በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና መፈናቀሎች ራስን በምግብ መቻል ላይ ተጽዕኖ አሳርፈዋል ተባለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ያንን ተከትሎ የሚመጡት መፈናቀሎች ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል ባስቀመጠችው ውጥን ላይ  ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት በግጭት ምክንያት አርሶ አደሮች ከማምረት ስራቸው ከመስተጓጎላቸው ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ለሌላ ስራ ማዋል የሚገባውን በጀት ለእርዳታ በማዋሉ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል ብለዋል።

ከሰሞኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል በቀረበለት ጥያቄ መሰረት በሁለት ቦታዎች እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ምትኩ ተናግረዋል። መስሪያ ቤታቸው በዶዶላ ለ3366 ሰዎች፣ በሰበታ ደግሞ ለ1100 ሰዎች እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ ያብራሩት ኮሚሽነሩ “በሌሎች ቦታዎች ጥያቄዎች አልቀረቡልንም” ብለዋል። ለተፈናቃዮች እየቀረበ የሚገኘው እርዳታ “የህግ የበላይነትን በማስከበር ዜጎች ወደ ቀደመ ቦታቸው እስኪመለሱ ባሉበት ይቀጥላል” ሲሉም አስረድተዋል።

Karte Dodola Ethipia AM በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 7.8 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የእለት ደራሽ እርዳታ እንደሚቀርብላቸው የጠቀሱት ኮሚሽነር ምትኩ የፌደራል መንግስት በየአመቱ ለእርዳታ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ረሃብ የለም” የሚሉት አቶ ምትኩ “ረሃብ የሚመጣው ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ  ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለተረጂዎች ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎች በመንግስት በኩል እየቀረበ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በድርቅ በየ10 አመቱ ስትጠቃ እንደነበር የገለጹት ኮሚሽነሩ አሁን ግን ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ በየአመቱ እየተከሰተ መሆኑን አመልክተዋል። “ሃገሪቱ በዚህ ሁኔታ ልትቀጥል አይገባም” ያሉት አቶ ምትኩ “እርዳታ እያቀረብን ስለማንቀጥል የተሻለ አሰራር በመዘርጋት ችግሩን ለመከላከል መጣር ይኖርብናል” ብለዋል።
ረሃብን ማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምዕተ አመቱ የልማት ግብ ውስጥ ከተካተቱ እቅዶች አንዱ ነው። ኮሚሽነር ምትኩ የተሳተፉበት፤ ይህንኑ ለማሳካት የሚረዳ አለም አቀፍ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተደርጓል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።