የኤርትራ መንግሥት ሲአይኤ መፈንቅለ መንግሥት ሞሳድ ስም ማጥፋት ሞክረውብኛል ሲል ከሰሰ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBC Amharic : የኤርትራ መንግሥት ባወጣው ያልተለመደ መግለጫ ሲአይኤን በመፈንቅለ መንግሥት ሽረባ ይከሳል። የእስራኤል የስለለ መረብ ሞሳድንም ስም በማጥፋት ተባብሯል ይላል።

የኤርትራ መንግሥት ይህን ስኢረ መንግሥት ተሸርቦብኝ ነበር የሚለው በፈረንጆች 2011 ላይ ነው። ይህንኑ የተመለከተ ሁነኛ ምሥጢራዊ መረጃ እጄ ገብቷል ብሏል።

ምስጢራዊው የመፈንቅለ መንግሥት ሴራው በኤርትራ ውስጥ ልክ እንደ “አረቡ ጸደይ” ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞና አመጽ የማስነሳት ጥንስስ ነበረበትም ብሏል።

ይህ በትግርኛ ቋንቋ ዛሬ አርብ የተሰራጨው የኤርትራ መንግሥት መግለጫ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራውን ለመጎንጎን በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተሰብስበው ነበር ያላቸውን ተቋማትና ግለሰቦች በስም ሳይቀር ይዘረዝራል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ኤርትራዊያንን በገፍ እንዲሰደዱ የማሳለጥ ሥራ እንዲሰራ በሲአይኤ ይታዘዝ ነበር ይላል።

‘ሴረኞቹ’ የኤርትራ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላትም አገራቸውን ጥለው እንዲኮበልሉ ያባብሏቸው ነበር ሲልም ይከሳል።

በ2009 በኬንያ ተሳትፎ ያደረገው የኤርትራ እግር ብሔራዊ ቡድን ከፊል አባላት ወደ አገር ቤት ለመመለስ አሻፈረኝ ማለታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ደግሞ አራት የብሔራዊ ቡድን አባላት በኡጋንዳ በተመሳሳይ ጥገኝነት ጠይቀው እንደሚገኙና ለደህንነታቸው በመስጋት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የድብቅ ኑሮ እንደሚኖሩ መዘገባችን ይታወሳል።

የዛሬው መግለጫ በስም የሚጠቅሳቸው ‘የመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾች’ አመጽ ከተቀሰቀሰ በኋላ ልክ ጋዳፊ ላይ እንዳደረጉት ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ሲያብሰለስሉ ነበር ይላል።

የእስራኤሉ ሞሳድ በበኩሉ የኤርትራ መንግሥት ከመካከለኛው ምሥራቅ ከሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖች ጋር እንደሚሰራ የሚገልጹ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ተሳትፎ ማድረጉን ያወሳል።

የኤርትራ ወጣቶችን የማስኮብለል ተደጋጋሚ ሴራ ነበር የሚለው መግለጫው፤የኤርትራ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ኤርትራዊያንን በሕገወጥ ሰው ማስተላለፍ ሥራ እጃቸውን አስገብተዋል ሲል በተቀነባበረ መልኩ በሐሰት ይከስ የነበረው ሞሳድ ነው ይላል።

የኤርትራ መንግሥት ይፋ ባደረገው ‘ምሥጢራዊ’ ሰነድ ከተጠቀሱት ጉዳዮች መሐል የሚከተለው ሐሳብ ይገኝበታል።

“በኤርትራ የመንግሥት ለውጥ የሚሻ እንቅስቃሴ መጠበቅ ከንቱ ህልም ነው። ስለሆነም፤ የኤርትራን መንግሥት ለማስወገድ፡ የአገሪቱን ወታደራዊ ባህሪ ጠንቅቆ የሚያውቅ የውጭ ኃይል መጠቀም ይኖርብናል። ይህንን የሚያሟላ ደግሞ የ’ወያኔ’ ሥርዓተ ነው።” ይላል።

ይኸው ሰነድ አያይዞም፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ መንግሥትን ወታደራዊ አቋም በሚመለከት ያቀረበልን ጥናት ተጨባጭና በአጭር ግዜ ለውጥ ለማምጣት ተስፋ ሰጪ ነው” ካለ በኋላ ‘አትቸኩሉ’ ስለተባሉ እንጂ፤ [እ.ኢ.አ] ከ1998 ጦርነት በኋላ በድጋሚ ጦርነት ለመክፈት ፈልገው ነበር። የኤርትራን መንግሥት ለመገልበጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አጋሮቹ ሙሉ ድጋፍ አግኝተው ነበር”ሲል ያትታል።

ሰነዱን ጠቅሶ መግለጫው “…ጎን ለጎን ደግሞ በናይሮቢ የቀጠርነው ቄስ፡ ኢትዮጵያን ኤርትራን አንድነት እንዲሰብክ ሥራው ጀምሯል። ይሄ ደግሞ በ’ፍሪዶም ሃውስ’ የሚደጎም ሆኖ፡ ገና ከአሁኑ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል።”ሲል የግለሰቡን ማንነት በስም ሳይጠቀስ ያልፈዋል።

የኤርትራ መንግሥት ይህን መግለጫ ባልተለመደ መልኩ ለምን በዚህ ሰዓት ማውጣት እንደፈለገ ግልጽ አይደለም። በጉዳዩ ላይ የአሜሪካና የእስራኤል መንግሥታትን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ሙከራ ፍሬ አላፈራም።