በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሄዱ የተነገራቸውና የቀሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገለጹ፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሄዱ በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የተነገራቸውና የቀሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

(አብመድ) የትግራይ ክልል መንግሥት ‹‹በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ሳላለ ተማሪዎችን አልክም›› በማለት መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በመግለጫው መሠረትም ‹ትግራይ ክልል በሚገኙ ዮኒቨርሰቲዎች በተለያዩ መርሀ ግብሮች ትማራላችሁ› እንደተባሉ የገለጹ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ሳይሄዱ ቀርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቃል በተገባላቸው መሠረት ተግባራዊ አለመሆኑን ተከትሎ ለእንግልት መዳረጋቸውንና ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን በስልክ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ በዚህም አዲስ እና ነባር ተማሪዎች ለችግር ተጋልጠዋል፤ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡


በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች ግንቦት 2011 ዓ.ም በተፈጠረ የሠላም መደፍረስ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደነበር በስልክ ነግረውናል፡፡ በወቅቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ቢነግራቸውም መፍትሔ ሳያገኙ ከአምስት ወራት በላይ ቆይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዕጣ ፈንታቸው ችግር ላይ መውደቁንም ነው የተናገሩት። በዚህ ወቅትም የመንግሥትን ምላሽ የሚጠባበቁና ተስፋ በመቁረጥ የራሳቸውን አማራጭ የወሰኑ ተማሪዎች መኖራቸውን ተማሪዎቹ ነግረውናል፡፡

በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ያለው የዓሲምባ ዴምክራሲያዊ ፖርቲ (ዓዴፓ) አስተባባሪ አቶ ዶሪ አስገዶም በበኩላቸው ተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ለመሄድ ጊዜው በማለፉ ምክንያት እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ዶሪ ገለጻ ተማሪዎች ለጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘታቸው ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቢያስቡም መንግሥት አግዷቸዋል፡፡ በግላቸው እንዳይማሩ አቅም የሌላቸው በርካታ ተማሪዎች ስላሉ በሕይወታቸው ላይ የተጋረጠው ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ‹‹የትግራይ ክልል መንግሥትም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ ዓዴፖ በአፅንኦት ይጠይቃል›› በማለትም አሳስበዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ነባር የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች ግንቦት ወር ላይ ተቀብሎ የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ፈተናቸውን እንዲወስዱ እንደሚያደርግና እስከዚያው ግን በራሳቸው እያጠኑ እንዲቆዩ አሳስቧል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶክተር) ለአብመድ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው መተዳደሪያ ሕግ መሠረት ከሁለት በላይ ፈተናዎችን ያልተፈተነ ተማሪ በሚቀጥለው ዓመት ተፈትኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የአማራ ክልልን ጨምሮ በ2011 ዓ.ም ግንቦት ላይ ፈተናቸውን አቋርጠው የነበሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጅ ተማሪዎችም በተያዘው ዓመት ግንቦት ወር ፈተና ይወስዳሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ለመቀበል መዘጋጀቱንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በተያዘው የትምህርት ዘመን በአዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመደቡ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች 60 የሚሆኑ ነበሩ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉት ግን 27 ብቻ ናቸው›› ብለዋል፡፡ የቅበላ ጊዜው እስከ መስከረም 29/2012 ዓ.ም ድረስ ቢሆንም በተለያዩ ምክንቶች ዘግይተው የነበሩ ተማሪዎችን እስከ ጥቅምት 19/2012 ዓ.ም ድረስ መቀበሉን የገለጹት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር ዳይሬክተር ገብሩ ታደሰ (ዶክተር) ናቸው፡፡

ዶክተር ታፈረ መላኩ እንዳስታወቁት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ዩኒቨርሲቲው ያልገቡ ተማሪዎች ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ማመልከት ይኖርባቸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አዲስ ምደባ ሊያደርግላቸው አለበለዚያም ደግሞ ዩኒቨርሲቲው እንዲቀበላቸው ሊወስን እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

አብመድ ከትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ጥረት አድርጓል፤ ነገር ግን ሥራ ላይ እንደሆኑ በጽሑፍ መልዕክት ከማሳወቅ በቀር ስልክ ሊያነሱ አልቻሉም፤ ምላሽ ለመስጠት በቻሉበት ጊዜ ሐሳባቸውን የምናቀርብ ይሆናል፡፡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ቀጠሮ ካስያዙን በኋላ ስልክ ባለማንሳታቸው ለጊዜው አልተሳካም፤ ደጋግመን በመጠየቅ ምላሽ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፡፡