ገዳይ ሳይታወቅ የደም ካሳ ከፋይ የመጣበት የኦሮሙማ ጉድ

የሞዴል ቀነኒ አዱኛን ጉዳይ በባህላዊው የገዳ ስርዓት ለመፍታት የተደረገው ጥረት ያለስምምነት ተቋረጠ
 ባለፈው ዓመት ከአርቲስት አንዱዓለም ጎሳ ጋር ትኖርበት ከነበረው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ህይወቷ ያለፈው የሞዴል ቀነኒ አዱኛን ጉዳይ በባህላዊው የኦሮሞ አባገዳዎች ስርዓት በእርቅ ለመቋጨት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን አባገዳዎች አስታወቁ፡፡
ጉዳዩን ላለፉት ሦስት ወራት በሽምግልና እና በባህላዊው የፍትህ ስርዓት ለመፍታት ሲጥሩ የቆዩት የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ፤ ጥረቱ በተጎጂ ቤተሰቦች ፈቃደኛ አለመሆን ምክንያት መቋረጡን ዶይቼ ቬለ ለእኔ ነግረውኛል ብሏል፡፡
የሽምግልናው ሂደትና የአባገዳዎች እይታ አባገዳ ጎበና እንደገለጹት፤ ጉዳዩ በመደበኛው ፍርድ ቤት እልባት ባለማግኘቱ የገዳ ስርዓት አባቶች ተጠርጣሪውንና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማገናኘት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። “ሆኖም በአራተኛው ቀጠሮ የሟች አባት አቶ አዱኛ ዋቆ ሂደቱን አፍርሰውብናል” ብለዋል፡፡
አባገዳዎቹ ጉዳዩን ከኦዳቡልቱም አባገዳዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በጥልቀት እንደተመለከቱትና “እውነቱ ተገኝቷል” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የሟች ቤተሰብ ሽምግልናውን ባለመቀበላቸው ምክንያት፣ የተገኘውን እውነት ለጊዜው ይፋ ሳያደርጉ ሂደቱን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አብራርተዋል።
🔴የሟች ቤተሰብ ተቃውሞ
በሌላ በኩል የሞዴል ቀነኒ አዱኛ አባት አቶ አዱኛ ዋቆ፤ የሽምግልና ሂደቱን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ “በቅድሚያ የልጄ ገዳይ ማን እንደሆነ ሳይታወቅ ካሳ (ጉማ) አንቀበልም” የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል።
አቶ አዱኛ አክለውም፤ “እነሱ (ሽምግሌዎቹ) የሚሉት ‘ደም በእጃችን አለ ግን አልገደልኩም’ ነው፤ እኛ ደግሞ የገደለ ሳይታወቅ እንዴት ጉማ እንበላለን?” በማለት ጠይቀዋል። አባትየው አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት፣ በቅድሚያ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እውነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ መሃላና ሌሎች ሂደቶች መግባት እንደሚቻል ጠቁመው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሂደቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ሞዴል ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤት ከ5ኛ ፎቅ ወድቃ ህይወቷ ማለፉ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ አርቲስት አንዱዓለም ጎሳ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም፤ አቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ክስ ባለመመሥረቱ ከሦስት ወራት እስር በኋላ በ50 ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ አይዘነጋም።