" /> በጋምቤላ የተራድኦ ድርጅት ሰራተኞችን በመግደል የተጠረጠሩ አለመያዛቸው ተገለፀ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በጋምቤላ የተራድኦ ድርጅት ሰራተኞችን በመግደል የተጠረጠሩ አለመያዛቸው ተገለፀ

BBC Amharic : ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አክሽን ኤጌይንስት ሃንገር የተባለው የተራድኦ ድርጅት ሁለት ሰራተኞች በማይታወቁ ታጣቂዎች ከጋምቤላ አርባ አምስት ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ቦታ ተገድለዋል።

ግድያው ከተፈፀመ በኋላ ድርጅቱ ድረገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ በግድያው የተሰማውን ኃዘን አስፍሮ ከነፍስ አድን ስራዎች ውጭ ሌሎች የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጋምቤላ ማቋረጡን ገልጿል።

እስካሁን ድረስ ተጠርጣሪ እንዳልተያዘና ምርመራው እንደቀጠለ የጋምቤላ ክልል የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ብለን ጥቃቱ የደረሰበት አካዶ ቀቦሌ ሶስት የስራ ኃላፊዎች አስረናል። የስራ ኃላፊዎቹ በቁጥጥር ስር ሆነው ተጠርጣሪዎችን ማግኘት ስለሚያስቸግር ከህዝቡ ጋር ሆነን ጥቆማ ለመንግሥት እንሰጣለን በማለታቸው በዋስ ተለቀዋል” ይላሉ አቶ ቶማስ

አክለውም “የምንጠረጥራቸው ሰዎች አሉ ነገር ግን መረጃው ሙሉ እንዲሆን ከህዝብ ጥቆማ ያስፈልገናል” ያሉት አቶ ቶማስ ኃላፊዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር ተመካክረው ተጠርጣሪዎችን እንዲያጋልጡ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አቶ ቶማስ ግድያው የተፈፀመ እለት ዝናብ ዘንቦ በመጨቅየቱ የተጠርጣሪዎች ዱካ መገኘቱንና የፀጥጣ ኃይሎችም ዱካውን ተከትለው ቢሰማሩም ውጤት ላይ መድረስ አልቻሉም።

ግድያው እንዴት ተፈፀመ?

ግድያው የተፈፀመበት በጋምቤላ ክልል ይታንግ የምትባል ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በቅርብ እርቀት የምትገኝ ቦታ ናት። አቶ ቶማስ እንዳሉት የተገደሉት የኃገር ውስጥ ሰራተኞች ሲሆኑ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ማለፉን አስረድተዋል።

“አንደኛው ሟች የመኪናው አሽከርካሪ ከመኪናው ውጭ ሞቶ የተገኘ ሲሆን ሌላኛው ሟች መኪና ውስጥ የአደጋ መከላከያ ቀበቶ እንደታጠቀ ተገድሏል” ብለዋል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የተራድኦ ድርጅት እንዳስታወቀው ሟቾቹ ወደ ዊኜል ስደተኞች መጠለያ ጣብያ እየተጓዙ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ስቴቨን ዌሬ ኦማሞ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰብዓዊ እርዳታ የሚሳተፉ ተቋማትንም ሆነ ሰራተኞች ደህንነትና ጥበቃ መንግሥት እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ስራ ኃላፊዎች ግድያውን የፈፀሙትን ግለሰቦች ወደ ህግ እንደሚያቀርቡ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል።

ድርጅቱ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰራ እንዳለ ከድረገፁ የተገኘው መረጃ ያሳያል።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV