የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በስም ያልተጠቀሱ አካላትን ለግጭቱ መባባስ ተጠያቂ አድርጓል።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBC Amharic : በአንድ ጭብጥ ላይ ብቻ ያተኮረው የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከሰሞኑ በኦሮሚያ፣ ሐረሪ ክልሎችና እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶች፣ መፈናቀልና ጥቃቶች ዙርያ 78 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪ ጽሕፈት ቤትን ወክለው መግለጫውን የሰጡት ቢልለኔ ስዩም ከግጭቱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 409 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ብለዋል። የተጠርጣሪዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የወጣው መግለጫ የሟቾቹን ቁጥር 67 እንደሆነ የሚገልጽ ነበር።

ቢልለኔ ስዩም ግጭቱ የሃይማኖትና የብሔር ገጽታ እንደነበረው አውስተው ለግጭቱ መባባስ በስም ያልጠቀሷቸው አካላትን ተጠያቂ አድርገዋል። እርሳቸው በስም ያልጠቀሷቸው እነዚህ አካላት አሁን እየተደረገ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ይፈልጋሉ ሲሉም ከሰዋል።

እነዚህ ኃይሎች አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ተቀባይነት ማሳጣት የሚሹና በአገሪቱ ፍርሃት እንዲረብብ ፍላጎቱ የነበራቸው ናቸው፤ እንደ ቢልለኔ ገለጻ። በመግለጫቸው እነዚህ በስም ያልተጠቀሱት አካላት አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል፤ አባብሰውታልም ብለዋል።

ግጭቱ የገዢው ፓርቲ አሁን ለመዋሃድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የመጣ አጸፋዊ ምላሽ እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል።

ቢልለኔ ስዩም ከጋዜጠኞች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መሀል “ጀዋር መሐመድ ጠባቂዎቼ ሊነሱ ነበር ባለበት ምሽት በትክክል የሆነው ምንድነው?” የሚል ይገኝበታል። ከዚህ ቀደም በዚህ ረገድ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ መግለጫዎች ከፌዴራል መንግሥትና ከኦሮሚያ ክልል መውጣታቸው የሚታወስ ነው።

ቢልለኔ ስዩም ሲመልሱ በዚያ ምሽት ስለሆነው ነገር በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ስለተሰጠ እርሳቸው አሁን የሚጨምሩት እንደሌለ ተናግረዋል። እርስ በርስ የሚጣረሱ መግለጫዎች ይወጡ እንደነበረ ግን እርሳቸውም መታዘባቸውን አውስተዋል። ይህም የሆነው ምናልባት በተለያየ ፍጥነት መረጃዎች መውጣታቸው የፈጠረው ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ተጠርጣሪዎቹን በተመለከተ በመንግስት በኩል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ ፍላጎት ይኖራል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ቢልለኔ አሁን ያለው ምርመራ ሂደት ላይ ስለሆነ እሱ የሚኖረውን ውጤት አይተን የሚያስፈልግ ከሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል ብለዋል።