በዳውሮ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት አለፈ

(ኢዜአ) — በዳውሮ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት አደጋው የደረሰው በማረቃ እና ሎማ ወረዳዎች ያማላ ሜሶኮና ሀልአኒ አይሲ በተባሉ ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

በቀበሌዎቹ ትናንት ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የመሬት መንሸራት አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው ሌላ አምስት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና እርዳታ ወደ ጤና ተቋማት መላካቸውን አቶ እንዳለ ገልጸዋል ።

እንዲሁም ከ30 ሄክታር በላይ የለማ ሰብል ከጥቅም ውጪ መሆንና ብዛት ያላቸው የቤት እንስሳት መሞታቸውን አመልክተዋል።

“ጉዳቱ የደረሳባቸውን ነዋሪዎች መልሶ ለማቋቋም የመለየት ስራ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የሞቾቹ የቀበር ስነሰርዓት በየአካባቢያቸው እየተፈጸመ መሆኑም ተመልክቷል።