ሳይቃጠል በቅጠል፦ ነአምን ዘለቀ

ሳይቃጠል በቅጠል፦ ነአምን ዘለቀ

በጋራ ሀገራችን ላይ ያጠላውን የመበታተንና የህዝብ ለህዝብ እልቂት ለመቀልበስ የመፍትሄዎች አካል እንሁን!
በሀገር ውስጥ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ፣የአማራ፣የኦሮሞ፣የልዩ ልዩ የቋንቋና ባህል ማህበረሰቦችን ለምትወክሉ
ልሂቃንና ምሁራን፣ የሃይማኖትና የፓለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ በሀገር ውስጥና በዲያስፓራ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣
አክቲቪስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የማህበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች በሙሉ፦

ሰሞኑን በአገራችን በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊና ንጹሃን ወንድሞች፣
እህቶች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ አዛውንቶች ፣ ሕጻናት ሳይቀሩ፣ የሃይማኖት አገልጋዮች ጭምር በግፍ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣
ተፈናቅለዋል። አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችም ተቃጥለዋል። ብዙ ግፍ ተፈጽሟል። ሕይወታቸውን ላጡ ንጹሐን ዜጎች
ወገኖቼና ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመዶቻቸው በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እገልጻለሁ።
የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለየን ረቂቅ ሕሊናን፣ ርሕራሄን፣ ሰብአዊነት ነው። ከአራት አስር አመታት በላይ በተሰበኩ ፣ ላለፉት
በርካታ ወራት ደግሞ በተካረሩና ጥላቻን መሰረት ባደረጉ የተዛቡና ቁንጽል የታሪክና የፓለቲካ ትርክቶች ሳቢያ ለደረሰው እጅግ
አሳዛኝ ጥቃትና የኢትዮጵያውያን ሕይወት መቀጠፍ የራሳቸው ሚና እንደነበራቸው የሚያጠያይቅ አይደለም።
እነዚህን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊቶች የፈጸሙ ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፣ መንግስት እነዚህን ኢ-ሰብአዊ ወንጀል የፈጸሙ
ግለሰቦች በሕግ ፊት ማቅረብ አለበት።
ከጥቂት ወራት በፊት በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ሃሳቤን ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከአንዳንድ የኦሮሞና የአማራ፣የሕብረ
ብሔር ኢትዮጵያውያን ልሂቃን ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሚዲያዎችና ሶሻል ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የብሔርም የሕብረ
ብሔርም የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች ሲሰነዘሩ የቆዩ ትንኮሳዎች፣ ጠብ አጫሪ ተግባሮች፣ እንቅስቃሴዎች በልዩ ልዩ ማህበረስቦች
መካከል ለዘመናት የነበረውን ተጋምዶ፣ ትስስር፣ ትብብር፣ ፍቅር፣ ወልዶ ተዋልዶ አብሮ መኖር የነበረውን እንዳልነበር እያራከሰ
እያኮሰሰ የደረሰበትን አሳዣኝ ዝቅጠት ከንፈር እየመጠጥን ስንታዘብ ሰንብተናል። በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፣ እልህ
ተጋብተውም እንዱ እንዱን ለመብለጥ የቃላት ጦርነቶችና፣ ከሁሉም ጎራ የሚሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች፣ በሶሻል ሚዲያ የቃላት
ሰይፍ መማዘዝ ፣ ጥላቻን በሕዝብ መካከል መርጨት በስፋት ሲደረጉ የቆዩበት ሁኔታ፣ በስፋት በተሰራጩ የታሪክም የፓለቲካም
የተዛቡ ትርክቶች፣ እጅግ ሲጋነኑ የነበሩ ቁንጽል መረጃዎች፣ በሰፊው የተዛመቱ የፈጠራ ወሬዎችን ጨምሮ በማሕበረሰቡ
መካከል ፣ በተለይም ለዘመናት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በመገንባት ትልቅ ድርሻ ያላቸውን በኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች መካከል
ትልቅ ክፍተት እንዲፈጠር፣ የተወሰኑ የሕዝብ ክፍሎች ውስጥም ጥላቻ አየሰፋ፣ እየተጠናከረ እንዲመጣ አፍራሽ አሰተዋጽኦ
በማድረግ ከሰሞኑ ለተቀሰቀስው ከጥላቻ የመጣ ጥቃት፣ እጅግ አሳዛኝና እሰቃቂ ድርጊቶች ሚና እንደነበራቸው መታወቅ ያለበት
ይመስለኛል።
በተለይ በህዝብ ቁጥር ትልቅ በሆኑት ብሔሮች በአማራና በኦሮሞ መካከል ቅራኔን፣ ጥላቻን፣ ጥርጣሬን የሚያጠናክሩ
ትንኮሳዎች፣ በየመድረኩ፣ በጀርመን በእስራኤል ፣ በሌሎችም የዲያስፓራ የተቃውሞ ሰልፎች የተሰነዘሩ የጥላቻ፣ እንዱ ሌላውን
በንቀት የሚያንኳስሱ ቃላቶችና ድርጊቶች፣ የተሳሳቱና የተዛቡ ትርክቶች በስፋት ሲካሄዱ እንደነበር የሚካዱ ሊሆኑ አይችሉም።
ከዚህ አፍራሽና እጅግ ስስና ተሰባሪ የሆነውን የሀገሪቱን ሁኔታ፣ ተዋናዮቹ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከግለሰቦች ጀርባ የሚገኙ
የዶ/ር መረራ ጉዲናን አጠቃቀም ለመዋስ “የሚጋጩ ህልሞች” እንዲሁም ቅዠቶች፣ ሃሳቦችና ትርክቶች፣ በእነዚህ ትርክቶች
ዙሪያም የተሰለፉ ሚሊዮኖች መኖራቸውን እነዚህ ሚዲያዎች፣ ሶሻል ሚዲያዎችና፣ አክቲቪስቶችና የፓለቲካ ልሂቃን ከግምት
ውስጥ ሊያስገቡት አልቻሉም፣ ለማስገባትም አልተፈለገምም ነበር።የሴራ መልዕክቶች፣ ባልተጣሩና ለማጣራትም ምንም ጥረት
ባልተደረገባቸው በዜና መልክ የሚቀርቡ የፈጠራም የተጋነኑም ወሬዎች በተለይ ሀገር ውስጥ በመሬት ላይ ለሚገኘው የገፈቱ
ቀማሽ ሰላማዊ ሕዝብ የማይበጀው መሆኑ መረዳት ያስፈልግ ነበር።
ያደራጁት ሃይል በእጃቸው በሌለበት፣ አማራጭ ራዕይና ፕሮግራም ባላዘጋጁበት፣ አገርን ሊያረጋጋ ፣ ሕዝብን ከጥቃት ሊከላከል
የሚችል ወታደራዊና የጸጥታ ሃይሎችን ባላሰለጠኑበት፣ በማይመሩበት፣ ለዚህ ደግሞ መንግስታዊ አቅሙም፣ ችሎታም፣
ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ሆነ ቅደመ ዝግጅቶች ማንም ምንም በወጉ ባላሰቡበት፣ ባልተዘጋጁበት ሁኔታ በስልጣን ላይ የሚገኘውን
ብዙ ተግዳሮቶች የገጠመው ነገር ግን ለውጥን ለማምጣት ደፋ ቀና ሲል የቆየውን የለውጡን አመራር በከፍተኛ ርብርብ
ለማዋከብና ለመሸርሸር የተሄደበት ርቀት ትልቅ ታሪካዊ ስሕተት ይመስለኛል።

2 | P a g e
አገራችንን ኢትዮጵያን አጣብቆ የያዘውን መንግስታዊ ሃይል ቢዳከም ፣ እነዚህ የታሪክም የፓለቲካ መሰረት ያላቸው ልዩ ልዩ
ቅራኔዎች በየቦታው ቢፈነዱ፣ በህዝብ መካከል የእርስ በእርስ ግጭቶች ቢበራከቱ በብዙ አቅጣጫና ውስብስብ የብሄር ቅራኔዎች፣
ሌሎች ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፣ ማህበራሲ ችግሮች የተጠመደች አገራችንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዴት ሊወስዱ እንደሚችሉ
ከግምት ማስገባት አስፈላጊና ወሳኝ ይሆናል። እንደ ሀገር መኖር አለመኖር፣ እንደ ሀገር መቀጠል ወይንም አለመቀጠል
የምንችልበት ወይንም የማንችልበት የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ደርሰናል። በአንድ አካባቢ የሚጀመር እሳት፣ ወደ ሌላ አካባቢ
ሊዛመት እንደሚችል ወደ ሰደድ እሳት ሊያድግ፣ ሊሸጋገር ወደሚችል ደረጃ እንደሚደርስ ብዙ እውቀትና ማሰብ የሚፈልግ
አይመስለኝም፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተቀጣጠሉ፣ አድማሳቸው እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል፣ በአንድ
አካባቢ የተነሳ ግጭትና የግጭቱ ጥቃት ስለባ የሆኑ ወገኖች በሌላ አካባቢ በሚገኙ የአጥቂዎች ወገኖች ላይ የብቀላ ጥቃት፣የብቀላ
ብቀላ አድማሱ አየሰፋ፣ እየተዛመተ ፣ ማንም ምድራዊ ህይል ሊቆጣጠረው ወደማይችል ምድራዊ ሲኦል ሊለወጥ የማይችልበት
ምክንያት አይኖርም።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦
ዛሬ ትላንት አይደለም። ትላንት የሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ፣የአብዛኛው የዲያስፓራ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትኩረትና
የትግሉ ግብ ፣ የትግሉም ኢላማ በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሲዘወር በነበረ ግፈኛና ጨካኝ አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር
የሚካድ አይደለም። ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከባሌ ዶሎ እስከ ወሎ፣ ከሐረር እስከ ባሕር ዳር የኢትዮጵያ ህዝብ ከኦሮሞ እሰክ
አማራው፣ ከጋምቤላ እሰከ ሶማሌ፣ ከአዲስ አባባ እስከ አምቦ ትግሉ ከመንግስት ሃይሎች ፣ ከጨቋኝና ግፈኛ ገዥዎችና የመጨቆኛ
መስራሪያዎቻቸው ፣ ተቋማቶቻቸው ጋር ሲያፋፍም የነበረ፣ አለፍ ካለም የእነሱ ጥቂት ደጋፊዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር
የማይረሳ ነው።
ዛሬ ግን ቅራኔው፣ ግጭቱ፣ ጥላቻው የጎንዮሽ በሕዝብ መካከል ሆኖአል፣ በማህበረሰቦች መካከል ሆኗል። ትልቁ አደጋ ይህ
ከሰሞኑ የተከሰተውና ነጥሮ የወጣው እውነታ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑ የሚያጠራር፣ የሚያሻማ ሊሆን አይችልም። ዛሬ
ቅራኔው ለዘመናት አብረው በኖሩ ማህበረሰቦችና በሕዝብ መካከል መሆኑ ነው። ይህ እውነታ በስፋትና በጥልቀት በበርካታ
የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታይ እጅግ አደገኛ ሂደት መሆኑ ግልጽ አየሆነ ነው።
ይህን ልዩና እጅግ አስጊ ሁኔታ ለመለወጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ዘዴዎች፣ ብልሃቶች ይጠይቃል። መንግስታዊ የማድረግ አቅም
የመኖር አለመኖር ብቻ ሳይሆን የመንግስት እርምጃዎች፣ የመንግስት ድርጊቶች ሊፈጥሩ የሚችሉትን አሉታዊ የሆነ የአንድ
ወንም የሌላ ወገን የአጸፋ ምላሽ ለመቋቋም የሚያስችል፣ ያልተጠበቁ ትላልቅ አደጋዎች በህዝብ ላይ እንዳይደርሱም እስቀድሞ
ችግሮቹ በቀጥታ የሚመለከታቸውና ከችግሩ ጋር ተፋጠው የሚገኙ የመንግስት መሪዎችና ልዩ ልዩ የመንግስታዊ ተቋማት
ሃላፊዎች ሊደረግ ብቻ የሚችል የቢሆንስ ትንታኔም የሚያስፈልገው ነው። የመንግስት መሪዎች ወደ ስልጣን ያመጣቸው ፓርቲና
ሕዝብ ውስጥ ያላቸው ቅቡልነት፣ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ዝግጁነት፣ በየጊዜው የሚፈተሽ ዕቅድና ይህንኑ
የማስፈጸሚያ/የማድረግ አቅም የሚሰጡ ልዩ ልዩ የመሳሪያዎች ሳጥን በአግባቡና በብቃት ማዘጋጀትን የሚጠይቁ ናቸው።
ድርብርብና በየደረጃው የሚከናወኑ ተግባሮች ያሉበት ውስብስብ ሁኔታ ነው፡፡በመንግስት ብቻ ሳይሆን ፣ በአገር ሽማግሌዎች፣
በሃይማኖት አባቶች፣ በልሂቃን፣ በልዩ ልዩ ሃይሎችና ባለድርሻዎች በጋራም፣ በተናጠልም ስራዎችን ይጠይቃሉ።
የኢትዮጵያን ሰላምና፣ ደህንነት፣ መረጋጋት የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ይህን አስጊና አደገኛ በሕዝባችን ደህንነት፣ በሕዝባችን
አብሮነት፣ በኢትዮጵያ ሃገራዊ ህልውና ላይ የተደነቀረ ከባድ አደጋ ለመሻገር ከተፈለገ ይህን አደጋ ከሚያባብሱ፣ ከሚቀጣጥሉ
ቃላት፣ ቅስቀሳዎች፣ ቁንጽልና በቅጡ ያልታሰቡባቸው፣ ያልተጠኑም በርካታ የሀሰትም ወሬዎች ፣ የተዛቡና በምንም መልኩ
መቼም ሙሉና ሁለንተናዊ እይታን ሊሰጡ የማይችሉ ትርክቶች በሚዲያና በማህበራዊ ሚዲያዎች ከማሰራጨት መቆጠብ የግድ
ይሆናል። በምትኩ የሚዲያዎች ሚና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ መስጠት፣ ማሕበረሰቦች እንዲቀራረቡ የበኩላቸውን ሚና
መጫወት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡፡ግጭት ሳይሆን ውይይት፣ ቅራኔን ሳይሆን መግባባት እንዲመጣ ገንቢ ጥረቶች ማድረግ
የሁሉም የፓለቲካ ልሂቃንና የሚዲያዎች፡ በሀገር ቤትም በውጭ ሀገርም የሚገኙ የብሄርም የሕብረ ብሄሔርም አላማ ያነገቡ
አክቲቪስቶች ታሪካዊ ሃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይም እሳቱ የማይደርስባቸው፣ በእነሱም በቤተሰቦቻቸው፣
በዘመዶቻቸው ላይ ጭምር ሊደርስ የሚችል የማይመስላቸው በውጭም በሀገር ውስጥም የሚገኙ የየብሔሩ ልሂቃን፣
የየብሔሩና በሕብረ ብሔርም ኢትዮጵያዊነትና ዜግነት ፓለቲካ የተደራጁ አክቲቪስቶች ሁሉ ቆም ብለው ማሰብ የሚገባቸው
ወቅት አሁን መሆኑን በጥብቅ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
የሚቀጥለው እሳት ወደ ሰደድ እሳት እንዳያመራ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ለትላልቆቹ የፓለቲካ ልዩነቶች መፍትሄ ማፈላለግ
ያስፈልጋል ። የተጀመረው አዝጋሚና ብዙ ተግዳሮቶች የገጠመው የለውጥ ሂደት ከእናካቴው እንዳይቀለበስ ሁሉም የድርሻውን
ማበርከት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ያቆበቆቡ ፣ ይህን ሁኔታ ለመጠቀም ሰሞኑን በሀዘን

3 | P a g e
የተመለከትነውን ጥቃት በማጦዝ፣ በማራገብ ጮቤ የረገጡ ፣ ልዩ ልዩ ዘዴዎችንም በመጠቀም ከተለያዩ የፓለቲካም የሚዲያም
ተዋናዮች ጀርባም በመሆን ቅራኔዎችና ችግሮች እንዲሰፉ፣ እንዲባባሱ የእነማን ዘርፈ ብዙ ጥረት እንደሆነ የሚጠቁሙ በርካታ
መረጃዎች በየጊዜው እንደሚያሳዩ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ይመስለኛል። ክመሸጉበት ለማንሰራራት፣ ብሎም
የኢትዮጵያን ሃገረ መንግስት ማዕከል ዳግም ለመቆጣጠር ያላቸውን ቀቢጸ ተስፋ ዕውን ለማድረግ፣ የለመዱትንም ግፈኛ
መንግስታዊ ሽብርና መንግስታዊ ዘረፋ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ለማስቀጠል ሙከራቸውን ከማድረግ ወደ ኋላ
የማይሉ እኩይና ከታሪክ የማይማሩ ያረጁ ያፈጁ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የፓለቲካ አስተሳሰብ ጋር እራሳቸውን ማለማመድ፣
ካለፈው ወንጀሎቻቸውና ውድቀታቸው መማር የማይችሉ ድኩማን የፓለቲካ ድርጅች እንዳሉ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ ነው ብዬ እገምታለሁ።
እነዚ ህይሎች የራሳቸውን ጥቅምና ያጡትን የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት ከማየት በስቲያ ፣ በሕዝብ ላይ ጭነው ከነበሩት
የበላይነት ባሻገር ለሕዝብ መከራ፣ ለሰው ልጆች ጉስቁልና ቁብ የማይሰጣቸው ናቸው። የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ደምና
እንባ ለ27 አመታት አንደ ጎርፍ እንዲፈስ ያደረጉት እነዚህ የፓለቲካ ሀይሎች ይህን እኩይ አላማቸውን ለማሳካት የጋራ አገራችን
ኢትዮጵያ አገራዊ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ፈጽሞ የማይጨነቁበት መሆኑን ሲጀምሩም የተነሱበት የፓለቲካ አላማ፣ ታሪካቸው ፣
እስካሁንም የቀጠሉበት አንደበታቸው፣ የተካኑበት መሰሪነትና ተንኮል ያረጋግጣል። “እኛ የኢትዮጵያ አዳኞች ነን” በሚል
ሽፋንና ነገር ግን የማዕከላዊ መንግስትን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ቀቢጸ ተስፋቸው እሁንም በትዕቢትና በትምክሕት ተወጥረው
በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ትርምስ ጎዳና ሊያስገባ የሚችል እድል እንዳንሰጣቸው የኢትዮጵያ ህዝብ
ሁሉ ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት በጽኑ አምናለሁ።
የኢትዮጵያ ምድር ከጥንት ከሺ አመታት በፊት ዛሬ የሚገኙ ሕዝቦች ያልነበሩበት፣ አንዱ በአንድ ዘመን ከደቡብ ተነስቶ ሌሎችን
ማህበረሰቦች አስገብሮ መሬት ሲይዝ፣ በሌላ ዘመን ሌላው ይህኑ አጸፋ ሲያደርግ፣ ሲስፋፋ፣ በአመዛኙ ደግሞ የየብሔሩ ገዢዎች
፣ በአለም ላይ እንደነበሩ ገዥዎች ሁሉ የተደረጉ ሂደቶች ናቸው፡፡ ሌሎች የአለም ሃገሮች ከተመሰረቱበት የሀግሮች ምስተታ ሂደት
ምንም የሚለየው የለም። ባርያ ፈንጋዩና አስገባሪው ደግሞ የአንድ ብሔር አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ብቻም አልነበሩም። በልዩ ልዩ
የታሪክ ምእራፎች የየማህበረስቡ/ብሄሩ ንጉሶችና ገዢዎች፣ አስገባሪዎች ፣ ተስፋፊዎች በመሆን ተፈራርቀዋል። የልዩ ልዩ
ብሔሮች/ማህበሰቦች ገዢዎች ከመሃል ወደ ደቡብ ፣ከደቡባዊ ከምስራቃዊ ኢትዮጵያ ተነስቶ እስከ መሃላዊ የዛሬዋ ኢትዮጵያ
ብቻ ሳይሆን እስከ ሲሜናዊና ሰሜን ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዝመት በመስፋፋት ሲፈራረቁበት የቆዪበት የረጅም
ዘመናት ሂደት ነው። የረጅም ዘመናት ታሪካችን እያንዳንዱ ማህበረሰብና በየዘመኑ፣ በሰፊው የታሪካችን ምእራፎች የነበሩ
የብሔርም የሕብረ ብሔርም ገዥዎች በቀደሙት ዘመናት አጣሁዋቸው ያላቸውን መሬቶች ለማስመለስ ዳግም በሃይል ሲስፋፋ
የነበረበት ውጥንቅጥና አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ረጅምና ተጽፎ ያላለቀ፣ ተጽፎም ሊያልቅ የማይችል ፣ የብዙ ዘመናት
የመጥበብ ፣ የመስፋት ሂደቶችና ተደጋጋሚ ኡደቶች ብቻም አልነበሩም፡፡ የንግድ ልውውጥ፣ የማህበራዊ ግንኙነቶች፣ የቋንቋና
ባህል መወራርስና መዳቀል የነበሩበትም ሂደት ነበር። ለዳር ድንበርና ለሕዝብ ክብር ለኢትዮጵያ አገራዊ ግንባታ በኦሮሞም ፣
በአማራም ፣ በአፋር ፣ በትግሬ፣ በወላይታ ፣ጉራጌ በሌሎችም የቋንቋና የባህል ማህበረሰቦች ባፈሯቻቸው በመቶ ሺዎች
የሚቆጠሩ ሀገራዊ እርበኞች ፣ አንጸራቂ ጀብ ድ በፈጸሙ ፣ታላላቅ ጀግኖችና የጦር መሪዎች መስዋዕትነት የተገነባ ሕብረ ብሔራዊ
ኢትዮጵያ ማንነትና ሃገራዊነት የታሪክ ሂደትም ነው። ይህ ውስብስብ የታሪክ ሂደት በ150 አመት ታሪክ ትንሽ አጭር መነጽር
ሊታጠር ፣ሊገደብ የማይችል ሰፊ የዘመናት የታሪክ ባህርን በጭልፋ በሰፈረ ፣ እጅግ ቁንጽ የሆነ የነፍጠኛ የሰባሪ
የገባር/የአስገባሪ ትርክትና እንድምታ የማያይወክለው፣ የማይገልጸው ሰፊና ጥልቅ የሆኑ የታሪኮቻችን ገመዶችና ክሮች የልዩ
ልዩ ማህበረስቦች መስተጋብሮች፣ ግንኙነቶችና ፣ የሂደቶች ውጤት ነው።
ዋናው፣ ትልቁ ሃቅ ግን ከዚህም ከዚያም ወገን ማንም የታሪካችን ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ መረጃ እንኳን በዚህኛው በወዲያኛውም
ሕይወቱ ሊኖረው አይችልም። ታላላቆቹና በአለም ደረጃ የሚታወቁት የታሪክ ጸሐፊዎች እነ አርኖልድ ቶዬንቢ፣ ኤድዋርድ ጊበን፣
ዘመናዊና ትላልቅ ስም ያላቸው ኒያል ፊርግሰን ፣ ፈርናንድ ብራውዴል ፣ ሌሎችም ታዋቂ የታሪክ አጥኚዎች የሀገራቸውንም ሆነ
የአለምን ታሪክ በሚመለክት የጻፉዋቸው ሁሉንም የታሪክ ምዕራፎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ክንውኖች፣ ሁሉንም ታሪካዊ
መረጃዎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ሂደቶች አጣርተው በሙሉ ፣ ፍጹም በሆነ እውቀት/ዩኒቨርሳል የታሪክ ዘይቤም የታሪክ ሙሉ እይታ
ሊኖራቸው እንደማይችል የታወቀ ሃቅ ነው። የብዙ አገሮች ታላላቅ የታሪክ ጸሐፊዎች በእያንዳንዱ የታሪክ ምዕራፍ አስከ ዛሬ
የሚወዛገቡባቸው በርካታ የታሪክ ኩነቶች ፣ የታሪክ ትርጓሜዎች፣ የታሪክ ዘይቤዎች እንዳሉ ራሱ የኢትዮጵያን ታሪክ በራሳቸው
ልክ ለሚፈልጉት የፓለቲካ አጀንዳ ቀንጭበውና ቆንጽለው የሚያቀርቡ የየብሔሩ ልሂቃን የሚያጡት ሓቅም አይደለም።
እነዚህ አጨቃጫቂ ፣ አወዛጋቢ የሆኑት በሁሉም ወገን ቁንጽል የሆኑና ማንም በምንም መልኩ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ
እንደበርክታ የታሪክም የማህበራዊ ሳይንስ የመነጩ ጥናትችና ትርክቶች ሙሉ እይታ፣ ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ ግንዛቤ፣

እንደሌላቸው ይታወቃል። የተፈጥሮ ሳይንስ በተለይም ከአንስታይ የሬላቲቪትይ የፊዚክስ ቲዎሪ ግኝት በኋላ ሁሉን አዋቂና
ሁሉን ተንባይ ነኝ የሚለው ማንነቱ ላይ በደረሰብት ቀውስ ሳቢያ የሳይንሱ ማህበረሰብ የሚቀበለው በአመዛኙ ፍጹም የሆነ፣

ሙሉ የሆነ እውቀት፣ ዩኒቨርሳል የሆነ እርግጠኝነት፣ የትንበያ አቅምም እንደሌለ ነው። ሌሎች ታላላቅ የሳይንስ ፈላስፎች ኢ-
እርግጠኝነት (Uncertainty principle) የሚል ስያሜ የሰጡት የተፈጥሮ ሳይንስ ንጉስ የሆነው ፊዚክስ ተፈጥሮን ሙሉ

በሙሉ ፣ ሁሉን ለማወቅና የሚሆነውንም ለመተንበይ የማይችል፣ በእጅጉ ያለውን ውሱንነት ያጠናከሩ ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት
ዘርፎችም ከኢኮኖሚክስ እስከ የፓለቲካ ሳይንስ የእውቀት ዘርፎች ጠቅላይ ሊሆኑ፣ ሙሉና የወድፊቱንም በፍጹም እርግጠኝነት
ሊተነብዩ እንደማይችሉ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎች በተወስነ አውድ፣ በተወሰነ ካባቢ ውሱን ለሆነ ግንዛቤና እውቀት፣ ለውሱን
ችግሮች መፍቻ ዘይቤዎች/መሳሪያዎች ብቻ እንደሆኑ፣ የወደፊቱም የመተንብይም ሆነ ያልፈውን የታሪክም የማህበረሰብን
ውጥንቅጦች በሁለንተዊና ጠቅላይ/ዩኒቨርሳል በሆነ መልኩ ለማወቅ እንደማይቻል እንዱ ሌላውን ሲገለብጡ፣ የኖሩ ንደፈ
ሃሳቦች ፣ ጽንሰ ሃሳቦች ፣ ቲዎሪዎች፣ የአለም እይታዎች/ፓራዳይሞች፣ ልዩ ልዩ የማሀበረስባዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ፍልስፍናዎች
፣ እንዲሁም የዘይቤዎች/ሜተድስ።ሞዴልስ የትየለሌ መሆናቸው የሚያረጋግጡት ይህንንኑ ነው። በብዙች ዘንድ በዚህ ጉዳይ
ላይ ሰፊ ግንዛቤና መግባባት የተደረሰ ይመስለኛል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ልሂቃን በተለይ በፓለቲካው ትልቅ ሚና ያላችሁ የታሪክና የህብረተሰቡን ችግሮች ሁሉ በሚመለከት አለን
የምትሉት ግንዛቤ ውሱንነት መቀበል። ትህትና ብትህውትነት (humbleness and humility) እኛ ሁሉን እናውቅለታለን
ብለው ለሚገምቱት ህዝብና ማህበረሰብም የተሻለው ምልከታ ይመስለኛል ። ምክንያቱም ፍጹም እወቀት፣ ፍጹማዊ እውነት
አለኝ ለማለት በማይቻልበት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የተፈጥሮ ፣የታሪክ፣ የማህብረሰብም ሂደቶች፣ ጉራማይሌዎች፣ ጓዳ ጎድጓዳዎች፣
ጉራንጉሮች፣ ዥጉርጉር ሁኔታዎችና ሂደቶች የነበርን ህዝቦች በመሆናችን። የሰው ልጆች ህይወትም ሆነ የአለም ህዝቦች ታሪክ
አካል የሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ(ታሪኮች) ግራጫ ቀለም ያላቸውእንጂ ነጭና ጥቁር ባለመሆናቸው የኋላ ታሪኮቻችን፣ የሚጋጩ
ትርክቶች ያን ወይንም ይህን ቁንጽል የታሪክ ጠብታ ይዞ ሙሉ እውቀት ባለቤት ነኝ ፣በሞኖፖል እውቀት እኔ ጋር ብቻ የሚል
ስሜት ያላቸው የየብሄሩ ልሂቃን ቁንጽ የታሪክ ትርጉሞች/ትርክትን መሰረት አድርገው የሚሰነዘሩ ሽኩቻዎች የህዝብ፣
የማህበረሰብ ቅራኔዎች ፣ ጥላቻና ፣ ግጭቶች፣ ጥቃቶች መንሴም እየሆነ የመጣበት ይህ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ እሁን ላይ መቆም
ይገበዋል። ለአገርና ለሕዝብ የተሻለው፣ የሚበጀው መንገድም ይህ ይመስለኛል። ሁለተኛው አማራጭ ህዝብን ማጫረስ፣
ሀገርን ማፍረስ፣ ሁሉም በእሳት የሚጫወት ተዋናይ በሰደድ እሳቱ ወላፈን እራሱም ሆነ በምድር ላይ የሚገኙ የሚወዳቸውም
ሳይቀሩ የመለብለብ፣ የሚጠበስ ምድራዊ ገሃነም ብቻ ናቸው።
የኦሮሞም የአማራም ከዚያም የደቡባዊና የምስራቃዊ ኢትዮጵያን ፣ እንድሁም የኦሮሞን ታሪክ በአግባቡ አላካተተም ወይንም
አይወክልም የሚባለው የግዕዝ ስልጣኔ ታሪክ ፣ ሌላም ካለ ሁሉም ወገን የኔ የሚላቸው ትርክቶች፣ ልዩ ልዩ ታሪኮች ወይንም
የሚጣጣሙበት ወይንም የሚቀራረቡበት መንገዶችና ዘዴዎች መፈለግ። ወይንም ደግሞ ተመሳሳይ የታሪክ አረዳድ
ያልነበራቸው አገሮች ፣ የሚጋጩ ትርክቶች አገራዊ ትርምስ የፈጠሩባቸው የሌሎች ሀገሮችን ሕዝቦች ልምድ ቀስሞ ከሁሉም
የተውጣጣ፣ ይህንኑ የሚያጠና ባለሙያዎች የሚገኙበት ኮሚሽን የሚቋቋምበት ሁኔታ ቢመከር ምናልባት አንዱ የመፍትሄ
አካል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደተነሳው የአገራችን ትላልቅ የፓለቲካ ቅራኔዎች አንዱ ከአለፉ ታሪኮቻችን
የታሪክ አረዳድና አተረጓጎም ልዩነቶች፣ የሚጋጩ ትርክቶች ላይ የሚመነጩ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጠው
ይገባል እላለሁ።
ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት፣ ማንም ተሸናፊ የማይሆንበት በሀገሪቱ ዋና ዋና ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ተኮር ውይይቶች
በየደረጃው የሚደረጉበት ሁኔታዎች መፈለግ አስፈላጊ ይሆናል። ሁሉም ባለድርሻዎች አገሪቷን እሁን ላይ ከገጠማት የህልውና
አደጋ ለመታደግ ከለውጡ መሪዎች ጋር በመነጋገር ፣ በለውጡ መሪዎችም በኩል ጉልህ ድምጽ ያላቸውን ባለድርሻዎች፣
የየብሄሩን ልሂቃንና የፓለቲካ ሃይሎች ሁሉ ፍላጎታቸውን በግልጽ ወደ ጠረጴዛው እንዲያቀርቡ ፣ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ ሰጥቶ
የመቀበል፣ ብሎም ሀገራዊና ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንዲቻል መድረኮችን የማመቻቸት ጊዜው አሁን ነው የሚል
የሚል ሃሳብ አቀርባለሁ።
የሁሉም ዜጎችና የቋንቋና የባህል ማሕበሰቦች ጥቅምና መብቶች ያልተከበሩባት ኢትዮጵያ የማንም የየትኛውም ብቸኛ
ማህበረሰብ/ወይንም ብሔር መብት፣ ፍትህና ጥቅም ለዘለቄታው ሊከበርባት እይችልም። የአማራ ፣ የኦሮሞ፣ የሌሎም
ማህበሰቦች ልሂቃንና የፓለቲካ ሃይሎች ቆም ብለው የማንም የማትሆን አገር ሁላችንም ወደ ምድራዊ ሲኦል የሚወስድ መንገድ
ከመግፋት እጅግ የተሻለው አመራጭ ለሁሉም ጥቅም፣ ለሁሉም እኩልነት፣ መብቶች፣ ለሁሉም ድምጽና ክብር ፡ ለሁሉም
የምትመች ኢትዮጵያን እንድትሆን ተነጋግሮ፣ ተግባብቶ ፣ ፍኖተ ካርታውን፣ የጨዋታውን ህግ ፣ ሂደቱን ፣ የስነ መግባር ደንቡን
፣ ወዘተ የሚመለከቱ እንዲሁም ዋና ዋና ፓለቲካዊ ልዪነቶች ላይ ዉይይቶች በማድረግ፣ ወደ መግባባት ላይ ለመድረስ ማሰብ

5 | P a g e
ያለባቸው ጊዜ አሁን የመስለኛል። ይህ ጥሪ ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለሶማሌ፣ ለአፋር፣ ለትግራይ ለሌሎችም ማህበሰቦች ልሂቃን፣
የፓለቲካ ሃይሎች፣ እንዲሁም የሕብረ ብሔር የኢትዮጵያዊነት የዜግነት የፓለቲካ ሃይሎች በሙሉ ለህሊናም፣ ለታሪካችሁም
እጅግ የተሻለው አማራጭ መሆኑን በአንክሮ ማሰብ ወቅቱ አሁን ይመስለኛል።
በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ሕብረ ብሔር ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብቶችና ጥቅሞች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲስተናገድ፣
እንዲከበሩ ፣ እንዲረጋገጡ የሚያስችል ሂደት መጀመርም አለበት። የየትኛውም ብሔር የበላይነት/ ወይንም ሄጀመኒ፣
በየትኛውም አካባቢ ይህ የኔ ለእኔ ብሔር ብቻ ነው ሌላው ዜጋ መጤ ነው፣ ሰፋሪ ነው ወዘተ የሚሉ የተዛቡና ብዙ ሚሊዮን
ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ያደረጉ፣ ስጋትን፣ የነገን ተስፋ አለማየት ፣ ከሰሞኑ ደግሞ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች
ሕይወት ያስቀጠፉ አስተሳሰቦችና ስነ ልቦናዎች የሚለወጡበት ሁኔታ በቅጡ መታሰብ ፣ መፍትሔም ማግኘት አለባቸው።
በተጨማሪም ይሄ “የኔ ብሔር፣ ይሄ የኔ አካባቢ ብቻ ነው”፣ የሚሉ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ- ጸረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች “የኔ”
ለተባለውም ብሔር ሕዝብ ጥቅምንም መብቶችንም ለዘላቂው ሊያስከብርና ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአት
በሌለበት፣ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌሉዋቸው የፓለቲካ ስርአቶች በስመ ብሄር፣ ወይንም
በሀገራዊ ብሄርተኝነት ስም ወደ ስልጣን የመጡ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች ብሄሬ በሚሉት ህዝብ ላይ ያደረሱትን መከራ፣
ስቃይና፣ እልቂት በታሪክም አሁን ላይ በዘመናችንም ከበቂ በላይ ሁላችንም የታዘብን፣ ያየን ይመስለኛል።
በአንድ ሀገር ውስጥ ግማሹ የበኩር ልጅና አንደኛ ዜጋ ፣ ገሚሱ የአገሪቱ ሕዝብ ደግሞ የእንጀራ ልጅና ሁለተኛ ዜጋ ፣ ከዚያም
ወረድ ብሎ በስጋት በፍርሃት፣ ያለዋስትና እየኖረ የሚቀጥልባት ኢትዮጵያ እንደ እንድ የጋራ አገር፣ በጋራ አብሮ ለመኖር
ሊያዘልቁ የሚያስችሉ አይሆኑም ። ይህን እስከፊና ለ26 አመታት የተንሰራፋ፣ ዛሬም ሊደገም፣ ተጠናክሮ ሊቀጠልበት
የሚሞከርበት፣ ብዙ ሚሊዮኖች አማርኛ ተናጋሪ ይሁኑ እንጂ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታ፣ ከትግሬ፣ ከከንባታ፣ ጋሞ፣ ከሶማሌ
አፋር፣ ከሌሎችም ማሕበረሰቦች ቅይጥና ቅልቅል የሆኑ፣ ወይንም በስነ ልቦናም፣ በአመለካከትም፣ የትኛውም ብሔር ሳጥን
ውስጥ ሊገፉና ሊከተቱ የማይችሉ ፣ ነገር ግን ሁሉንም ብሔሮች/ማሕበረሰቦች የሚወዱ፣ አብሮ የኖሩ፣ አፍቅሮ፣ ተጋብቶና
ተዋልዶ፣ በልዩ ልዩ ማህበራዊና ሰዋዊ ገመዶች የተሳሰረ፣ በደም በአጥንት የተለሰነ የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የተገኙ
“ከአስገባሪነት”፣ “ከነፍጠኝነት፣ ከሰባሪነት” ጋር ምንም ግኙነት የሌላቸው፣ ከኢትዮጵያዊነት ሌላ ቤት የሌላቸው፣ ብዙ ሚሊዮን
ዜጎቻችን በአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ በሐረር፣ በድሬ ዳዋ፣ በባሌ፣ በአዳማ፣ በአሰላ ፣ በአዋሳ፣ በልዪ ልዪ ሌሎች የሀገሪቱ የከተማ፣
ከተማ ቀመስና የገጠር አካባቢዎች ሁሉ ሙሉ መበቶቻቸው፣ ደህነታቸው ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም
በኦሮሞ፣ በደቡብ በሌሎችም አካባቢዎች መከበር፣ መረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታዎች ፣ ውይይቶች፣ ድርድሮች ፣ መግባባቶች
መደረስ ይኖርበታል።
በሀገርም ውስጥ በውጭም የምትገኙ የምታውቁኝም የማታውቁኝም ወድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦
ታላቁ የአሜሪካን ፕሬዝደንት አብረሃም ሊንከን የአሜሪካ ጥቁ ር ሕዝቦችን ከባርነት ለማላቀቅ በተደረገው የደቡብ ባሪያ አሳዳሪ
ኮንፌደሬት ሰራዊትና የስሜኑ የአንድነት ሰራዊቶች ከዛሬ 160 አመታት በፊት ባድረጉት የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት
እንደተናገረው እርስ በእርሱ ተከፋፈለ ቤት ሊቆም/ሊዘልቅ አይችልም “A house divided against itself cannot
stand” ። አሁን እየታየ ባለው በህዝብ ውስጥ የሚገኝ ቅሬኔና ትላልቅ ህመሞችና ስንጥቆች ሳቢያ የሁላችንም የጋራ ቤት
የሆነችው ሀገረ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ህልውናዋ መቀጠል አይችልም። ፍትሃዊነትና ልከኝነትን (just and fair) ማዕከል
አድርገን አገራዊ የፓለቲካ ችግሮቻችንን ካልፈታን፣ ይህ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችንን መብት አልባና እንገት እስደፊ ያደረገ፣
እስከፊና አሳፋሪ ሁኔታ እንደ አገር አብሮ ለመኖር አያስችለንም፡፡ይህን አስከፊና ከሀገሪቱ ችግሮች አንዱ የሆነ አስተሳሰብና ሕጎች
ለመለወጥ ሂደቶች መጀመር አለባቸው። ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ስልጣን የተገደበበት፣ ሕዝብ በርካታ አማራጮች ቀርበውለት
በነጻ ርዕቱአዊ ምርጫ ሊወስን የሚችልበት የሕግ የበላይነትና ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች መድህን ሊሆን የሚችል ፌደራላዊም
ዴሞክራሲያዊም የሆነ የፓለቲካ ስርአት ለዘላቂው ለሁሉም የቋንቋና የባህል ማሕበሰቦች፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች
ሊበጅና ሊጠቅም የሚችለው። በአንድ ጎን በየአካባቢው የሚገኙ የማሕበረሰቦች የስልጣን ምንጭነት፣ የባህል ቋንቋቸው
እኩልነት የሚረጋገጥበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ መብቶች
የሚከበሩበት፣ የሚረጋገጡበት ምንትዮሽ ግብ ሊያጣጥም፣ ሊያስታርቅ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ፣ ሌሎች መሰል
አመራጮችንም ማፈላለግ የአገሪቱ የፓለቲካ ልሂቃንና የተደራጁ ሃይሎች በጥልቀት ሊያስቡበት የሚገባ እንገብጋቢና
ከቀዳሚዎቹ የፓለቲካ ችግሮቻችን አንዱ ይመስለኛል።
የ20ኛ ክፍለ ዘመ ን ታላቁ የስይንስ ጄኒ አልበርት አንስታይን ከእምሮዋዊ አቅምና እውቀት፣ የወደፊቱን የማለም ምናባዊ ህይል
የበለጠ ነው” “Imagination is more important than Knowledge” እንዳለው ወቅቱ እውቀት እለን የምትሉ ልሂቃን

6 | P a g e
ምናባዊ አቅማችሁን በመጠቀም የሀገችንን የፓለቲካ ችግሮችና ተግዳሮቶች በውይይት፣ በድርድር፣ ለመፍታት ማሰብን በረጅሙ
ማለምን ይጠይቃችሁሃል። ፓለቲካ የእድሎች ጥበብ ወይንም “Politics the Art of the possible” ጭምር ነው ይባላል።
ይህ አሻግሮ ማይትን፣ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም እድሎች፣ አደጋዎችን ወደ ጥሩ አጋጣሚዎች ለመለወጥ ምናባዊ እቅምን
መጠቀምንም የሚጠይቅም ጭምር ስለሆነ ይመስለኛል። ዊኒስን ቸርችል ታላቅ ከመሆን ጋር ታላቅ ሃፊነትነትም እብሮ ይመጣል፣
ትልቅ ዋጋም ያስከፍላል እንዳለው የብሄርና የህበረ ብሄር የፓለቲካ ልሂቃን የሀገራችን የፓለቲካ ሃይሎች ለሀገራዊ ስላም፣ ለህዝብ
መረጋጋት ፣ለፍትሃዊ የፓለቲካ ስርአት ምስረታ ፣ እናንም ትልቅ ለመሆን ለምትችሉበት ፣ በርእቱዊ ነጻ ምርጫ አማራጽ የፓለቲካ
ፕሮግራሞቻችሁን አቅርባችሁ ካሸነፋችሁ 105 ሚልዮን ህዝብ ለመምራት ለምትችሉበት ዴሞክራሲያዊ የፓለቲካ ስርአት በጋራ
መስርቱ። ቆምንለት ለምትሉት ብሄር/ብሄረሰብም ደህነትና ሰላም፣ ጥቅምና መብቶች ፣ እንዲሁ ለመላው ህዝብ፣ ለሁሉም
ኢትዮጵያውን ዜጎች፣ ለሁላችንም የጋራ ሃገር በታላቅ ሀላፊነት መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰን ብልህነትና አስተውሎ ነው።
በታሪክ ፊት፣ በህግም ፊት ፣ በሂሊናችሁም ተጠያቂ አያደርጋችሁም። በሰማይም እንዲሁ። ሀገር ከሌለ፣ ሀገር ውስጥ ሰላም
መረጋጋት ከጠፉ ስልጣንም ፣ ጥቅምም፣ ታላቅነትም፣ ማንም ምንም የሚያገኝበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል፣ ሁሉም
ሊጠፋፋ የሚችልበት ሀገራዊ ትርምስ ውስጥ እንደ ዋዛ ፈዛዛ ሊገባ እንደሚቻል በዛሬ ዘመን የተወለዱ የሊቢያን፣ የሶርያን፣
የመንን ህዝቦች መከራና ስቆቃ እያዩ ያደጉ ታዳጊ ወጣቶች እንኳን የሚገነዘቡት እውነታ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስበው እንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ሰሞኑን በተከሰተው የንጹሃን
ዚጎቻችን ሕይወት መቀጠፍ፣ መቁሰልና መፈናቀል እንደሚያሳዝነው አንድ ሰብአዊ ፍጡር፣ ለአማራ ወይንም ለኦሮሞ ብቻ
ሳይሆን ለሁሉም የቋንቋና የባሕል ማሕበረሰቦች፣ ዜጎች በፍትሕ፣በሕግ የበላይነት ፣ በማህበራዊ ፍትህ፣ በዴሞክራሲ ፌደራላዊ
የፓለቲካ ስርአት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን የበኩሉን አስተዋጽኦና ትግል እንዳደረገ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ
ለጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ እህመድ፣ ለም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፣ ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው
፣ ሌሎችም ለውጡን የመሩና በመምራት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ አመራሮች ይህን ጉዳይ በጥብቅ እንዲያስቡበት ከሀገሪቱ ልዩ
ልዩ ባለድርሻ አካላት፣ የብሔርም/ዘውግም ፣ የሕብረ ብሔራዊ የፓለቲካ አመለካከትና ፕሮግራም ያላቸው ልሂቃንና ተጽእኖ
ፈጣሪ ባለድርሻዎች ሁሉ በአግባቡ የሚሳተፉበት ብሄራዊ የውይይት፣ የምክክር መድረኮች ማመቻቸት ሰ-ሰአቱ የድረሰ
ይመስለኛል። መግባባትና እርቅ የሚደረስበት ፣ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሊያራምዱ የሚችሉ ፍኖተ ካርታ በሁሉም
ባለድርሻዎች ተሳትፎ ወደ ስምምነት የሚያደርሱ መድረኮች የማመቻቸት ሂደት እንዲጀመር የግሌን ሃሳብ እንደ እንድ
ኢትዮጵያዊ ለማቅረብ እወዳለሁ።
የአገራችንን ችግሮችና ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት በማዘጋጀት ላይ ያለሁትን የግሌን ሰፋ ያለ ምልከታ በቀጣይ አቀርባለሁ።
ፍትህ፣ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት፣ የሕዝብና የአገርን ጥቅም ማስቀደም በአገራችን እንዲሰፍን ፣ መቻቻልና አብሮ መኖር
እንዲለመልም ቸሩ አምላክ ይርዳን!!

ነአምን ዘለቀ
ቨርጂኒያ፡ አሜሪካ