ጽንፈኞችን ለሕግ ማስገዛት ካልቻሉ ዶ/ር አብይ ቢለቁ ይሻላል #ግርማካሳ

ሰሞኑን በአገራችን የመጀመሪያው ያልሆነ ዘግናኝና አንገት የሚያስደፋ የሽብር ተግባራት በዜጎች ላይ ተፈጽሟል፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድ 83 ኢትዮጵያዉያን ሕይወታቸው እንደተቀጠፈ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ራሱን ቄሮ ብሎ የሚጠራው ቡድን ፣ የጃዋር መሀመድን “ተከብቢያለሁ” ጩኸት ተከትሎ በዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ፣ ድብደባ፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችንና የእምንት ተቋማትን የማውደም፣ የማቃጠል ተግባር የፈጸመ ሲሆን፣ ፣ ዜጎች ራሳቸውን ለመመከት በወሰዱት እርምጃና በአንዳንድ አካባቢዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ ግጭት የተወሰኑት ቄሮዎች ተገድለዋል፡፡

በዶዶላ ፣ በሕመም ሲሰቃዩ የነበሩ፣ የ80 አመት አዛዉንት ነበሩ፡፡ አቶ ኃይሉ አማረ፡፡ አንገታቸው ታርዶ፣ ራሳቸው በድንጋይና በስለት ተፈጥፍጦ፣ አይናቸውን ወጥቶ፣ ምላሳቸው ተቆርጦ፣ አገጫቸው ተከፍሎ፣ቀኝ እጃቸውን ተቆርጦ፣ ሆዳቸውን በስለት ተቀድዶ…በዘግናኝ ሁኔታ ነበር የተገደሉት፡፡ በኦሮሞ ቄሮዎች፡፡

ዘምሼ ሲሳይ ትባል ነበር፡፡ እህታችን፡፡የሁለት ሕጻን እናት፡፡ ጡቷን ቆርጠውና አርደው ነበር የገደሏት፡፡

ከድረዳዋ ቀርብ ብላ ባለች የምስራቅ ሃረርጌ ዞን አካባቢ፣ ከነበረው ግርግር በመሸሽ ተደብቀው የነበሩ አንዲት እናትና ሴት ልጃቸው በቤታቸው እንዳሉ፣ በር ተዘግቶባቸው ፣ ቤታቸው ላይ እሳት በቄሮዎች ተለኩሶ ነው የተገደሉት፡፡

አሁንም በምስራቅ ሀረርጌ በሮዳ በሚባል ቦታ አቶ ደረጀ ኃይሉና አቶ ደመና የተባሉ በንግድ የሚተዳደሩ ሁለት ወንድማማቾች፣ የአቶ ደመና ባለቤት ወ/ሮ ወላንሳ ፍቅሬ በቄሮዎች ታርደዋል፡፡ በተለይም አቶ ደረጄ ለማምለጥ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቢገቡም፣ ፖሊስ ጣቢያዉን ሰብረው በመግባት፣ የኦሮሞ ክልል የአካባቢው ፖሊስ እየተመለከተ፣ በዱላ ቀጥቅጠው፣ ብልታቸውን ቆርጠው አፉቸው ውስጥ በመክተት ነበር አሰቃይተው የገደሏቸው፡፡ በፊታቸው ይሄ ሁሉ ሲፈጸም የኦሮሞ ክልል ፖሊስ ዝም ማለቱ፣ የክልሉ ፖሊሶች ዩኒፎርም የለበሱ ቈሮዎች ናቸው ለሚለው አባባል አንድ ማሳያ ነው፡፡

የጃዋር መሐመድን ጥሪ ሰምተው የጭካኔ ተግባር የፈጸሙ ቄሮዎች ብዙ ጥፋት የፈጸሙት በዋናነት ከሃያ የኦሮሞ ክልል ዞኖች በአራቱ ሲሆን ( ምእራብ አርሲ ፣ ባሌና ምስራቅና ምእራብ ሃረርጌ ዞኖች) እንደ ሁሩታና አሰላ ያሉ ከተሞች ባሉባት የአርሲ ዞን አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቃት ለመፈጸም ሞከረው ነበር፡፡ ሆኖም ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል በመቻላቸው እንደ ምእራብ አርሲና ባሌ ዞኖች እንደታየው ዜጎች ብዙ አልተገደሉም፡፡

በሸዋ የአዲስ አበባና የአዲስ አበባን ዙሪያ ዲሞግራፊ ለመቀየር በሚል፣ በኦሮሞ ክልል መንግስት ከሃረርጌ፣ ባሌና አርሲ መጥተው የሰፈሩ፣ በአካባቢው ባሉ ኦህዴድ ሃላፊዎች የተደራጁ፣ የሚደገፉና ጥበቃ የሚደረግላቸው ቄሮዎችም፣ የጃዋርን ጥሪ ተከትለው ብዙ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በናዝሬት፣ በደብረ ዘይት፣ በሞጆ፣ በዱከም፣ በሰበታ/ወለቴ እንዲሁም እንደ ጀሞ ባሉ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሜንጫና የተሳለ መሳሪያዎች በመያዝ ብዙ ሰዎችን ገድለዋል፤ አቁስለዋለዋል፡፤ ንብረትም አውድመዋል፡፡

ነዋሪነቱ በደብረ ዘይት የሆነ አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ እናቱ አማራ ሲሆኑ አባቱ ኦሮሞ ናቸው፡፡ “ወደ ቢሾፍቱ ስገባ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው የመጡ ቄሮዎች አስቆሙኝ፡፡ በእጃቸው ሜንጫና የተሳለ መሳሪያ ይዘዋል፡፡ በኦሮምኛ አናገርኳቸው፡፡ ጃዋርን አውቀዋለሁ አልኳቸው፡፡ ያኔ እለፍ ብለው አሳለፉኝ፡፡ ኦሮምኛ ባልናገር ኖሮ አልቆልኝ ነበር” ሲል ነው፣ ከአዲስ አበባ ወደ ቤቱ ሲመለስ ያጋጠመውን በፌስ ቡክ ገጹ የገለጸው፡፡

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገው ደግሞ፣ በአዳማ ቄሮዎች አንድ ወጣትን ያገኙታል፡፡ ተመስገን ቶሎሳ ይባላል፡፡ ኦሮሞ ነው፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነው፡፡ ተቀላቀለን አሉት፡፡ እምቢ ሲላቸው ደበደቡት፡፡ በስለት ቆራረጡት፡፡

በወለቴ/ሰበታ የሆነው ሌላ የሚሰቀጥጥ አሳዛኝ እልቂት ነበር፡፡ ወደ ስምንት የሚሆኑ በሰበታ ይኖሩ የነበሩ የጋሞ ወንድሞች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት መካከል የፕሮቴስታንት እምነት ሰባኪያን የነበሩ 2 ዜጎች ይገኙበታል። ከሁለቱ ወንጌላዊያን መካከል አንደኛው ቤተክርስትያን ውስጥ እያለ ድንገት በመጡ ቄሮዎች “አንገቱ ታርዶ” ሲሞት ሁለተኛው ከቤተክርስትያን ወደቤት ሲሄድ አግኝተዉት በተመሳሳይ የአገዳደል መንገድ ነበር የገደሉት፡፡

የጋሞ ሜዲያ ኔትዎርክ እንደዘገበው፣ ባለቤቷን በፊቷ ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በቄሮዎች የገደሉባት የሁለት መንታ ልጆች እናት ስለነበርወው ሁኔታ ይሄንን ብላለች፡

“ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ቄሮ መጣ እያሉ ሰዎች እየጮኹ ወደየቤታቸው መግባት ጀመሩ። እኛም ቤታችን ገብተን በር ዘግተን ተቀመጥን። ቄሮዎቹም እንደደረሱ የእኛ ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። እኛ ምንም አላሰብንም፤ ደነገጥን። ከዝያም አጥራችንን አፍርሰው ወደጊቢያችን እንደገቡ በመጀመርያ ስድብ መስደብ ጀመሩ። መሬቱም የኛ ነው፤ መንግስትም የኛ ነው እናንተ ጋሞዎች ኑ ውጡ አሉን። ከነርሱም መካከል ሁለቱ ቤት ገብተው እኔና ባለቤቴን ይዘውን ወጡ። ባለቤቴም ከቄሮዎቹ መካከል የሚያውቀውን አንድ ጋዲሳ የተባለ የሰፈር ልጅን ‘አንተ ጋዲሣ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር በእኛ ላይ ታደርጋለህ እባክህን ተው፤ ለነዚህ ህፃናት ስትል ተው ባክህ’ ይለዋል። እነርሱ ግን እንጨርሳለን፤ ገና እንጨርሳቹኋለን እያሉ ባለቤቴን በድንጋይ መደብደብ፣ በስለት መውጋት ጀመሩ። ባለቤቴ ብዙ ከደበደቡት በኋላ ሞተ። እሱ እንደሞተ እኔ መጨው ስጀምር ‘ለምን ትጮዄለሽ አፍሽን ዝጊ እያሉ እኔንም መምታት ጀመሩ። ከዝያንም የሰፈራችን ሰው 5 ሌትር ጅሪካን እና ክብሪት ሲሰጣቸው አየሁ። ‘ጨርሱ ካለቀ እኔ ጨምራለው’ አላቸው። ባመጡት ጋዝ ቤታችንን አቃጠሉ። አብዝቼ ብጮህም የደረሰልኝ የለም። የፖሊስ ልብስ የለበሱ ሰዎችን የባሌን አስክሬን አንሱልኝ ስላቸው እየሳቁ አይተውኝ ሄዱ።”

በአገራችን ያለው የዘር ፖለቲካ ዜጎች አጥበው እንዲያዩ ያደረገ ፖለቲካ ነው፡፡ ለስብእናትና ለዜግነት ቦታና ክብር የሚሰጥ ሳይሆን ለዘርና ለጎጥ ቦታ የሚሰጥ ነው፡፡

በዚህ ሳምንት የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት፣ ምን እንኳን አሁን አለም አቀፍ ሽፋንና ወገዛ ቢያስከትልም፣ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከሁለት አመት በፊት አሁን የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክና የኦሮሞ ጽንፈኞች ሲያራግቡት በነበረው ጸረ ሶማሌ ዘመቻ ሰለባ የሆኑ ኦሮሞዎች፣ በአወዳይ ከተማ በአንድ ቀን ብቻ ከስልሳ በላይ ሰላማዊ የሶማሌ ወገኖች አርደው መጨረሳቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከአንድ አመት በፊት በቡራዩ በተለይም የጋሞ ተወላጆች ላይ በቄሮዎች እጅግ አሰቃቂ ግድያና እልቂት ተፈጽሞ ነበር፡፡ ያንን እልቂት ተከትሎም እርቅ በሚል በጋሞ ሽማግሌዎችና በኦሮሞ አባገዳዎች መካከል ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ እርቁ የአንድ ቀን የፎቶና የፕሮፖጋንዳ ዜና ከመሆን ውጭ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ ይኸው በአመሩ ጋሞዎች እንደገሰና በኦሮሞ ቄሮዎች ተጨፈጨፉ፡፡

ከአንድ አመት በፊት በቡራዩ፣ ከሁለት አመት በፊት በአወዳይ እንዲሁም ሰሞኑን የተከሰተው ዘር፣ኃይማኖትና ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አሁን ባለው ህግ መንግስት፣ አሁን ባለው ዘር ተኮር ፖለቲካ እንደውም የበለጠ እየከፋ ይመጣል እንጂ በምንም መልኩ አይሻሻልም፡፡

ይሄ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ በአገራችን እየሆነ ያለው መንግስት አለ በተባለበት አገር ነው፡፡ ሆኖም መንግስት ቀዳሚ ስራውን መወጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ የዶ/ር አብይ አስተዳደር እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ ለሞቱት ፣ ለተገደሉት፣ ለተፈናቀሉት ተጠያቂ ነው፡፡ አገር ወደ ዚህ ደረጃ ልትደርስ እንደምትችል ብዙዎች አስጠንቅቀዋል፣ ጽፈዋል፡፡ ሆኖም አስተዳደሩ ከወዲሁ ችግሮች እንዳይከተሉ ማድረግ ባለመቻሉ ዜጎች እየሞቱ ነው፡፡

አሁን በአስቸኳይ መሰራት ያለበት የሚከተሉት ናቸው፡

1) አገርን ትልቅ አደጋ ላይ የጣለው የኦሮሞ ጽንፈኝነት እንደመሆኑ በኦሮሞ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የፌዴራል መከላከያ ሙሉ በሙሉ ከክልል እክሰ ቀበሌ ሕግን የማስክበር ስራ እንዲሰራ ማድረግ

2) የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ ያሉ የዘር ጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የሚትያሰራጩ የሜዱኢያ ተቋማትን መዝጋትና እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ለዜጎች መሞት ምክንያት የሆኑትን በአስቸኳይ ለፍርድ ማቅረብ

በቀጣይነት ችግሩን ከስር ለመንቀል ፣ ስር ነቀል ስራ መሰራት አለበት፡፡

በሕግ የዘር ፖለቲካ ካልታገደ፣  “ሀ” ወይም አንድ ብለው ተከባብረው፣ ዘርና ኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እንደ አገር መኖር የሚችሉበት ስርዓት መገንባት ካልጀመሩ፣  ከፍተኛ እልቂት ነው የሚሆነው፡፡ በዘር ተደራጅቶ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ መታገድ አለበት፡፡ ያ ብቻ አይደለም በዘር ላይ የተመሰረተውን የፌዴራል አወቃቀር መፍረስ አለበት፡፡ ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ኃይማኖታቸውና ዘራቸው ሳይጠየቅ መኖር፣ መስራት፣ መነገድ፣ መውጣት፣  መግባት፣ መመረጥ፣ መምረጥ መቻል አለባቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ማእዘናት ዶ/ር አብይ አህመድ ከብዙዎች ተማጽኖ እየቀረበላቸው ነው፡፡ ሆኖም እስከ አሁን ዜግችን በማረጋጋት ረገድ ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ በቃልም ሆነ በጽሁፍ የሰጧቸው መግለጫዎች እንኳን ሊጠቅሙ እንደውም ባይሰጡ ይሻል ነበር የሚያስብሎ መግለጫዎች ሆነው ነው የተገኙት፡፡ እነ ጃዋርን ለፍርድ አለማቅረባቸው  ብዙዎች ዶ/ር አብይ ራሳቸው ከነጃዋር ጋር አብረው የሚሰሩ ሳይሆኑ አልቀረም ብለው ወደ ማሰብ እየወሰዳቸው ነው፡፡

በኔ እይታ ዶ/ር አብይ በቶሎ ትልቅ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከኦሮሞ ጽንፈኞች ጋር ያላቸው ገመድ በጥሰው ከአብዝኝዐእ ሰላም ወዳድ የኦሮሞ ማህበረሰብ፣ ከአብዛኝዐው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሙ ይሻላቸዋል፡፡ከነ አቶ ለማ መገርሳ ጋር ያላቸው ጓደኝነት ይዟቸው መደረግ ያለበትን ማድረግ ካልቻሉ፣ መድፈር ካቃጣቸው ግን  እንደ አቶ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ  ስልጣቸውን ቢለቁ፣ እርሳቸው መስራት ያልቻሉትን ሊሰሩ ለሚችሉ ቢያስረክቡ ጥሩ ነው፡፡