በርካታ ሴቶች የሚጠቀሙት ዕፅ እና መዘዙ

“ልጄን ያጣሁት ሱሰኛ በመሆኔ ነው”፡ በርካታ ሴቶች የሚጠቀሙት ዕፅ እና መዘዙ

ከጀርባ የምትታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

አይሾቱ በታባ ሱስ ትሰቃያለች። ልጇን ያጣችው በሱስ ምክንያት እንደሆነም ታምናለች።

ታባ የትንባሆ ቅጠል ደርቆ፣ ተፈጭቶ የሚዘጋጅ አደንዛዥ ዕፅ ነው።

ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረው አይሾቱ የምትኖረው ጋምቢያ ነው። ባለቤቷን በሞት ተነጥቃለች።

ለ15 ዓመታት ያህል ታባ ተጠቅማለች። በመሀል ለማቆም ብትሞክርም ከሱስ መላቀቅ አቃታት።

በተለይም በምዕራብ አፍሪካ በርካቶች በታባ ሱስ ይንገላታሉ። አንዳንዶች በአፍንጫቸው ይስቡታል፤ ሌሎች ደግሞ ያጨሱታል፤ የሚያላምጡትም አሉ።

እንደ አይሾቱ ያሉ ሴቶች ታባ በምሥጢር ገዝተው በብልታቸው ውስጥ ያስገቡታል።

ቢቢሲ አይሻቱን ያገኛት መንግሥት ባዘጋጀው የፀረ-ታባ ግንዛቤ መስጫ ላይ ነው። ታባ መጠቀም መጀመሯ ይጸጽታታል።

ሴቶች በምሥጢር የሚገዙት እና የሚሸጡት ታባ

ታባ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች በምሥጢር ይሸጣል። ሴቶች በመላው አገሪቱ ታባ ይሸጣሉ፤ ይገዛሉ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ታባ የሚቀመምበት መንገድ ተለውጧል። በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የትንባሆ ቅጠል ወደ ዱቄት ይለወጣል።

አይሻቱ እአአ በ2021 ስታረግዝ ዕፁን ለማቆም ወሰነች። ከዚያ በፊት ባረገዘችባቸው ወቅቶች ዕፁን መጠቀም አቁማ ነበር።

በ2021 ስታረግዝ ግን ታባ ማቆም ተሳናት። ልጇንም በሞት ተነጠቀች።

ልጇን ያጣችው በታባ ምክንያት እንደሆነ ታምናለች። ልጇ ማሕጸኗ ውስጥ መንቀሳቀስ ሲያቆም ነበር ወደ ሆስፒታል የሄደችው።

“ዶክተሮች ልጄ መሞቱን ገለጹልኝ። ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንዳለብኝ አሳወቁኝ። ልጄን ከማሕጸኔ ሲያወጡት ቆዳው ተቃጥሏል። ልጄን የገደለው ታባ እንደሆነ አወቅኩ።”

አይሻቱ ልጇን ያጣችው በታባ ምክንያት መሆኑን ብትገልጽም፤ በሕክምና አልተረጋገጠም።

ታባ የጀመረችው ከዓመታት በፊት ነው። የሰውነት ክብደት ለመቀነስ እና ለማርገዝ እንዲረዳት በሚል ነበር የጀመረችው። አደንዛዥ ዕፁ ግን ምንም አልፈየደላትም።

“ታባ ሰውነት ውስጥ ሲገባ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። ጤናማ ስሜት ውስጥ ለመግባት የግድ ታባ መጠቀም ያስፈልጋል። ታባ ያስደስተኝ ነበር። ሆኖም የወሲብ ፍላጎቴ ቀነሰ። በጣም በሱስ ከመጠመዴ የተነሳ በቀን ሦስቴ እና አራቴ እወስድ ነበር” ትላለች።

ልጇ ከሞተ በኋላ አደንዛዥ ዕፁን መጠቀም ብታቆምም የማሕጸን ካንሰር እንዳለባት ተነገራት።

ሌላዋ የታባ ሱሰኛ ራሺዳ (ስሟ ተለውጧል) ናት። የማንጎ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ከቢቢሲ ጋር ባደረግቸው ቃለ ምልልስ ለሰባት ዓመታት ታባ መጠቀሟን ገልጻለች።

ሱስ እንዴት ሕይወቷን እንደተቆጣጠረው ስትናገር እምባ እየተናነቃት ነው።

የባለቤቷ እህት ሆስፒታል ገብታ ልትጠይቃት የሄደችበትን ጊዜ አትረሳውም። በወቅቱ ለሦስት ቀናት የባለቤቷን እህት መንከባከብ ይጠበቅባት ነበር።

“ሆስፒታል ስሄድ ታባዬን ረስቼ ነበር። ምንም ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አቃተኝ” ትላለች።

ታባ ለመግዛት ወደ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ስትሄድ ሱሷ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ ታወቃት።

ታባ

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,ታባን አንዳንዶች በአፍንጫቸው ይስቡታል፤ ሌሎች ደግሞ ያጨሱታል፤ የሚያላምጡትም አሉ።

ታባ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚጠቀም ሰው በስቃይ የተሞላ ተሞክሮ መሆኑን ሁለቱም ሴቶች ተናግረዋል።

“መጀመሪያ ታባ ስወስድ ከአንድ ሰዓት በላይ ራሴን ሳትኩ። ሁለተኛ አልጠቀምም ብዬ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ስወስደው አስመለሰኝ። ዕፁን የሰጠኝ ሰው ያስመለሰኝ ሰውነቴ እየጸዳ ስለሆነ ደጋግሜ እንድወስድ ነገረኝ” ትላለች አይሾቱ።

ራሺዳም ተመሳሳይ ተሞክሮ አላት። “አዞረኝ፣ አንቀጠቀጠኝ። ወባ የያዘኝ እመስል ነበር። ትንሽ ቆይቼ ራሴን ሳትኩ። ለሦስተኛ ጊዜ ስወስደው ነው ጥሩ ስሜት የተሰማኝ” ትላለች።

በጋምቢያ ታባ እንደ ጭንቀት መድኃኒት ይወሰዳል። ኃይል ለማግኘት፣ ጤናማ ለመሆንም ይረዳል ይባላል። ሐኪሞች ግን አደገኛ መሆኑም በመናገር ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ታባ ሻጮች ገበያ ላይ የተለያዩ ሸቀጦችን በማቅረብ አደንዛዥ ዕፁን ለመሸፈን ይሞክራሉ። ምሥጢራዊ ቃላቸውን ለሚያውቅ ሰው ብቻ ነው የሚሸጡት።

በገጠር አካባቢዎች አዛውንት ሴቶች ዕፁን ያቀርባሉ።

የ56 ዓመቷ ራማት በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት ለሁለት ዓመት በምሥጢር ታባ መሸጧን ትናገራለች።

ታባ መጀመሪያ ላይ በጨርቅ ይጠቀለልና ሽታውን ለመደበቅ በወረቀት ይሸፈናል። አንድ ጥቅል 15 ዳላሲ (20 ሳንቲም) ያወጣል።

ለራማት አደንዛዥ ዕፁን የሚሸጡላት ሰዎች በውስጡ ምን እንደሚያደባልቁበት አታውቅም። ንግዷ እንደተጧጧፈ ግን ትናገራለች።

አምስት ሊትር በሚይዝ ባልዲ የሚሞላ ታባ ሸጣ 200 እጥፍ እንደምታተርፍ ገልጻለች።

ታባ መሸጥ ስትጀምር ምን ያህል ሱስ እንደሚያስይዝ አታውቅም ነበር።

“ሴቶችን እየጎዳሁ መቀጠል ስለማልፈልግ ሌላ ሥራ ካገኘሁ ታባ መሸጥ አቆማለሁ” ትላለች።

አክላም “አንድ ቀን ለኢንፌክሽን ታባ ተጠቅሜ ልሞት ደርሼ ነበር። ከዚያ ቀን በኋላ ተጠቅሜው አላውቅም። አንዳንድ ደንበኞቼም እንደሆኑ ይናገራሉ” ብላለች።

ዘ ጋምቢያ በ2020 ታባ ጎጂ ነው ስትል አውጃለች። ሆኖም ግን እርምጃ መውሰድ ላይ ክፍተት ይስተዋላል።

የሕዝብ ተወካዩ ካጃሊ ሶንኮ አገሪቱ ጠንካራ እርምጃ እንደምትወስድ ይናገራሉ።

ቀጣናዊ የዕፅ ዝውውር ሰንሰለት

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ የታባ ዝውውር ከጋምቢያ አልፎ በጊኒ ቢሳው እና ሴራ ሊዮን ይደርሳል።

በ2020 ታባ ለታዳጊ እና አዋቂ ሴቶች አደገኛ ነው ብሎ መንግሥት ቢያውጅም መሬት ላይ የሚታይ እርምጃ አልተወሰደም።

ሻጮች እና ገዢዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድም አይታይም።

ታባ ሕገ ወጥ ባይሆንም ሲጋራ ማጨስ መጀመር የሚቻለው ከ18 ዓመት በኋላ ነው።

የእናቶች ጤና ላይ የሚሠሩ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የጋምቢያ የፆታ፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ፀሐፊ ካጂል ሶንኮ “ታባ የጋምቢያን ሴቶች ጤና እየጎዳ ያለ ዕፅ ነው። ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ፖሊሲ ለማውጣት ቁርጠኛ ነን” ይላሉ።

የሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ባይ ቻም በታባ ላይ ጥናት ሠርተዋል። ሌሎች ጭስ የሌላቸው የቶባኮ ዓይነቶች ከሚያደርሱት ጉዳት በተጨማሪ ታባ ጉዳት እንደሚያስከትል በምርምር ደርሰውበታል።

ታባ ላይ በቤተ ሙከራ ጥናት እየሠሩ ያሉት ባለሙያው ተጨማሪ ግኝቶችን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

42 ሴት እና 15 ወንድ የታባ ተጠቃሚዎችን አነጋግረዋል። ያነጋገሯቸው ሰዎች የኒኮቲን መመረዝ ምልክት አሳይተዋል። እነዚህም ማስመለስ፣ ማስቀመጥ፣ ሽንት መቆጣጠር አለመቻል፣ የሰውነት መጋል እና ምቾት ማጣት ናቸው።

አንዳንድ ሴቶች ከታባ ሱስ ለመላቀቅ ካውስቲክ ሶዳ መጠቀም መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ምርመራ ባደጉበት የታባ ናሙና ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ኒኮቲን አግኝተዋል።

3.63 ሚሊግራም ወይም ኪሎግራም በሚመዝን ታባ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ምጣኔ 10 በመቶ የላቀ ንጥረ ነገር ተገኝቷል።

ቢቢሲ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሌጎስ ያስመረመረው ታባ ውስጥ ከኒኮቲን ጋር የተያያዙ ንጥረ ነገሮች (pyridine derivatives) እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ጤናማ ነው ብሎ ካስቀመጠው የበለጠ የሊድ (lead) መጠን ተገኝቷል።

የጋምቢያ መንግሥት ማኅበራዊ ንቅናቄ በማድረግ ታባ ላይ ዘመቻ ከፍቷል። በአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነ ከአደንዛዥ ዕፅ ማገገሚያ ማዕከልም ተገንብቷል።

አይሾቱ “እኔ ባለፍኩበት መንገድ ሌላ ሴት እንድታልፍ አልሻም” ትላለች።

ራሺዳም አንድ ቀን ከሱስ እንደምትላቀቅ ተስፋ አላት። “እርዳታ ከተሰጠኝ በእርግጠኛነት ታባ መጠቀም አቆማለሁ። ሌሎችም እንደ እኔ ሱስ እንዳይዛቸው ታባን እንዳይሞክሩ አሳስባለሁ” ስትልም ታስጠነቅቃለች።