በቅርቡ በመታወቂያ ዋስ ከእሥር የተፈቱ 75 የኅሊና እሥረኞች መግለጫ ሊሰጡ ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በቅርቡ በመታወቂያ-ዋስ ከእሥር ከተፈቱ ከመቶ በላይ እሥረኞች ውስጥ፣ ከአዲስ አበባና ከክልሎች የተሰባሰቡ 75 የሚሆኑ የኅሊና እሥረኞች፣ ነገ ጠዋት መግለጫ ሊሰጡ ነው፡፡

ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ፣ ከሶር አምባ ሆቴል ፊት-ለፊት በሚገኘው ባልደራስ ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫው ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በመግለጫው፤ የኅሊና እሥረኞች ስለ-ታሰሩለት ኹነት፣ ስለ-ፖሊስ የምርመራ ሂደት፣ ስለ-ፍትሕ ሥርዓቱ፣ ስለ-እሥር ኹኔታ እና ስለ-ሰብዓዊ መብት አያያዝ በተጨባጭ የተመለከቱትን ይናገራሉ ተብሏል፡፡

ከእሥር የተፈቱት የኅሊና እሥረኞች ቀደም ሲል የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ፣ መምህራን፣ የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች፣ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች መሆናቸውን ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ለኢትዮ-ኦንላይን አስታውቋል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውም በዋናነት ለጋዜጠኞች፣ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ሠራተኞች፣ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ለአክቲቪስቶች መዘጋጀቱን የነገረን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት አማርኛ ቋንቋ ማድመጥ የሚችሉ ወኪሎቻቸውን እንዲልኩ አሳስበናቸዋል ብሏል- ለዘጋቢያችን፡፡

በእለቱ- እንደ ከዚህ በፊቱ፣ ሊረብሹንና ሊበጠብጡን የሚመጡ ቡድኖች ካሉ፣ ለፖሊስ የሕግ ከለላ እንጠይቃለን ሲል የገለጸው እስክንድር ነጋ፣ በሰለጠነ መንገድ በንግግር ሃሳባቸውን የሚገልጹ ከሆነ ግን፣ እኛን ስላልመሰሉና የእኛን ሃሳብ ስላልደገፉ ብቻ እኛ አንቃወማቸውም፤ አናገላቸውም፤ ይህ ነው ስልጡኑ መንገድ፤

ሆኖም ግን፣ በቡድን ተደራጅተው እናጠቃለን ካሉ ግን፣ ራሳችንን የመከላከል መብታችንን እንጠቀማለን፤ ለዚህም ሕግ በማስከበር ሂደት ፖሊስ ይተባበረናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብሏል፡፡

በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲሰ አበባ እና በባህርዳር ‹‹መፈንቅለ መሥተዳድር›› በተባለው ግጭት ታስረው የተፈቱ የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች የነበሩ ዜጎች፣ ስለተፈጠረው ኹኔታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሃቁን እንዲረዳ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣሉ ሲል በቅርቡ ከእስር የተለቀቀው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ለኢትዮ-ኦንላይን ተናገሯል፡፡

ከሰኔ 15 ቀን ሀገራዊ ኹነት ጋር በተያያዘ፣ 108 ዜጎች ጋር አብሮ መታሰሩን የተናገረው አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ ሌሎች 22 እስረኞች ጋር ባለፈው ሳምንት በመታወቂያ ዋስ መፈታታቸውን ገልጿል፡፡

Source ኢትዮ-ኦንላይን