በድሬደዋ ከተማ እንዲበተኑ የተደረጉ ወጣቶች ባደረሱት ጥቃትና ዝርፊያ በርካታ ነዋሪዎች ተጎድተዋል።- የከተማዋ ነዋሪዎች

ኢትዮ 360 – በድሬደዋ ከተማ እንዲበተኑ የተደረጉ ወጣቶች ባደረሱት ጥቃትና ዝርፊያ በርካታ ነዋሪዎች ተጎድተዋል።- የከተማዋ ነዋሪዎች

በድሬደዋ ዛሬ ጠዋት በተሽከርካሪ ተጭነው ከተማው ውስጥ እንዲበተኑ የተደረጉት ወጣቶች በየቤቱ ድንጋይና የጠርሙስ ስብርባሪ በመወርወር ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ።

ኢትዮ 360 ወደ አካባቢው ደውሎ የአካባቢውን ነዋሪዎች ባነጋገረበት ወቅት እንዳሉት ችግሩን እያደረሱ ያሉት ወጣቶች ድንጋዩንና የጠርሙስ ስባሪውን የሚወረውሩበት ወንጭፍ በጆንያ እየታሸገ ወደ ከተማ መግባቱንም ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩትነው ።

ችግር እየፈጠሩ ያሉት ወጣቶች ብሔርን መሰረት ባደረገውና ቤትን እየለየ በሚፈጸመው ጥቃታቸው ይሄን ወንጭፍ መጠቀምና ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረስ አላማቸው አድርገውት አርፍደዋል ብለዋል።

ይሄ ብቻ አይደለም ይላሉ ነዋሪዎቹ ከውርወራው በዘለለ በየቤቱ በመግባት ከባድ ዝርፊያ ፈጽመዋል፡በሮችን ሰባብረዋል፡በሮቹ አልገነጠል ባሉ ቤቶች ደግሞ በግንብ ዘለው በመግባት ዝርፊያ ፈጽመዋል ሲሉም ይናገራሉ።Image may contain: cloud and outdoor

በየመደብሮቹ በመግባትም የሃይላንድ ውሃዎችን እየቀዳደዱ መሬት እንዲፈሱ ማድረጋቸውንና ምግቦችን መድፋታቸውም ታውቋል።

ወጣቶቹ ይህን ሁሉ ዝርፊያና ጉዳት ሲያደርሱ በአካባቢው የፌደራል ፖሊስና የከተማ የጸጥታ ሃይል ቢኖሩም ቆመው ከመመልከት ውጪ ወንጀሉን ለማስቆም ያደረጉት ምንም አይነት ጥረት የለም ሲሉ ይከሳሉ።

ምናልባትም ሳተናው የሚባለው የከተማዋ ወጣቶች ቡድን በአካባቢው ደርሶ ህብረተሰቡን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ ባያደርግ ኖሮ አደጋው ከዚህ የከፋ ይሆን ነበር ብለዋል።

Image may contain: one or more people, people standing, sky and outdoorየጥፋት ሃይሎቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ ህብረተሰቡ በቀላሉ ተከላክሎ መመለስ እንዳይችል ማድረጉንም ገልጸዋል።

በሁሉም ችግር ላይ ዝምታን የሚመርጠው የከተማዋ አስተዳደር ችግር ተፈጥሯል ብሎ ለፖሊስ ከመደወልና፡መከላከያ ከመጥራት የዘለለ፡ስራ የለውም ብለዋል የከተማዋ ነዋሪዎች።Image may contain: one or more people, people standing, people walking and outdoor

በደቻቱ፡በመጋላ፡በገንደምስኪን፡በቀፊራና በሌሎች አካባቢዎች ዝርፊያውና ጥቃቱ እንደተፈጸመ የሚገልጹት ነዋሪዎች ሰፈራቸውን ጥለው ወደ ሌላ አካባቢ የሸሹም እንዳሉ ተናግረዋል።ኢትዮ 360ም አካባቢያቸውን ጥለው ሸሹ የተባሉትንም አግኝቶ አነጋግሯቸዋል።

እነሱም ሁኔታው እጅግ አስፈሪና ብሔርን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም መሆኑ ነገሮችን ከባድ አድርጓቸዋል ይላሉ።

ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሃይል ደርሶ አካባቢውን ለማረጋጋት ቢሞክርም ጥፋት አድራሾቹ ከዋኖቹ አካላት ጋ ግንኙነት ስላላቸው መከላከያ ከመድረሱ በፊት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ይደረጋሉ፡ ስለዚህ መከላከያ ሃይሉ በአስለቃሽ ጭስ የሚበትነው ነዋሪውን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

የከተማዋ ነዋሪዎች የፌደራል መንግስቱም ሆነ የሚመለከተው አካል ለከተማዋ ችግር መፍትሄ፡ ችግር እየፈጠሩ ላሉት አካላት ደግሞ የህግ የበላይነትን ማሳየት ካልቻለ ነገሮች ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ማምራታቸው አይቀርም ሲሉ ለኢትዮ 360 ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ኢትዮ 360 የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላትን በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።

ኢትዮ 360