ብሄራዊ የውይይትና የመግባባት መድረኮች አስፈላጊነት – ነአምን ዘለቀ

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦
በኢትዮጵያ ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ እንድሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መዳረሻ ባለድርሻዎች፣ የፓለቲካ ልሂቃን፣ የብሄርም የህብረብሄር የፓለቲካ ሃይሎች የሚሳተፉበት የሚመክሩበት ብሄራዊ ውይይትና የመግባባት መድረኮች አስፈላጊነት (ይህ ማለት የሽግግር መንግስት ማለት አይደለም) በተከታታይ ከቀረቡት የቀጠለ

ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት፣ ማንም ተሸናፊ የማይሆንበት በሀገሪቱ ዋና ዋና ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ተኮር ውይይቶች በየደረጃው የሚደረጉበት ሁኔታዎች መፈለግ አስፈላጊ ይሆናል። ሁሉም ባለድርሻዎች አገሪቷን እሁን ላይ ከገጠማት የህልውና አደጋ ለመታደግ ከለውጡ መሪዎች ጋር በመነጋገር ፣ በለውጡ መሪዎችም በኩል ጉልህ ድምጽ ያላቸውን ባለድርሻዎች፣ የየብሄሩን ልሂቃንና የፓለቲካ ሃይሎች ሁሉ ፍላጎታቸውን በግልጽ ወደ ጠረጴዛው እንዲያቀርቡ ፣ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ ሰጥቶ የመቀበል፣ ብሎም ሀገራዊና ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንዲቻል መድረኮችን የማመቻቸት ጊዜው አሁን ነው የሚል የሚል ሃሳብ አቀርባለሁ።

የሁሉም ዜጎችና የቋንቋና የባህል ማሕበሰቦች ጥቅምና መብቶች ያልተከበሩባት ኢትዮጵያ የማንም የየትኛውም ብቸኛ ማህበረሰብ/ወይንም ብሔር መብት፣ ፍትህና ጥቅም ለዘለቄታው ሊከበርባት እይችልም። የአማራ ፣ የኦሮሞ፣ የሌሎም ማህበሰቦች ልሂቃንና የፓለቲካ ሃይሎች ቆም ብለው የማንም የማትሆን አገር ሁላችንም ወደ ምድራዊ ሲኦል የሚወስድ መንገድ ከመግፋት እጅግ የተሻለው አመራጭ ለሁሉም ጥቅም፣ ለሁሉም እኩልነት፣ መብቶች፣ ለሁሉም ድምጽና ክብር ፡ ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እንድትሆን ተነጋግሮ፣ ተግባብቶ ፣ ፍኖተ ካርታውን፣ የጨዋታውን ህግ ፣ ሂደቱን ፣ የስነ መግባር ደንቡን ፣ ወዘተ የሚመለከቱ እንዲሁም ዋና ዋና ፓለቲካዊ ልዪነቶች ላይ ዉይይቶች በማድረግ፣ ወደ መግባባት ላይ ለመድረስ ማሰብ ያለባቸው ጊዜ አሁን የመስለኛል። ይህ ጥሪ ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለሶማሌ፣ ለአፋር፣ ለትግራይ ለሌሎችም ማህበሰቦች ልሂቃን፣ የፓለቲካ ሃይሎች፣ እንዲሁም የሕብረ ብሔር የኢትዮጵያዊነት የዜግነት የፓለቲካ ሃይሎች በሙሉ ለህሊናም፣ ለታሪካችሁም እጅግ የተሻለው አማራጭ መሆኑን በአንክሮ ማሰብ ወቅቱ አሁን ይመስለኛል።

በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ሕብረ ብሔር ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብቶችና ጥቅሞች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲስተናገድ፣ እንዲከበሩ ፣ እንዲረጋገጡ የሚያስችል ሂደት መጀመርም አለበት። የየትኛውም ብሔር የበላይነት/ ወይንም ሄጀመኒ፣ በየትኛውም አካባቢ ይህ የኔ ለእኔ ብሔር ብቻ ነው ሌላው ዜጋ መጤ ነው፣ ሰፋሪ ነው ወዘተ የሚሉ የተዛቡና ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ያደረጉ፣ ስጋትን፣ የነገን ተስፋ አለማየት ፣ ከሰሞኑ ደግሞ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሕይወት ያስቀጠፉ አስተሳሰቦችና ስነ ልቦናዎች የሚለወጡበት ሁኔታ በቅጡ መታሰብ ፣ መፍትሔም ማግኘት አለባቸው። በተጨማሪም ይሄ “የኔ ብሔር፣ ይሄ የኔ አካባቢ ብቻ ነው”፣ የሚሉ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ- ጸረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች “የኔ” ለተባለውም ብሔር ሕዝብ ጥቅምንም መብቶችንም ለዘላቂው ሊያስከብርና ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሌለበት፣ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌሉዋቸው የፓለቲካ ስርአቶች በስመ ብሄር፣ ወይንም በሀገራዊ ብሄርተኝነት ስም ወደ ስልጣን የመጡ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች ብሄሬ በሚሉት ህዝብ ላይ ያደረሱትን መከራ፣ ስቃይና፣ እልቂት በታሪክም አሁን ላይ በዘመናችንም ከበቂ በላይ ሁላችንም የታዘብን፣ ያየን ይመስለኛል።

በአንድ ሀገር ውስጥ ግማሹ የበኩር ልጅና አንደኛ ዜጋ ፣ ገሚሱ የአገሪቱ ሕዝብ ደግሞ የእንጀራ ልጅና ሁለተኛ ዜጋ ፣ ከዚያም ወረድ ብሎ በስጋት በፍርሃት፣ ያለዋስትና እየኖረ የሚቀጥልባት ኢትዮጵያ እንደ እንድ የጋራ አገር፣ በጋራ አብሮ ለመኖር ሊያዘልቁ የሚያስችሉ አይሆኑም ። ይህን እስከፊና ለ26 አመታት የተንሰራፋ፣ ዛሬም ሊደገም፣ ተጠናክሮ ሊቀጠልበት የሚሞከርበት፣ ብዙ ሚሊዮኖች አማርኛ ተናጋሪ ይሁኑ እንጂ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታ፣ ከትግሬ፣ ከከንባታ፣ ጋሞ፣ ከሶማሌ አፋር፣ ከሌሎችም ማሕበረሰቦች ቅይጥና ቅልቅል የሆኑ፣ ወይንም በስነ ልቦናም፣ በአመለካከትም፣ የትኛውም ብሔር ሳጥን ውስጥ ሊገፉና ሊከተቱ የማይችሉ ፣ ነገር ግን ሁሉንም ብሔሮች/ማሕበረሰቦች የሚወዱ፣ አብሮ የኖሩ፣ አፍቅሮ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ፣ በልዩ ልዩ ማህበራዊና ሰዋዊ ገመዶች የተሳሰረ፣ በደም በአጥንት የተለሰነ የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የተገኙ “ከአስገባሪነት”፣ “ከነፍጠኝነት፣ ከሰባሪነት” ጋር ምንም ግኙነት የሌላቸው፣ ከኢትዮጵያዊነት ሌላ ቤት የሌላቸው፣ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችን በአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ በሐረር፣ በድሬ ዳዋ፣ በባሌ፣ በአዳማ፣ በአሰላ ፣ በአዋሳ፣ በልዪ ልዪ ሌሎች የሀገሪቱ የከተማ፣ ከተማ ቀመስና የገጠር አካባቢዎች ሁሉ ሙሉ መበቶቻቸው፣ ደህነታቸው ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሞ፣ በደቡብ በሌሎችም አካባቢዎች መከበር፣ መረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታዎች ፣ ውይይቶች፣ ድርድሮች ፣ መግባባቶች መደረስ ይኖርበታል።

በሀገርም ውስጥ በውጭም የምትገኙ የምታውቁኝም የማታውቁኝም ወድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦

ታላቁ የአሜሪካን ፕሬዝደንት አብረሃም ሊንከን የአሜሪካ ጥቁ ር ሕዝቦችን ከባርነት ለማላቀቅ በተደረገው የደቡብ ባሪያ አሳዳሪ ኮንፌደሬት ሰራዊትና የስሜኑ የአንድነት ሰራዊቶች ከዛሬ 160 አመታት በፊት ባድረጉት የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት እንደተናገረው እርስ በእርሱ ተከፋፈለ ቤት ሊቆም/ሊዘልቅ አይችልም “A house divided against itself cannot stand” ። አሁን እየታየ ባለው በህዝብ ውስጥ የሚገኝ ቅሬኔና ትላልቅ ህመሞችና ስንጥቆች ሳቢያ የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችው ሀገረ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ህልውናዋ መቀጠል አይችልም። ፍትሃዊነትና ልከኝነትን (just and fair) ማዕከል አድርገን አገራዊ የፓለቲካ ችግሮቻችንን ካልፈታን፣ ይህ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችንን መብት አልባና እንገት እስደፊ ያደረገ፣ እስከፊና አሳፋሪ ሁኔታ እንደ አገር አብሮ ለመኖር አያስችለንም፡፡ይህን አስከፊና ከሀገሪቱ ችግሮች አንዱ የሆነ አስተሳሰብና ሕጎች ለመለወጥ ሂደቶች መጀመር አለባቸው። ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ስልጣን የተገደበበት፣ ሕዝብ በርካታ አማራጮች ቀርበውለት በነጻ ርዕቱአዊ ምርጫ ሊወስን የሚችልበት የሕግ የበላይነትና ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች መድህን ሊሆን የሚችል ፌደራላዊም ዴሞክራሲያዊም የሆነ የፓለቲካ ስርአት ለዘላቂው ለሁሉም የቋንቋና የባህል ማሕበሰቦች፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሊበጅና ሊጠቅም የሚችለው። በአንድ ጎን በየአካባቢው የሚገኙ የማሕበረሰቦች የስልጣን ምንጭነት፣ የባህል ቋንቋቸው እኩልነት የሚረጋገጥበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ መብቶች የሚከበሩበት፣ የሚረጋገጡበት ምንትዮሽ ግብ ሊያጣጥም፣ ሊያስታርቅ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ፣ ሌሎች መሰል አመራጮችንም ማፈላለግ የአገሪቱ የፓለቲካ ልሂቃንና የተደራጁ ሃይሎች በጥልቀት ሊያስቡበት የሚገባ እንገብጋቢና ከቀዳሚዎቹ የፓለቲካ ችግሮቻችን አንዱ ይመስለኛል።

የ20ኛ ክፍለ ዘመ ን ታላቁ የስይንስ ጄኒ አልበርት አንስታይን ከእምሮዋዊ አቅምና እውቀት፣ የወደፊቱን የማለም ምናባዊ ህይል የበለጠ ነው” “Imagination is more important than Knowledge” እንዳለው ወቅቱ እውቀት እለን የምትሉ ልሂቃን ምናባዊ አቅማችሁን በመጠቀም የሀገችንን የፓለቲካ ችግሮችና ተግዳሮቶች በውይይት፣ በድርድር፣ ለመፍታት ማሰብን በረጅሙ ማለምን ይጠይቃችሁሃል። ፓለቲካ የእድሎች ጥበብ ወይንም “Politics the Art of the possible” ጭምር ነው ይባላል። ይህ አሻግሮ ማይትን፣ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም እድሎች፣ አደጋዎችን ወደ ጥሩ አጋጣሚዎች ለመለወጥ ምናባዊ እቅምን መጠቀምንም የሚጠይቅም ጭምር ስለሆነ ይመስለኛል። ዊኒስን ቸርችል ታላቅ ከመሆን ጋር ታላቅ ሃፊነትነትም እብሮ ይመጣል፣ ትልቅ ዋጋም ያስከፍላል እንዳለው የብሄርና የህበረ ብሄር የፓለቲካ ልሂቃን የሀገራችን የፓለቲካ ሃይሎች ለሀገራዊ ስላም፣ ለህዝብ መረጋጋት ፣ለፍትሃዊ የፓለቲካ ስርአት ምስረታ ፣ እናንም ትልቅ ለመሆን ለምትችሉበት ፣ በርእቱዊ ነጻ ምርጫ አማራጽ የፓለቲካ ፕሮግራሞቻችሁን አቅርባችሁ ካሸነፋችሁ 105 ሚልዮን ህዝብ ለመምራት ለምትችሉበት ዴሞክራሲያዊ የፓለቲካ ስርአት በጋራ መስርቱ። ቆምንለት ለምትሉት ብሄር/ብሄረሰብም ደህነትና ሰላም፣ ጥቅምና መብቶች ፣ እንዲሁ ለመላው ህዝብ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውን ዜጎች፣ ለሁላችንም የጋራ ሃገር በታላቅ ሀላፊነት መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰን ብልህነትና አስተውሎ ነው። በታሪክ ፊት፣ በህግም ፊት ፣ በሂሊናችሁም ተጠያቂ አያደርጋችሁም። በሰማይም እንዲሁ። ሀገር ከሌለ፣ ሀገር ውስጥ ሰላም መረጋጋት ከጠፉ ስልጣንም ፣ ጥቅምም፣ ታላቅነትም፣ ማንም ምንም የሚያገኝበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል፣ ሁሉም ሊጠፋፋ የሚችልበት ሀገራዊ ትርምስ ውስጥ እንደ ዋዛ ፈዛዛ ሊገባ እንደሚቻል በዛሬ ዘመን የተወለዱ የሊቢያን፣ የሶርያን፣ የመንን ህዝቦች መከራና ስቆቃ እያዩ ያደጉ ታዳጊ ወጣቶች እንኳን የሚገነዘቡት እውነታ ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስበው እንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ሰሞኑን በተከሰተው የንጹሃን ዚጎቻችን ሕይወት መቀጠፍ፣ መቁሰልና መፈናቀል እንደሚያሳዝነው አንድ ሰብአዊ ፍጡር፣ ለአማራ ወይንም ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የቋንቋና የባሕል ማሕበረሰቦች፣ ዜጎች በፍትሕ፣በሕግ የበላይነት ፣ በማህበራዊ ፍትህ፣ በዴሞክራሲ ፌደራላዊ የፓለቲካ ስርአት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን የበኩሉን አስተዋጽኦና ትግል እንዳደረገ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ እህመድ፣ ለም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፣ ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ ሌሎችም ለውጡን የመሩና በመምራት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ አመራሮች ይህን ጉዳይ በጥብቅ እንዲያስቡበት ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት፣ የብሔርም/ዘውግም ፣ የሕብረ ብሔራዊ የፓለቲካ አመለካከትና ፕሮግራም ያላቸው ልሂቃንና ተጽእኖ ፈጣሪ ባለድርሻዎች ሁሉ በአግባቡ የሚሳተፉበት ብሄራዊ የውይይት፣ የምክክር መድረኮች ማመቻቸት ሰ-ሰአቱ የድረሰ ይመስለኛል። መግባባትና እርቅ የሚደረስበት ፣ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሊያራምዱ የሚችሉ ፍኖተ ካርታ በሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ወደ ስምምነት የሚያደርሱ መድረኮች የማመቻቸት ሂደት እንዲጀመር የግሌን ሃሳብ እንደ
እንድ ኢትዮጵያዊ ለማቅረብ እወዳለሁ።

የአገራችንን ችግሮችና ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት በማዘጋጀት ላይ ያለሁትን የግሌን ሰፋ ያለ ምልከታ በቀጣይ አቀርባለሁ። ፍትህ፣ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት፣ የሕዝብና የአገርን ጥቅም ማስቀደም በአገራችን እንዲሰፍን ፣ መቻቻልና አብሮ መኖር እንዲለመልም ቸሩ አምላክ ይርዳን!!

ነአምን ዘለቀ
ቨርጂኒያ፡ አሜሪካ