" /> የብ/ጄ አሳምነው ጽጌ እናት እማሆይ የውብሰፈር አሳዬ እህታቸው ደስታ ፅጌና ጓደኛቸው ይናገራሉ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የብ/ጄ አሳምነው ጽጌ እናት እማሆይ የውብሰፈር አሳዬ እህታቸው ደስታ ፅጌና ጓደኛቸው ይናገራሉ

BBC Amharic : ከጥቂት ወራት በፊት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ኢትዮጵያ በታሪኳ በብዙዎች ዘንድ የማይሽር የታሪክ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ክስተት አጋጠማት። የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ሜጄር ጄኔራል ገዛኢ አበራ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንንና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴንና የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደን በጥቂት ቀናት ውስጥ አጥታለች።

ይህንን የከሸፈውን “መፈንቅለ መንግሥት” አቀነባብረዋል የተባሉት በወቅቱ የአማራ ክልል የደኅንነትና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ከክስተቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ተገደሉ። ባህርዳር ዙሪያ በሚገኝ ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በባጃጅ ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው የሞቱት። የብርጋዲየር ጄኔራሉ ቀብር በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ጊዮርጊስ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ. ም. ተፈፅሟል። በቅርቡ ላሊበላ የነበረው የቢቢሲ ባልደረባ የቀድሞው የደኅንነትና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እንዴት እንደሚታወሱ ከእናታቸው እማሆይ የውብሰፈር አሳዬ፣ ከእህታቸው ደስታ ፅጌና ጓደኛቸው ፀጋዬ ማሞ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ እናት እማሆይ የውብሰፈር አሳዬ

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬእናት

ቢቢሲ፡ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ሲወለዱ የተለየ የሚያስታውሱት ነገር አለ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬ ሁለተኛ ልጄ ነው፤ እኔ ወራቱን አላውቀውም። የጥምቀት ታቦቱ ሲወርድ ነው የተወለደው። አውደ ዓመት ስለነበር እንግዳም አዝማሪም ሞልቷል። የዓመት አውደ ዓመት አለ፣ የታህሳስ ተክለሃይማኖት ይባላል በአገራችን። ቤተሰብ በተሰባሰበበት ታላቅ ወንድሙ ስምሪት ቆይቶ ይመጣል። እዚያ ቆይቶ ሲመጣ አዝማሪውም እንግዳውም ሆይ ሆይ እያለ፣ ትልቅ አዳራሽ ነው፤ ከዚያ ከሞላው እንደመጣ ገብቶ ወጋግራውን ያዘ። ና ሲሉት ወጋግራውን ይዞ ዝም አለ።

“ተዉት እስቲ ያስተውልና ወደሚፈልገው ይቅረብ” ሲል አባትየው፤ ዝም ብሎ ቆይቶ ታላቅ ወንድሙ “ጌታሸት” ሲል “አቤት አለ” አባትየው “የሚወለደው ወንድ ነው ስሙን አሳምነው በለው” አለው።

ወዲያው አባትየው “ሊቀመኳስ” ብሎ “አቤት” ይለዋል “አዳምጠኝ” ይለዋል፤ “እሺ” ሲለው “አይቆረጠምም የተልባ ቆሎ አሳምነው ጽጌ በትንቢት ያለ” ብሎ እዚያው ገጠመ። እንደዛሬው ራዲዮ የለም፤ ቴሌቪዥን የለም፤ አዝማሪ ነው ቤተሰብ የሚያሟሙቅ፣ በዚያው ሆኖ ቀረ ስሙ።

ጎበዝ ተማሪ ነበሩ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬላሊበላ ነው ትምህርት ቤት የጀመረው። አስኳላ ነው የጀመረው። አዎ ድንቅ ነው።

የሙያ ይወታቸውን በመምህርነት ነው የጀመሩት፤ እንዴት ወደ ትግሉ ገቡ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬመጀመሪያ መምህር ነው የነበረው ሌላ ቦታ። እኒህ ህወሓቶች ሲመጡ ወደ መቄት ሲሻገሩ ልጄን ይገሉብኛል ብሎ አባትየው በበቅሎ ይዞት መጣ። ይዞት መጥቶ ና ተቀመጥ አለው። እነሱም እዛው ነበሩ። እነሱ ጋር እየገባ እየወጣ፣ እየገባ እየወጣ ወሰዱት፤ ኋላ “አገር ጎብኝተን ልንመጣ ነው” አለኝ። “መቼ ትመጣላችሁ” ስል “አይታወቅም” አለኝ። ከማንጋር ነው ስለው “እገሌ ጋር” አለኝ። ባልንጀራው ጋር እንደሱ መምህር ነበር። ታዲያ ቶሎ ትመጣላችሁ ስለው “አይታወቅም” አለኝ።

እሽ ብዬ ዝም አልኩኝ።በ ኋላ በአራተኛ ቀን ይሆናል እኛ ያለንበት ስብሰባ አድርገው ለአገራችን፣ ለድርጅታችን ያሉት ወንድሞቻችን እነአሳምነው ጽጌ እና ደጉ አስናቀ ይኼው ትግል ሄደዋል ተብሎ ተነገረ። ያን ጊዜ ከስብሰባው ወጥቼ እሪ አልኩኝ ጎረቤትም ተሰብስቦ አፅናናኝ፤ ልጁ ደግሞ ወደ ደጅ ወጥቶ አያውቅም ከተማሪ ወጥቶ አስተማሪ ነው የሆነው።

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

 ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

ከአስተማሪነት ወጥቶ ነው ትግል የገባው። ያው ሲያገኙት ሆይ ሆይ ብለው አስገቡት። በዚያው ሄዶ፤ ደህና ሳይቆስል፣ ምን ሳይል መጣ። በሠላም መጣ። እኔም መጣልኝ ብዬ ደስ ብሎኝ ሳለ ደግሞ እዚሁ ድርጅት ገባ። ከዚያ ወዲህ እንዲህ ነው ያለው። አንዴ ውጭ አገር ሂድ ሲሉት፣ አንድ ጊዜ ታሰር ሲሉት፤ ብሎ ብሎ መጨረሻው ይኼ ሆነ።

ምን አይነት ልጅ ነበሩ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬባህሪው ጥሩ ነው፣ የተለየ ባህሪ የለውም፣ የታወቀ ነው። እንደሰው አሁን ቁጥት፣ አሁን ሳቅ አይልም። ጠባዩ አንድ ነው። ቅብጥብጥ ያለ ነገር የለውም። እንደልጅ ጨዋታ፣ ፍቅርም ጠብም የለውም። የተረጋጋ ነው ከልጅነቱ ጀምሮ። መቼም ድንቅ ነው እንደ ልጅ ቅብጥብጥ ያለ ድርስ ምልስ ያለ ነገር የለውም። ድንቅ ልጅ፣ ቀና፣ ለኔ አሳቢ ነበር፤ ለሁሉም ነገር።

እስር ቤት ሳሉ የነበሩበት ሁኔታስ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬእኛ እየሄድን ማየት ነው እንጂ ሁኔታውን ማን ያውቃል። አዲስ አበባ ቃሊቲ አሰሯቸው፤ ከዚያ ደግሞ ዝዋይ ወሰዷቸው። እዚያ በዓመት ሁለት ጊዜ እየሄድኩ እጠይቀዋለሁ። ምን ይለኛል “መንገድ መሃል ገብተሽ አትሂጂ፤ ልብሽ ብዙ ያስባልና ሃሳብ ላይ ስላለሽ መኪና ይመታሻል የፊትሽን ስታዪ በኋላ ይገጭሻል”።

“የኋላ መጣ ስትዪ፤ የፊትሽ ይገጭሻል፤ ወይ ከዚህ ሆነሽ ወይ ከዚያ ሆነሽ ጸልዪ መንገድ አትግቢ” ይህንን ይለኛል። ሊፈቱ ነው ተባለ። እኛም እነሱን ለማምጣት ሄድን። ተፈቱልን ይዘን መጣን። ከዚያ አገርም ጎብኝተው፣ ከዚህም አርፈው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ።

ዓመት በዓልንስ እንዴት ነው የሚያሳልፉት

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬያርዳል፣ እኛ እንጠምቃለን እንጋግራለን። ጎረቤት፣ ቤተሰብ ጋር አብረን በልተን ጠጥተን፣ ስቀን፣ ተጫውተን አመት በዓል እናሳልፋለን እንደዚህ ነው አዋዋሉ። ከዚያ መለስም ወረቀት ያነባል። በዓመት በዓልም፣ በሌላውም ጊዜ ይረዳኛል። ሁልጊዜም ጠያቅዬ ነው።

ቤተሰብ አፍርተዋል? ከሞቱ በኋላስ ይጠያየቃሉ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬአዎ አግብቷል ወልዷል። ከመጀመሪያ ሚስቱ አንድ ልጅ ወልዷል። ከእሷ ጋር ሲለያዩ ደግሞ ሦስት ልጅ ወልዷል።

አይ የሞተ እለት መጥው ነበር። የ40ው ዕለትም መጥተው ነበር፤ እንጂ ምን አቅም አግኝቼ? እያኸኝ። ያው እሱ ታስሮ ሳለ ወደ እሱ ነበር እሄድ የነበረው። ፊት እነሱንም እጠይቅ ነበር፤ ኋላ ግን እየደከመኝ አልሆን አለኝ።

ለመጨረሻ ጊዜ መች ነው ያዩዋቸው?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት “ለትንሳኤ ነይ ብሎ ነው። አምና ካንቺ ውለናል ዘንድሮ ነይ ከእኛ” ብሎ ሚስቱን ላካት። እኔ እንኳን አልሄድም ስል፤ ከዚህ ነው የምንውለው ብሎ ላከብኝ። ሄድኩኝ ለትንሳኤ አየሁት።

ታርዶ፣ ተጠምቆ ነበር። ከሰዎች ጋር መጥቶ ለአውደ ዓመት ቀምሶ ሄደ እንጂ ደግሞ አልመጣም። ከዚያ ወዲህ አልመጣም። አሁን የጠፋው ወንድሙ ሌላ ስፍራ ነበር። ከእሱ ሄደን ስንጫወት ውለን በዚያችው እንደተለያየን ቀረን።

ቀኑን ለይቼው አላውቅም፤ ሆዴ እየተጨነቀ እምቢ ሲለኝ ደውሉልኝ አልኩ። ደሞ ወደማታ አሁን መጥቶ ይሆናል ደውሉለት ስል፤ ኧረ ደክሞት ይተኛል፤ ደሞ ይረፍበት የሚያሳርፈው የለም አሉኝ። ከሥራው ደግሞ ይደውሉለትና በዚህ ና ይሉታል፣ ውክቢያ ነው የሱ ኑሮ ተይው ጥቂት ይረፍ ይሉኛል። ድንቅ እላለሁ፣ በዚያው ድምጹን ሳልሰማ ቀረሁ፣ በዚያው ቀረሁ።

ሰኞ መጀመሪያ ባህርዳር ረብሻ ተነስቶ ተኩስ ተሰምቷል መባሉን ስሰማ፤ እንዴት ሆኖ ይሆን? ይኼ ልጅ እንዴት ነው ነገሩ? ስል እሱማ ያሰለጠናቸውን ወታደሮች ይዞ ጎንደር ገብቷል ያንቺው ልጅ ይሉኛል።

ጎንደር ከገባልኝማ ልጄ አይሞትም። እንኳን በዓይን አይተውት በዝና ታስሮ እያለ፤ ጀነራል ተፈራ ማሞ፤ ጀነራል አሳምነው ጽጌን ፍቱልን እያሉ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ሲጠይቁ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ።

ጎንደር ከገባማ ልጄ አይሞትም እያልኩን ተስፋ አደረኩኝ በእጄ የያዝኩት መስዬ። በኋላ ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድ እንዲህ ተብሎ ተወርቶ፤ ሰኞ እንዲህ ሆነ እያሉ መጡ።

እንው የማይረሳዎት ትዝታ አለ?

እማሆይ የውብ ሰፈር አሳዬምን አስታውሳለሁ። ይጦረኛል ይቀብረኛል ነው እንጂ ምን አስታውሳለሁ። አሁንማ ተፈቶልኝ ደስ ብሎኝ ነበር። ይሄንን ነው የማስታውሰው እንጂ ሌላ ምን አስታውሳለሁ።

ደስታ ጽጌ- እህት

አሳምነው ሦስተኛ ታላቄ ነው። እኔ ህጻን እያለሁ፣ እሱ አስተማሪ ነበር። እየመጣ ይጠይቀን ነበር፤ ተማሪ ይለኝ ነበር። ርህሩህ አንጀት ነው ያለው፤ ያለውን ነገር ይዞ ከቤተሰቦቹ ጋር ሰብሰብ አድርጎ፣ አውደ ዓመትም ይሁን ከቆዬበት ሲመጣ ተሰባስበን፣ ያለውን ነገር አብረን ተካፍለን ተጫውተን እንድንለያይ ነው የሚፈልገው። የወንድ ልጅ ሳይሆን የእናት አንጀት ነው ያለው እላለሁ።

የእስር ቆይታቸው ምን ያህል ለቤተሰቡ ከባድ ነበር?

ደስታ ጽጌእስር ቤቱ በጣም ከባድ ነበር፤ ያውም ዘጠኝ ዓመት። መጀመሪያ ማዕከላዊ ነበር። ስንቅ ዝም ብለው ይቀበሉናል። እኛ ተስፋችን ስንቅ ሲቀበሉን ነው፤ መኖር አለመኖሩን የምናውቀው ማለት ነው፤ ሰሃኑን ከተቀበሉን ደስ ብሎን እንመለሳለን።

ዛሬ አንቀበልም ብለው ምግቡን ይዘን ከተመለስን፤ ነገ ነግቶ ደግሞ ምን እንደሚፈጠር እየጠበቅን እያለቀስን ነው የምንውለው። እነሱን ወደ ማረሚያ ሲልኩ አሁን ተሰወረ የተባለው ወንድሜ እሱ ተለቀቀ። ሦስት ወር አይደል ጨለማ ቤት የነበሩት። ከዚያ እነሱ ወደ ቃሊቲ የእድሜ ልክ እስራት፤ እሱ ነጻ ተብሎ ተለቀቀ። ቃሊቲ ስንቅ እያመላለስን እያለ በኋላ ደግሞ ወደ ዝዋይ አራቁት።

እስር ቤት በነበረበት ወቅት፤ እሱን ብዬ፣ ሁሉን ነገር ትቼ አዲስ አበባ ነበርኩ። ቤት ተከራይቼ የማላውቀውን ሥራ ሁሉ ሰርቻለሁ ለእሱ ስል። እኛ ለሁሉም ነገር አቅሙ የለንም። ኃይል የእግዜር ነው። ያንን ሁሉ አልፎ ነበር። ብርዱ፣ ታክሲው አልፏል። እየተገፋን፣ ዘንቢል ይዘን ወድቀን ነበር። እግዜር ለቅሶአችንን ሰምቶት ሰጥቶን ነበረ።

አሁን ደግሞ መጨረሻ አንድ ዓመት ያልሞላ ደስታ። ብቻ ከባድ ነው። ሰው ሆኖ መቆማችን ራሱ ህልም ይመስለኛል። ወንድሜ ሳይሆን እናቴ ነው ማለት እችላለሁ።

በምን ታስታውሻቸዋለሽ?

ደስታ ጽጌእኔ እስከማውቀው ርህሩህ መሆኑን፣ ሰው አፍቃሪነቱን፣ ቤተሰብ የሆነ ያልሆነ አለማለቱን ነው። ማዕድ ተዘርግቶ፤ ይሄኛው አይበቃኝም፣ ይሄኛው ይሂድ የሚል ሰው አለ። እሱ አምጡ አቅርቡ ነው። ለምን ትመልሳለችሁ? ግባ በሉት? ነው የሚለው። ይሄንን ማንም መጠየቅ ትችላለሁ።

በዓል አያከብርም፤ ለእኛ ግን ያከብርልናል። እመጣለሁ ይላል እናዘጋጃለን። ለቤተሰብ ደስታ ሲል ደርሶ ተመልሶ ይሄዳል። ለሰው የሚኖር እና የተፈጠረ ነው፤ እኛን አስደስቶ ይሄዳል። ልጆቹን በጣም ይወዳል።

ጸጋዬ ማሞ – ጓደኛ

ትውውቃችሁ እንዴት ነው?

ጸጋዬ ማሞከ1984 ጀምሮ አውቀዋለሁ። የላሊበላ አስተዳዳሪ ሆኖ፤ በትጥቅ ትግል ወቅት እኔም እሱም ታግለናል። ትውልድ አካባቢያችን ተመሳሳይ ነበር። በኋላም በትውልድ አካባቢያችን ተመደብን፤ እሱ የቡግና ወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ። እኔ ደግሞ በጤና ሙያ እየሠራሁ ነው የምንተዋወቀው።

ብርጋር ጄነራል አሳምነውን እንዴት ይገልጿቸዋል?

ጸጋዬ ማሞአሳምነው ፍጹም ዴሞክራት፣ ጥሩ፣ ሰው አክባሪ ስብዕና ያለ፣ ፍጹም ሜካናይዝድ ሰው ነው። ሰውን ዕኩል የሚያይ፣ ተገልጋይ ቢሮ ሲሄድ ከመቀመጫው ተነስቶ ችግር የሚፈታ አይነ ግቡ ትልቅ ሰው ነው። ተጫዋች፣ በሥራ የሚያምን፣ ትሁት ነው። ለቅሶ ይሄዳል፤ በማኅበራዊ ሕይወቱ ደግሞ ትልቅ ቦታ ነበረው።

ህብረተሰቡ ከድህነት ወጥቶ፣ ልማት፣ ትምህርትና ጤና እንዲደራስ ሳያሰልስ ሰርቷል። ብዙም አሳክቷል። ህብረተሰቡ ተለውጦ ስኬታማ እንዲሆን ነበር ምኞቱ።

አሳምነው በጣም የእምነት ሰው ነው። አባቱም አገልጋይ ነበሩ። ኪዳነምህረት ሁሌም ይዘክራል። ጎረቤት እየጠራ ይዘክራል። እንደጓደኛ እኔም እሳተፍ ነበር። በዓልን እንደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ያከብር ነበር። ሕዝቡን እኩል የሚያይ ነበር።

ሁሌም ሲመጣ ስለ ክልሉ፣ ስለ ልማት እና ስለአማራ ሕዝብ አንስቶ ይብሰለሰላል፤ መጥቶም ለተተኩት አስተያት ይሰጣል። ሲመጣም ስለሕዝቡ ነው ብሶቱ፤ በግልም የሚነግረኝ ስለቤተሰቡና ስለ ግል ሕይወቱ ሳይሆን፣ ስለህብረተሰቡ ሲያወራ ነው የማውቀው።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV