ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን ለእንግልት ዳርጓቸዋል ተባለ

ኢትዮ ኤፍ ኤም : የሲዳማ ዞን ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ለማስፈጸም ወደ ቦታው ያቀኑ አስፈጻሚዎች በሐዋሳ እየተንገላቱ መሆኑን ተናገሩ።

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን ህዝበ ውሳኔው ደግሞ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።

ህዝበ ውሳኔውን በበላይነት የሚያስፈፅመው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ6ሺህ የሚልቁ የምርጫ አስፈጻሚዎችምን ትላንት ወደ ሀዋሳ ከተማና የሲዳማ ወረዳዎች ልኳል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም ተመልምለው ወደ ሀዋሳ ከተላኩት የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሰማው ከ400 የሚልቁ አስፈጻሚዎች አሁንም በሀዋሳ ከተማ እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡

አንድም የሚያናግረን ሰው አጥተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ምላሽ የሚሰጠን እና የምናናግረው አንድም ሰው የለም ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ብንደውል የስራ ሀላፊዎቹ ስልካችን ዘግተዋል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙንኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በበኩላቸው የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ምደባን ዛሬ እናጠናቅቃለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አስፈጻሚዎቹ ያቀረቡት ቅሬታ በተለይም ከክፍያ እና ማረፊያ ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ ተነጋግረን በመፍታት ላይ እንደሚገኙም ሶሊያና ተናግረዋል።

የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደነገሩን በእኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ዝግጅት አድርገናል እንደተባለው የአስጻሚነት ቦታቸውን ያላወቁ ከ400 የሚልቁ ወጣቶችን አግኝተን አናግረናል ፡፡

እኛ መመደብ ስለማንችል ለሚመለከተው የምርጫ ቦርድ ነገሩን አሳውቀናል እስከዛው ግን የሀዋሳ ከተማ አስተዳዳርና የሲዳማ ዞን ቁርስ እና ምሳ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሯሯጥን ነው ብለውናል፡፡

ይህ እንዴት ተፈጠረ ለሚለው ግን የስራው ባለቤት እኛ ሳንሆን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው ብለዋል አስተዳዳሪው፡፡

በህዝበ ውሳኔው የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞን በሚገኙ 66 ወረዳዎች እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች ለመራጭነት ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚገመት አቶ ደስታ ነግረውናል፡፡

የመራጮች ምዝገባ በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን ወረዳዎች በሚገኙ 598 ቀበሌዎች በ1ሺህ 692 የምርጫ ጣቢያዎች ይካሄዳል፡፡