ከባድ ሚስጥራዊ መረጃ፡- ጄ/ል ሳሞራ ዬኑስ በሱዳን 8ሺህ ወታደር እያሰለጠኑ ነው!

በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከሚፈፀሙ የተቀናጁ የወንጀል ተግባሮች፣ የብሔር ግጭቶች፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ወዘተ በስተጀርባ የህወሓቶች እጅ እንዳለ ስንናገር ለአንዳንዶች ውሸት ይመስላቸዋል። በእርግጥ ለህወሓት አባላትና ደጋፊዎች በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ ማቅረብ ቀርቶ ድርጊቱ ከዓይናቸው ስር የተፈፀመ ቢሆን እንኳን አምነው ለመቀበል ይቸግራቸዋል። ምክንያቱም እንዲህ ያለ የማፍያ ቡድን አባልና ደጋፊ መሆንን አምኖ ከመቀበል ይልቅ በተግባር ያዩትን እውነት መካድ ይቀላቸዋል። ነገር ግን ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆን በተደጋጋሚ የህወሓቶችን እኩይ ተግባራት የሚያሳዩ መረጃዎች ሲቀርቡለት በሙሉ ልብ አምኖ ለመቀበል ይቸግረዋል። ምክንያቱም ህወሓት ጨቋኝና ዘራፊ የሆነ የፖለቲካ ቡድን እንጂ የተደራጀ የማፍያ ቡድን እንደሆነ በግልጽ መገንዘብ ተስኖታል። ሆኖም ግን በተደጋጋሚ የሚደርሱን ሚስጥራዊ መረጃዎች የሚያሳዩት ቢኖር ህወሓት ትክክለኛ የማፍያ ቡድን መሆኑን ነው። ዛሬም የደረሰን ሚስጥራዊ መረጃ ይህንን እውነት የሚያረጋግጥ ነው።

በዛሬው ዕለት የደረሰን ሚስጥራዊ መረጃ አንድ ማንነቱ ያልተገለፀ የደህንነት ሰራተኛ የህወሓቶችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ያዘጋጀው ሪፖርት ነው። በዚህ መሰረት ህወሓት ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ ከፍተው ወደ 8ሺህ ሰራዊት በድብቅ እያሰለጠኑ እንደሆነ፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ቡድኖችን መቀሌ ላይ በመሰብሰብ እየሸረቡት ያለው ሴራ፣ መቀሌ ላይ የመሸገው የህወሓት ማፊያ ቡድን በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም አንዳንድ የደቡብ ልሂቃን ከህወሓት ጋር በመመሳጠር በተለይ በወላይታ ዞን ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየሰሩት ያለው ስራ በሪፖርቱ ተካትቷል። ይህ ሪፖርት በአጠቃላይ ሰባት ገፆች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስቱ ገፅ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ደርሶናል። በዚህ መሰረት ከላይ በተገለፁት አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የቀረበውን ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል።