" /> ኢትዮጵያ የተባረከች ሀገር ናት፣በኢትዮጵያ መገኘታችን ትልቅ ጸጋ ነው – የኮቲዲቫር ንጉስ ቺፌዝ ጆን ጋርቭየስ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ኢትዮጵያ የተባረከች ሀገር ናት፣በኢትዮጵያ መገኘታችን ትልቅ ጸጋ ነው – የኮቲዲቫር ንጉስ ቺፌዝ ጆን ጋርቭየስ

(ኢዜአ) – የኢትዮጵ ህዝብ ሰው አክባሪ ፣እንግዳ ተቀባይ እና አኩሪ ባህል ያለው መሆኑን አይተናል “ ሲሉ የኮቲዲቫር ንጉስ ተናገሩ።ንጉሱ ከነቤተሰባቸው ጋር በመሆን ለኃይማኖታዊ ስነስርዓት ዛሬ አክሱም ከተማ ገብተዋል።

ንጉሱ ቺፌዝ ጆን ጋርቭየስ አክሱም ሲደርሱ በኃይማኖት መሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያ ስልጣኔ በአክሱም እንደተጀመረና ብዙ ነግስታት ንግሳቸውን እዚህ እንደሚቀበሉ በታሪክ አውቃለሁ “ ብለዋል።

የኮንጎ፣ቱኒዝያ፣ናይጀሪያ፣ኡጋንዳና ግብጽ ነገስታት ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎች አብሮዋቸው እንደመጡ ያመለከቱት ንጉሱ የመጡበት ፕሮግራምም አህጉራዊ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ የተባረከች ሀገር ናት፣በኢትዮጵያ መገኘታችን ትልቅ ጸጋ ነው “ ያሉት ንጉሱ ከዚህ በኋላ አክሱምን እንደራሳቸው አካባቢ እንደሚያዩት ተናግረዋል።

የኢትዮጵ ህዝብ ሰው አክባሪ ፣ እንግዳ ተቀባይ እና አኩሪ ባህል ያለው መሆኑን ማየታቸውን ተናግረዋል።

የአክሱምና አከባቢው ህዝብ የጠነከረ ማህበረሰባዊ አንድነትና የተለየ የአለባበስ ባህል ያለው እንደሆነ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የአክሱም ፅዮን ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ ንቡረ ኢድ ቆመስ አባ መሓሪ ተክለ በበኩላቸው ለንጉሱ የእንኳን ደህና መጣህ መልእክት አስተላልፈዋል።

አፍሪካዊያን ወንድም እህቶች ወደዚህ ስፍራ መምጣታቸው ለኢትዮጵያን ትልቅ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

አባ መሓሪ አክለው ጥንታውያን ነገስታት በአክሱም ይነግሱ እንደነበር አስታውሰው የኮቲዲቫርና የሌሎች ሀገራት ነገስታት መምጣታቸው የሀገሪቱን ስልጣኔ ዳግም የሚያበስር መሆኑን አመልክተዋል።

የአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹም ብርሃን አክሱም በኃይማኖት ብቻ ሳይሆን በብዙ ቅርሶች በአለም የሚታወቅ ታሪካዊ ስፍራ መሆኑን ለእንግዶቹ ገለጻ አድርጎላቸዋል።

የውጭ ሀገር እንግዶች በታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ስፍራ መገኘታቸው ባህልሉንና ጥንታዊ ቅርሶች በማስተዋወቅ የአክሱም ታሪክ እንዲያውቁና የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

አቶ ገብረመድህን እንዳሉት የኮቲዲቫር ንጉስና ሌሎችም የአፍሪካ ንገስታት መምጣታቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያግዛል፤በቀጣይ በቱሪዝም ዘርፍ አብሮ ለመስራት ውይይት ይደረጋል።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV