተለያዩ ተግባራት ሲያከናወኑ መቆየታቸውን፤ ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር ያላትን ያለመግባባት ለመፍታት ኳታር ያደረገቸውን ጥረት በምሳሌነት አንስቷል።

የኤርትራ መንግሥት በመግለጫው ላይ ኳታር “የኤርትራ መንግሥት በእስላማዊ ተቃዋሚዎች መካከል ጽንፈኛ ሐይማኖታዊ አመለካከቶችን በማስረጽ አመጽ በመቀስቀስ፣ በወገኖቻቸው ላይ እንዲነሱ” ፍላጎት አላት ሲል ይከሳል።

በቅርቡ የወደብ ከተማዋን ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በምሥራቃዊ ሱዳን፣ በነዋሪዎች መካከል ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን በማንሳት ኤርትራ በመግለጫዋ ኳታርን “ፖርት ሱዳን ውስጥ የጎሳ ግጭቶች እንዲከሰቱ” በማድረግ ወቀሳ ሰንዝራለች።

በምሥራቃዊ ሱዳን በብሔሮች መካከል ግጭት መፍጠርን በሚመለከትም ‘አጃኢብ የሚያሰኝ ዕቅድ’ ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የኤርትራ መንግሥት ቱርክ እና ኳታር በኤርትራ ላይ አውዳሚ ተግባራት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።

ቱርክ በዚህ ዓመት ‘የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት’ በሚል የሚታወቀው ቡድን ጽህፈት ቤቱን እንዲከፍት መፍቀድዋን ጠቅሶ ይህም መግለጫው ‘አውዳሚ’ ላለው አላማ እንደሚውል ይገልጻል።

የኤርትራ ዑላማ ምክር ቤት (መጅልስ ሹራ ራቢጣ ዑላማእ ኤሪትሪያ) በሱዳን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለው የቡድኑ አባል የሆኑት መሓመድ ጁማ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የኤርትራን ክስ ተከትሎም የኳታር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር “ከክስና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመጠቀም ይልቅ እውነታዎችንና የችግሮቹን ስር መሰረት መለስ ብሎ እንዲመረምር” ጥሪ አቅርቧል።

በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያጋጠመው ቀውስ እስከተፈጠረበት ጊዜ ድረስ ኤርትራ ከኳታር ጋር ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት ነበራት።

በሳዑዲ አረቢያ በሚመሩት አገራትና በኳታር መካከል አለመግባባቱ ሲፈጠር ኤርትራ ወዳጅነቷን ከሳዑዲና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጎን በመቆም የመን ውስጥ የሚካሄደውን ዘመቻ ደግፋለች።

በዚህም ሳቢያ አገራቱ የመን ውስጥ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ለማገዝ ኤርትራ ከወደብ ከተማዋ አሰብ ወጣ ብሎ የሚገኝ ወታደረዊ ሰፈርን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሠራዊት እንዲጠቀምበት ፈቅዳለች።

የኤርትራ መንግሥት “ይህንን ከንቱ ተግባር በተለያየ መንገድ በመደገፍ በኩል ኳታርና ለእንደዚህ እኩይ አላማ ግዛቱን አሳልፎ በሰጠው የሱዳን ሥርዓት አማካይነት የሚፈጸሙ ናቸው” ሲል ከሶ ነበር።

ኤርትራ ከኳታር ጋር የነበራት ጠንካራ ዝምድና በመሻከሩ በሳዑዲ አረቢያ ወደ ሚመራውን የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጥምረት ፊቷን አዙራለች።

ከአራት ዓመታት በፊት በየመን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለፈጸመው በሳዑዲ የሚመራውን ኅብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ኤርታራ አስታውቃ ነበር።

ሳዑዲና አረብ ኤምሬቶች የሚገኙበት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጥምረት ኳታርን ካገለሉና የየብስና የባሕር መተላላፊያ ማእቀቦችን ከጣሉባት በኋላ ቱርክ የኳታር ሸሪክ መሆንዋን ይታወሳል።