በድፍረት በመጋፈጡ ዋጋ እየከፈለ ያለው ቢልየነር

ቢልየነሩ ጂሚ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ቢልየነሩ ጂሚ ላይ

በ2022 ክረምት ላይ ራፋኤል ዎንግ እና ፊጎ ቻን ሆንግ ኮንግ ወደሚገኝ እስር ቤት አቅንተው ከጂሚ ላይ ጋር ተገናኙ።

ቢሊየነሩ ጂሚ ሊ ከሁለት ዓመት በላይ ታስሮ ፍርድ እየተጠባበቀ ነበር። የተከሰሰው ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ነው። ከሳምንት በፊት ቢልየነሩ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ሆንግ ኮንግን በናጠው ተቃውሞ ውስጥ ሁሉም ተሳትፈዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል። ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እና ከቻይና ነጻ ለመውጣት ጠይቀዋል።

ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ እንገናኛለን ብለው አላሰቡም።

የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ተቀልብሶ የመብት ተሟጋቾች ታስረዋል። ጂሚ ‘ወፍራሙ’ የሚል ቅጽል የነበረው ቢሆንም ከታሰረ በኋላ ከስቷል።

በ70ዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ጂሚ፤ ከ40 ዓመት ታናናሾቹ ጋር ተቃውሞውን ተቀላቅሏል። በግንባር ቀደምነት ስሙ ይጠራም ነበር።

‘አፕል ዴይሊ’ የተባለ ታዋቂ ጋዜጣ ነበረው። ሆንግ ኮንግ ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን የሚጠይቁ ጽሑፎች ያስተናግዳል።

ይህም የቻይና መንግሥት ካወጣው ጥብቅ ክልከላ ጋር የሚቃረን ድርጊት ተደርጎ ተወስዷል።

ጂሚ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ዜጋ ቢሆንም ሆንግ ኮንግን ጥሎ ለመውጣት አልፈቀደም።

“ያለኝን ሁሉ ያገኘሁት ሆንግ ኮንግ ውስጥ ነው” እያለ በማልቀስ በ2020 ለቢቢሲ ቃለ ምልልስ ከሰጠ ከሰዓታት በኋላ ታሰረ።

ሆንግ ኮንግ ነጻነት እንድትቀዳጅ ይሻል። የቻይናን ኮምኒስት ፓርቲም አጥብቆ ይተቻል። ለዴሞክራሲ ያደረገው ትግል ነጻነቱን ቀምቶታል።

የጂሚን ክስ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ለኮምኒስት ፓርቲው ክፉኛ ጥላቸው አለው። በምዕራባዊ ርዕዮተ ዓለም እንዲተካ ይፈልጋል” ብሏል።

ከተቻለ ፓርቲውን ለማስወገድ፤ ካልተቻለ ደግሞ የፓርቲው መሪ ዢ ጂን ፒንግን ለማስወገድ እንደሚፈልግም ተገልጿል።

ጂሚ ክሶቹን ቢያስተባብልም ጥፋተኛ ተብሏል። ከቀረቡበት ክሶች ጠንካራው ከውጭ አገራት ጋር መመሳጠር ነው። እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ያስፈርዳል።

ለሆንግ ኮንግ መሻሻል እንደታገለ በመግለጽ ከውጭ አገራት ጋር መቼም ቢሆን አለመጣመሩን ይናገራል።

“የታገልኩት ለሕግ የበላይነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለንግግር ነጻነት፣ ለሃይማኖት ነጻነት እና ለመሰብሰብ ነጻነት ነው” ይላል።

የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪ ጆን ሊ በጂሚ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ደግፈዋል። በጋዜጣው “ማኅበራዊ ቀውስ” ለመፍጠር ሞክሯል ሲሉ ወንጅለዋል።

“በሰብአዊ መብት፣ በዴሞክራሲ እና በነጻነት ስም አገርን መጉዳትን ሕጉ አይፈቅድም” ብለዋል።

የጂሚ ባለቤት እና ልጅ
የምስሉ መግለጫ,የጂሚ ባለቤት እና ልጅ

ጂሚ በ2022 ሊጠይቁት እስር ቤት የሄዱትን ጓደኞቹን ‘ፀልዩልኝ’ ነበር ያላቸው።

ለብቻው እንዲታሰር በጠየቀው መሠረት ብቻውን ታስሯል። የካቶሊክ ሃይማኖትን አጥብቆ መከተሉንም ቀጥሏል።

እስር ቤት ሳለ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕል እያዘጋጀ ለጓደኞቹ ይልካል።

ጓደኛው እንደሚለው ጂሚ ፍርሃት አይታይበትም። ቅሬታም አያሰማውም። ይልቁንም ሰላም ይነበብበታል።

በ12 ዓመቱ ከቻይና ሸሽቶ ሲወጣ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ነበር። በሒደት ቢልየነር ሆነ።

ቻይና ያጣችው ሁሉ ሆንግ ኮንግ እንዳላት ያምናል። ሆንግ ኮንግ ካፒታሊስት እና የዕድል በሮች የተከፈቱባት ናት።

ጂሚ በአውሮፓውያኑ 1959 ሆንግ ኮንግ ሲገባ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች።

በ1995 የጀመረው ጋዜጣ እጅግ ዝነኛ ነው። ከአሜሪካው ‘ዩኤስኤ ቱዴይ’ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ጋዜጣን ያዘመነ እንደሆነ ይነገርለታል። ጋዜጣው የምጣኔ ሃብት ተንታኞች፣ ደራሲያን እንዲሁም በወሲብ ንግድ ለሚተዳደሩም አምድ ሰጥቷል።

በሆንግ ኮንግ የቻይና ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኛነት የሚያስተምሩት ፍራንሲስ ሊ እንደሚሉት ጋዜጣው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አንባቢያንን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የቀድሞው የጋዜጣው አርታኢ፤ ጂሚ ደፋር የሆነ ጋዜጠኛነትን ይደግፋል። ከተለመደው አሠራር ወጣ ብሎ ማሰብ የሚችል ሰው እንደሆነም ይናገራል።

የልብስ አምራች ፋብሪካ ሲከፍትም ተመሳሳይ መንገድ ነው የተከተለው። ኢንዱስትሪው ላይ በድፍረት ለውጥ ከማምጣት አላፈገፈገም።

ተገዳዳሪ ልብስ አምራች ውስጥ የሚሠራ የማስታወቂያ ባለሙያ “ጠላቶች ቢያፈራም ግድ አልነበረውም” ሲል ይገልጸዋል።

በቴሌቪዥን የተላለፈ የጋዜጣው ማስታወቂያ ጂሚ ‘የተከለከለውን አፕል’ ሲመገብ ከየአቅጣጫው ቀስት ሲወረወርበት ያሳያል። ማስታወቂያው ሲሠራ ገና 48 ዓመቱ ነበር።

ማስታወቂያው ለወደፊቱ የጂሚ ሕይወት ትንቢት ይመስላል።

በቴሌቭዥን የተላለፈ የጋዜጣው ማስታወቂያ ጂሚ 'የተከለከለውን አፕል' ሲመገብ ከየአቅጣጫው ቀስት ሲወረወርበት ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት,Jimmylai.substack.com

የምስሉ መግለጫ,በቴሌቭዥን የተላለፈ የጋዜጣው ማስታወቂያ ጂሚ ‘የተከለከለውን አፕል’ ሲመገብ ከየአቅጣጫው ቀስት ሲወረወርበት ያሳያል።

ከቻይና ማምለጥ

ጂሚ ገና ልጅ እያለ ቼኮሌት ቀመሰ። በባቡር ጣቢያ ሻንጣ ተሸክሞ ቼኮሌት ተሰጠው።

“ቼኮሌት የሰጠኝን ሰው ‘ከየት ነህ?’ ስለው ከሆንግ ኮንግ አለኝ። ‘ሆንግ ኮንግ ገነት መሆን አለባት፤ እንዲህ ያለ ነገር ቀምሼ አላውቅም’ አልኩት” ሲል ያስታውሳል።

ማኦ ዜ ዶንግ የሚመሯት ቻይና በጥብቅ ሕግ ትመራ ነበር። ካፒታሊስቶች የሚሳደዱበት አገር ናት።

የጂሚ ቤተሰብም ከንግድ ታገደ። እናቱ የግዳጅ ሥራ ማዕከል ተላከች።

እናቱ ከቤቷ ወጥታ እንድትንበረከክ በማስገደድ ሕዝቡ እንዲሳለቅባት መደረጉን ያስታውሳል። እሱ እና እህቶቹ ያንን የውርደት ቀን አይረሱትም።

“ሰውነቴ በሃፍረት ተቃጠለ። እንባዬ ያለ ማቋረጥ ፈሰሰ። ከቆምኩበት መነቃነቅ አቃተኝ” ይላል ጂሚ።

አያቱ ሁሌም ነጋዴ እንዲሆን ይገፋፉት ነበር።

በ12 ዓመቱ ከሚሊየነሮች ጋር ከቻይና ሸሸ። ሆንግ ኮንግ ጓንት ፋብሪካ ውስጥ ተቀጠረ።

“የወደፊት ተስፋ እንዳለኝ በማሰብ ደስተኛ ሆንኩ” ይላል። የሥራ አጋሮቹ እንግሊዝኛ አስተማሩት።

በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ሳለ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠርቷል። በአክስዮን ገበያ ያገኘውን ገንዘብ ይዞ በ27 ዓመቱ ‘ኮሚቴክስ ኪትነርስ’ የተባለ ፋብሪካ ከፈተ።

ለንግድ ኒው ዮርክ ይመላለስ ነበር። ኖቤል አሸናፊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ፍሬድሪክ ሃያክ የጻፈውን ‘The Road to Serfdom’ ማንበቡ ማንነቱን ለውጦታል።

ጂሚ ንግድ የጀመረው በ27 ዓመቱ ነው

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ንግድ የጀመረው በ27 ዓመቱ ነው

ሆንግ ኮንግ ያላትን የነጻ ገበያ አቅም ያየበት ነው። አንድን መጽሐፍ ደጋግሞ የማንበብ ልማድ አለው። የሚወዳቸው ደራሲያንን ሥራዎችም አዘውትሮ ያነባል።

“የደራሲዎችን ሐሳብ መውረስ እፈልጋለሁ። የአበባ እቅፍ ሳይሆን የአበባ ማሳ እንዲኖረኝ እመኛለሁ” ሲል በ2009 በሰጠው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

የፋብሪካ ሥራ ሲሰለቸው ‘ጊሮዳኖ’ የተባለ ልብስ ማምረቻን በ1981 ጀመረ። በጣም ዝነኛ የፋሽን ዲዛይነሮች ያማክሩት ነበር።

ማኦ ሲሞቱ ቻይና ዴሞክራሲያዊ ትሆናለች ብሎ ተመኘ። በቻይና መደብሮችም ከፈተ።

በ1989 በቤጂንግ ቲያናሚን አደባባይ ዴሞክራሲን የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ላይ ቻይና ጥቃት ፈጸመች።

ዩኬ በ1977 ሆንግ ኮንግን ወደ ቻይና አስተዳደር ለመመለስ ስምምነት ነበራቸው።

የጂሚ ልብስ ማምረቻ በቲያናሚን አደባባይ የነበሩ ወጣቶችን ምሥል ካናቴራ ላይ እያተመ ይሸጥ ጀመር።

በሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ሚሊዮኖች ተሳትፈዋል። በ2020 የቲያናሚን ጭፍጨፋ መታሰቢያ በሆንግ ኮንግ ተዘጋጅቷል።

ጂሚ ቻይናን መርሳት ቢፈልግም “የጨለማው ሕይወቴ ሊተወኝ የፈቀደ አይመስልም” ይላል።

በቲያናመን አደባባይ ለተፈጸመው ግድያ የተደረገ መታሰቢያ
የምስሉ መግለጫ,በቲያናመን አደባባይ ለተፈጸመው ግድያ የተደረገ መታሰቢያ

‘ነጻነት ምርጫ ነው’

ኔክስት የሚል ጋዜጣ መሥርቶ በ1994 ይፋዊ ደብዳቤ አትሟል። በቲያናሚን አደባባይ ለተፈጸመው ግድያ ተጠያቂ ለሆነው ሊ ፒንግ የተጻፈ ነበር።

ቻይና በዚህ ተቆጥታለች። ከ1994 እስከ 1996 በሻንጋይ የሚገኙ 11 የጂሚ መደብሮች ተዘግተዋል። ድርሻውን ሸጦ ከድርጅቱ ኃላፊነት ለቀቀ።

“ገንዘብ ማግኘት ብቻ ትርጉም የለውም። ሚዲያ ሲኖረኝ ግን መረጃ አደርሳለሁ። ይሄ ምርጫዬ ነው። ምርጫ ደግሞ ነጻነት ነው” ሲል በ2007 በተላለፈ ዘጋቢ ፊልም ላይ ተናግሯል።

ከዚያም በሆንግ ኮንግ የዴሞክራሲ ንቅናቄ ዋነኛ ተሳታፊ ሆነ። የቀድሞው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሕግ አውጪ ሊ ዊንግ ታት እንደሚለው፤ እየተገናኙ ስልት ይነድፉ ነበር።

ሆንግ ኮንግ ለቻይና መተላለፏን ይቃወማል።

“ኮምኒስት ፓርቲውን እቃወማለሁ። የግል ነጻነትን ይጋፋል” ሲልም ጽፏል።

“ከዓመታት ቅኝ ግዛት በኋላ ከእናት አገር ጋር መዋሀድ የሆንግ ኮንግን ነዋሪዎች አስደስቷል። እናት አገር ነጻነት ባትሰጠንም ልንወዳት ይገባል?” ሲል ይጠይቃል።

ሆንግ ኮንግን ከዩኬ የተረከቡት የቻይናው መሪ ዢያንግ ዚማን ሆንግ ኮንግ ለ50 ዓመታት የውሳኔ መብት እንደሚኖራት ቃል ገብተዋል።

ቻይና በ2014 በሆንግ ኮንግ ነጻ ምርጫ እንዳይከናወን ጣልቃ ስትገባ ‘አምብሬላ ሙቭመንት’ የተባለው ንቅናቄ ተጀመረ።

ለ79 ተከታታይ ቀናት ተቃዋሚዎች አደባባዩን ተቆጣጠሩ። ጂሚ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ለተቃውሞ ይወጣል። አንድ ግለሰብ የእንሰሳ ዐይነ ምድር ወርውሮበት እንኳን ከተቃውሞ አልቀረም።

ፍርድ ቤት የተቃውሞ ቦታዎች እንዲዘጉ ሲያዝ ተቃውሞዎች ጋብ አሉ። ከአምስት ዓመታት በኋላ በ2019 የወንጀል ተጠያቂዎችን ለቻይና አስተላልፎ የሚሰጥ ሕግ ሲረቀቅ ተቃውሞው አገረሸ።

ሰላማዊው ተቃውሞ ወደ ነውጥ አመራ። ለስድስት ወራትም ቀጠለ። ተቃዋሚዎች በቤታቸው ተቀጣጣይ ነገሮችን ሠርተው በአደባባይ ይወረውሩ ነበር። ምክር ቤቱን ጥሰውም ገብተዋል።

ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ፣ ውሃ እና የፕላስቲክ ጥይት ተኩሷል። ጂሚ ፈቃድ ባልተሰጠው ስብሰባ በመገኘት ለ20 ወራት ታስሯል።

ቢቢሲ ያነጋገረው ተቃዋሚ ጂሚን በአደባባይ ማየቱ አስገርሞታል። “ጊዜ የሌለው ነጋዴ ነው። ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም” ብሏል።

ጋዜጣው ‘አፕል ዴይሊ’ ለተቃውሞው ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል።

ጂሚ የልብስ ማምረቻ ከፍቶ ዝነኛ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,ጂሚ የልብስ ማምረቻ ከፍቶ ዝነኛ ሆኗል

የቻይና መንግሥት አማካሪ ሮኒ ቶንግ ጋዜጣው ተቃውሞውን ማቀጣጠሉን ገልጸዋል።

“ሐሰተኛ መፈክር ያትሙ ነበር። ሆንግ ኮንግ ቀውስ ውስጥ የገባች አስመስለዋል” ብለዋል።

ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በጂሚ የተከፈተው ክስ ለ156 ቀናት ዘልቋል።

ጋዜጣው ሁለት ጊዜ በፖሊሶች ፍተሻ ተደርጎበት በ2021 ተዘግቷል።

የጋዜጣው እህት ድርጅት የአርትኦት ክፍል ባልደረባ የነበው አንግ ኪም-ሀንግ እንደሚለው ጂሚ “ሰዎችን ለተቃውሞ የሚያነሳሱ ጽሑፎች” እንዲወጡ አሳስቧል።

ተከሳሽ የነበረው አንግ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ተቃውሞው ሲቀጣጠል ጂሚ አሜሪካ ሄዶ ከቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር ተወያይቷል።

ቻይና በዚያው ወቅት ነበር የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ ያወጣችው። ጂሚ ግን የጋዜጣው አንባቢዎች ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‘ሆንግ ኮንግን አድኗት’ የሚል ደብዳቤ እንዲጽፉ ያበረታታ ጀመር።

በዚህም ምክንያት በሆንግ ኮንግ የውጭ አገር ጣልቃ ገብነትን ጋብዟል በሚል ተከስሷል።

ሆንግ ኮንግ ፖለቲካዊ ለውጥ ታመጣለች ብሎ ማንም አለመጠበቁን ከተቃዋሚዎቹ አንዱ ይናገራል።

ቻይና የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ በማውጣቷ ሆንግ ኮንግ ሰላም እንደሰፈነባት ትናገራለች።

ጂሚ በሆንግ ኮንግ ተቃውሞ አንድም ቀን አደባባይ ከመውጣት ወደኋላ አላለም

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,ጂሚ በሆንግ ኮንግ ተቃውሞ አንድም ቀን አደባባይ ከመውጣት ወደኋላ አላለም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በአገር ወዳዶች” የተሞላ ሆኗል በሚልም ቻይና ገልጻለች።

ተቃውሞው ከስሞ የዜጎች ነጻነት ተነጥቋል።

የቀድሞው ሕግ አውጪ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሸሽተዋል። “ዩኬ እንደመጣሁ የጥፋተኛነት ስሜት ዋጠኝ። ጓደኞቼ ታስረው እንዴት በነጻነት እንቀሳቀሳለሁ? አልኩ” ይላሉ።

ጂሚ የስኳር በሽታ ስላለበት ከእስር እንዲፈታ ቤተሰቡ በተደጋጋሚ ጠይቋል። መንግሥት አልፈቀደም።

ልጁ ካምረት ሳንግ “ልጆቼ አያታቸው ናፍቋቸዋል። በየሁለት ሳምንቱ ትልቅ የቤተሰብ እራት ያዘጋጅ ነበር” ስትል ታስታውሳለች።

“ልጆቼ እሱ ቤት መሄድ ደስ ይላቸዋል። ያስቃቸዋል” ትላለች። ሆንግ ኮንግ ግን ነጻ እንደማትለቀው እርግጠኛ ናት።

“ዐይን ውስጥ አፈር ከገባ መውጣቱ አይቀርም” ስትልም ጉዳዩን በምሳሌያዊ ንግግር ትገልጻለች።