የኢህአዴግ ውህደት እና የህወሓት “አጥፍቶ-መጥፋት”

(ስዩም ተሾመ)

ባለፉት 45 አመታት ህወሓት የአቅም እንጂ የአቋም ለውጥ አላደረገም። እንደ ኢዲዩና ኢህአፓ ካሉ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ቀርቶ እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ኢ/ር ግደይ ዘርዓፂዮን ካሉ የድርጅቱ መስራቾች ጋር የነበረውን የሃሳብ ልዩነት በሰላም መፍታት አልቻለም። ጠፍጥፎ ከሰራቸው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ሆነ ራሳቸው ጠፍጥፈው ከሰሩት ኢህአዴግ ጋር ያላቸውን የአቋም ልዩነት በውይይትና ድርድር ለመፍታት አልሞከሩም። በአጠቃላይ ህወሓቶች የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያለውን ግለሰብ፣ አመራር ወይም ቡድን በእስር፣ ስደት ወይም ሞት ደብዛውን ከማጥፋት ባለፈ ሌላ ዘዴ ወይም መፍትሄ አያውቁም። ኢህአዴግ ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ የውህደት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ መሆናቸው ዘንድሮ ውህደቱን ከመቃወም አላገዳቸውም።

እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን ካየነው የህወሓትን አቋምና አመለካከት መረዳትና መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው። የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ሆኖ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር፣ በጠላትነት የፈረጀውን ህዝብ ለመምራት የሚጥር፣ በከባድ ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበት ያስመለሰውን ሉዓላዊ መሬት ለወራሪው ኃይል አሳልፎ የሚሰጥ፣ የራሱን ወደብ ለጎረቤት ሀገር አሳልፎ ሰጥቶ በውድ ዋጋ የሚከራይ፣ ሐዋሳ ላይ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ የመረጠውን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሳይውል-ሳያድር በጠላትነት የሚፈርጅ፣ አሁን ደግሞ ላለፉት 30 አመታት ሲጠይቅ የነበረውን የኢህአዴግ ውህደት የህልውና አደጋ ነው በሚል አምርሮ የሚቃወም ነው። በዚህ መሰረት የህወሓት አቋምና ውሳኔ ፍፁም የተደበላለቀና እርስ-በእርስ የተጠላለፈ እንደመሆኑ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት አቋምና አመለካከቱን ማወቅ ሆነ መገመት አስቸጋሪ ነው።

እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የሌለው ቡድንን መቃወም ሆነ መደገፍ ትልቅ አደጋ አለው። በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ህወሓት ያለ የፖለቲካ ቡድን ፍፁም ጨቋኝና ጨካኝ እንደመሆኑ መጠን እንኳን መቃወም የተለየ ሃሳብና አመለካከት በራሱ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል። በሌላ በኩል ይህን ቡድን በማንኛውም መደገፍ ወይም በዝምታ መተባበር ሀገርና ህዝብን ለከፋ ጉዳት ውድቀት ይዳርጋል። በመሆኑም እንዲህ ያለ ቡድንን መደገፍ ሆነ መቃወም ከባድ አጣብቂኝ ነው። በዚህ ምክንያት ህወሓት/ኢህአዴግን ለመቃወም ሀገር ጥሎ መሰደድ የግድ ነበር። በሀገር ውስጥ የሚኖር ሰው ደግሞ ራሱን ከጥቃትና አደጋ መከላከል የሚችለው ህወሓት/ኢህአዴግን መቀላቀል ሲችል ነው። ባለፉት አመታት በተግባር እንደታየው ሀገር ውስጥ ሆነው የተለየ ሃሳብና አመለካከት የነበራቸው ዜጎች ለእስራት፣ ሞትና እንግልት ተዳርገዋል።
በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ ቀጥተኛ የሆነ የመፍረስ አደጋ ሲደቀንባት በሀገር ውስጥና ውጪ የሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖች ቅንጅት በመፍጠር የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ጥረት ጀመሩ። በመጀመሪያ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲሉ አሊያም ከውስጥ ሆኖ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት የነበራቸው የኢህአዴግ አመራሮች የአቋም ለውጥ ለማድረግ ተገደዱ። እነዚህ አመራሮች የሚወክሉት ህዝብ እንጂ የህወሓት አገልጋይ አለመሆናቸውን በይፋ መግለፅ ጀምሩ። በመቀጠል የሚመሩትን የኢህአዴግ አባል ድርጅት አመራርነት በመያዝ ከህወሓት ተላላኪነትና አገልጋይነት ነፃ አወጡ። በመጨረሻም ህወሓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አማካኝነት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ የነበረው የስልጣን የበላይነት አሳጡት።

ህወሓት በፌደራል መንግስት ላይ የነበረውን የስልጣን የበላይነት የጣው በመጋቢት 2010 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል። ከዚያ በኋላ ባለው አንድ አመት ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢ የብሔር ግጭትና ብጥብጥ በማስነሳት ወደ ስልጣን ተመልሶ ለመምጣት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማድረግን ጨምሮ በአብዲ ኢሌ አማካኝነት የሶማሌ ክልልን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ሞክሯል። በቤኒሻንጉል ግሙዝ ክልል እና በምዕራብ ኦሮሚያ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖችን እንዲቋቋሙ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ህገ መንግስቱን እና የገዢው ፓርቲ አደረጃጀትን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል።

ህወሓት ኢትዮጵያን በብሔር ግጭት ለማተራመስና ለማፍረስ የዘረጋው ስርዓትና አደረጃጀት በሕገ መንግስትና የሕግ የበላይነት ስም ጥበቃና ከለላ ይደረግለታል። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና አመራሮች እንደ ቀድሞ የህወሓት አገልጋዮችና መገልገያዎች እስካልሆኑ ድረስ ኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ ተጋርጦባታል። በዚህ መሰረት ህወሓት ቀድሞ የነበረውን የስልጣንና ኢኮኖሚ የበላይነት መልሶ ማረጋገጥ ካልቻለ ኢትዮጵያ እንደ ሶቬት ህብረት እና ዮጎዝላቪያ ትበታተናለች። ከዚህ በተጨማሪ በፌደራል መንግስቱና ክልሎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ብሔር፥ ብሔረሰቦች መካክል ማቆሚያ የሌለው የእርስ በእርስ ጦርነትና ዕልቂነት ይከሰታል።

በእርግጥ ይህ የፀሓፋ ስጋትና ግምት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ህወሓት መጋቢት 2011 ዓ.ም ወይን በተሰኘው የድርጅቱ ልሳን ላይ ባወጣው ፅሁፍ ከገፅ 13 – 22 እና ከገፅ 29 – 33 በዝርዝር የተገለፀ ንድፈ ሃሳብ ነው። በፅሁፉ መጨረሻ ክፍል ከገፅ 38 – 43 ዝርዝር የአጥፍቶ መጥፋት መርሃ ግብር የተዘጋጀት ዕቅድ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን የማተራመስና የማፍረስ ጉዳይ ከሕገ መንግስትና የፓርቲ አደረጃጀት ባለፈ በንድፈ ሃሳብ የተደገፈ እና የአፈፃፀም መርሃ ግብር የተዘጋጀለት ተግባር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ለብዙ አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በብሔር ግጭት የማተራመስና የማፍረስ ዓላማ እንዳለው ሲገለፅ የነበረ ቢሆንም ለብዙዎች ይህንን አምኖ መቀበል ያስቸግራል። ምክንያቱም አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚመራውን ህዝብ በግጭትና ሁከት የማተራመስ፣ እንዲሁም የሚያስተዳድረውን ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ከዚያ ይልቅ እንዲህ ያሉ ጅምላ ፍረጃ ስርዓቱን የሚቃወሙ ኃይሎች ለፖለቲካ ፍጆታና ንቅናቄ የሚናገሩት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ ህወሓት ህወሓት ከስልጣን በተወገደ በተወገደ ማግስት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተግባር እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ነገር ቆሞ ብሎ ሊያስብበት ይገባል።

ህወሓት ከፌደራል ስልጣን በተወገደ አንድ አመት ውስጥ መጋቢት 2011 ላይ ወይን በተሰኘው የድርጅቱ ልሳን ላይ “በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የተዋሃደ ፓርቲ ጥያቄ ለምን?” በሚል ርዕስ ያወጣው ፅሁፍ ከማንኛውም በላይ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ ያሳያል። በእርግጥ ለብዙዎቻችን ግራ የሚገባ ቢሆንም ህወሓት በበላይነት የማይገዛውን ህዝብ በብሔር ግጭትና አለመረጋጋት ለማተራመስ፣ እሱ እንደፈለገው የማይዘርፋትን ኢትዮጵያ ለመበታተን የሚያስችል ንድፈ ሃሳብና ዕቅድ አዘጋጅቷል። “የኢህአዴግ አሰላለፍ፣ ተልእኮ፣ ማሕበራዊ መሰረትና መለያዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ኢህአዴግ ራሱን ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጥርናፍ አላቅቆ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተባለ የአፈናና ዘረፋ ቀንበርን ከህዝቡ ጫንቃ ላይ አውርዶ ከጣለ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ብትንትኗ እንደሚወጣ ይገልፃል። ይህን ደግሞ መጋቢት 2011 ዓ.ም በወጣው የወይን መፅሔት ገፅ 13 ላይ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-“ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ከተሸከማቸው ተልእኮዎች አኳያ ሲታይ በአገራችን በጣም መሰረታዊና ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሃላፊነት የተሸከመ ድርጅት ነው፡፡ ለመሰረታዊው ተልእኮ ድልም ትንሹ ሞተር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከቆየችበት የብሄር ጭቆና አላቆ በሱ ፈንታ በእኩልነትና በፍላጐት ላይ የተመሰረተ አንድነት በማምጣት ከመበታተንና መተላለቅ ሊያድናት የሚቻለው ዓለማና ተልእኮ የኢህአዴግ ነው፡፡ የኢህአዴግ ዓላማና ተልእኮ ከሌለ ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ ከሌለ ደግሞ መበታተን የግድ ነው፡፡ የኢህአዴግ ተልእኮ ይህን ያህል የአገር መድህን የሆነ ዓላማ የተሸከመ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ የኢህአዴግ ዓላማና ተልእኮ የኢትዮጵያን ህዝቦች መፃኢ ዕጣ ፈንታ በመወሰን ያለው ድርሻ ተኪ የሌለው ነው።”በእርግጥ ይህ ህወሓት መቀሌ ከገባ በኋላ የነደፈው ስልት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ላለፉት 27 አመታት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ሲመራበት የነበረ መርህ እንደሆነ ተገልጿል። ወይን መፅሔት “የኢህአዴግ ዓላማና ተልእኮ በዓለም ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የተለየ መሆኑና በአገራችን ያልነበረ ስር ነቀል አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በማምጣት አዲስ ስርኣት ለመገንባት ሲንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት እንደሆነ” የአብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ምንነት በሚለውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ ይገልፃል።

ከላይ በተገለፀው መሰረት የኢህአዴግ ዓላማና ተልዕኮ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በተለየ መልኩ የሀገርን ህልውና እና የህዝቦችን መፃኢ ዕድል የሚወስን ነው። እንደ ህወሓት አገላለፅ ኢትዮጵያን ከመበታተንና ህዝቦቿን ከመተላለቅ ሊያድናት የሚችል ብቸኛው ፓርቲ ኢህአዴግ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ሊኖር የሚችለው ኢህአዴግ ሲኖር ብቻ እንደሆነ መጠን የሀገሪቱ አንድነት እና የህዝቡ ህልውና በአንድ ድርጅት መኖርና አለመኖር የሚወሰን ይሆናል። ስለዚህ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው የህወሓት መርህ በግልፅ አጥፍቶ መጥፋት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይህ የአጥፍቶ-መጥፋት መርህ “ህወሓት ከሌለ የትግራይ ህዝብ የለም፤ የትግራይ ህዝብ ከሌለ ህወሓት የለም” በሚለው የህወሓቶች የተለመደ አባባል በተደጋጋሚ ሲገለፅ አስተውለናል።
በእርግጥ የአንድ ህዝብ የመኖር ህልውና ከአንድ ፓርቲ ስልጣን ጋር ማቆራኘት አጥፍቶ-መጥፋት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። የትግራይ ህዝብ የብዙ ሺህ አመት ታሪክና ህልውና ያለው ነው። የዛሬ አርባ አምስት አመት የተፈጠረ ድርጅት ህልውና የትግራይ ህዝብን ታሪክና የወደፊት ህልውና የሚወስን ከሆነ ችግሩ የቱ ጋር እንዳለ መገመት ቀላል። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ከህወሓት በፊት እንደነበረው ሁሉ ከህወሓት በኋላም ብዙ ሺህ አመታት ይኖራል። 50 አመት አንኳን ያልሞላው ድርጅት “እኔ ከሌለው የትግራይ ህዝብ አይኖም” ማለቱ የትግራይን ህዝብ አጥፍቶ ለመጥፋት ያለውን ቁርጠኛ አቋም ከመግለፅ የዘለለ ፍቺ ሊሰጠው አይችልም።

በተመሳሳይ ህወሓት ባስቀመጠው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ የማይመራ ከሆነ የኢህአዴግም መጨረሻ እጣፈንታ የተለየ ሊሆን አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ የኢህአዴግ ተልዕኮና ዓላማ ከሚመራው ፓርቲና መንግስት አልፎ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም እንደሚወስን ይገልፃል። ቀደም ሲል በተጠቀሰው የህወሓት ፅሁፍ ላይ ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደምትበታተን እና ህዝቦቿን በጦርነት ለዕልቂት እንደሚዳረጉ ተገልጿል። በዚህ መሰረት ልክ እንደ ህወሓት “ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ አትኖርም፤ ኢትዮጵያ ከሌለች ኢህአዴግ አይኖርም” እያለን እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል።

ኢትዮጵያም ሆነች ህዝቦቿ በኢህአዴግ አልተፈጠሩም፣ በኢህአዴግ አይጠፉም። ይሁን እንጂ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለው የህወሓት መርህ ከትግራይ ህዝብ አልፎ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አጥፍቶ መጥፊያ መሳሪያ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ የኢህአዴግ ህልውና በህወሓቶች አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ተግባራዊነት ላይ የተመሰረተ ከሆነ “ህወሓት ከሌለ ኢህአዴግ የለም፤ ኢህአዴግ ከሌለ ህወሓት የለም” ማለት ነው። በአጠቃላይ አሁን ላይ ህወሓቶች እየተከተሉት ያለው መርህ “ህወሓት ከሌለ ህዝብ፣ ሀገርና ፓርቲ አይኖርም!” የሚል ነው። ታዲያ እንደ ህወሓት ያለ “አጥፍቶ ጠፊ” አለን?

በቀጣይ ክፍል የህወሓት አጥፍቶ መጥፋት መርሃ ግብር በዝርዝር እንመለከታለን። በዚህ መሰረት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የወሰዷቸውን የተግባር እርምጃዎች፣ እንዲሁም ድርጅቱ የመጨረሻውን የአጥፍቶ መጥፋት እርምጃ ለመወሰን መቀሌ ላይ እያደረገ ባለው ስብሰባ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ጭምር እንዳስሳለን። ያም ሆነ ይህ ህወሓት ህዝብና ሀገርን አጥፍቶ የመጥፋት እርምጃ ሊወስድ የቀሩት ሁለት ቀናት ናቸው።