እነ ዶ/ር አብይ ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ለመቆም ድፍረቱ ይኖራቸው ይሆን? #ግርማካሳ

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚል ስጋት አላቸው። እኔ ደግሞ ምንም ስጋት የለኝም። የኛ ህዝብ ትግሬ፣ በሉት ኦሮሞ፣ አማራ በሉት ሲዳማ፣ ጉራጌ በሉት አፋር….አንድ ሕዝብ ነው። የተሳሰረ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ ትልቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስነ-ምግባርና ጨዋነት ያለው።

ችግሩ ያለው ፡

አንደኛ – ሕወሃትና ኦነግ የዘረጉትና የረጩት የዘር ፖለቲካ ላይ ነው። የዘር አወቃቀሩና ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ መተሳሰርና መደመር ላይ ሳይሆን ልዩነት ላይ ያተኮረው ሕግ መንግስት መሆኑ ነው።

ሁለተኛ – የለማ ቲም የሚባለው የ”ለውጥ” ሃይል፣ አሁን አገሪቷን ከዘር ፖለቲካ ለማውጣት በበቂ ሁኔታ እንቅስቅሴ ማድረግ አለመቻሉ ነው። የድሮውም የተበላሸና የቀረቀሰ መኪና ይዘው፣ የሹፌሮቹን ቦታ እነርሱ ተክተው እናሻግራቹሃለን ማለታቸው ነው።

የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች የዘር አሰራራቸውን ትተው ከተዋሃዱ፣ ሕገ መንግስቱንና የፌዴራል አወቃቀሩን ለማስተካከል ከሞከሩ፣ ሹፌሩን ብቻ ሳይሆን መኪናዉን ቀየሩ እንደማለት ስለሚሆን ፣ እመኑኝ፣ ነገሮች ይስተካከላሉ። የሚቀጥለውም ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ።ማሻገር ይችላሉ።

ይሄን ሲያደርጉ በሕወሃቶችና እንደ ኦነግ፣ ጃዋር ባሉ ጽንፈኞች ከፍተኛ ተቃዉሞ ይገጥማቸዋል። ሕወሃቶችና እነ ጃዋርም በቅንጅት ፣ በትግራይና በአንዳንድ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች (በዋናነት ወለጋ፣ ምእራብ አርሲና ባሌ..) ፣ እንዲሁም ኢጄቶዎችን በማስተባብር በሲዳማ ዞን ተቃዉሞዎችን ሊያስነሱ ይችላሉ። የጃዋር ቀኝ እጅ የሆነው ሕዝቄል ጋቢሳ በመቀሌ ተገኝቶ ሲናገር የነበረው ጸረ-ኢትዮጵያ ንግግሮችን፣ በሕወሃትና በኦሮሞ ጽንፈኞች ያለውም መቀራረብ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በነዚህ ጥቂት ጽንፈኞች ዘንድ ተቃውሞ ሊነሳ ቢችልም፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በኦሮሞ ክልል እንደ ሸዋ፣ አርሲ፣ ጂማ፣ ኢሊባቡር ..ባሉ አካባቢዎች፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሃረር ….ከሁለት ሶስተኛ በላይ በሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ያገኛሉ።

እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ፣ እነ ዶ/ር አብይ የሚያወሩትና የሚናገሩትን ትተው( ንግግራቸውና የተስፋ ወሬያቸው ሕዝብ ስለሰለቸው) ከጥቂት ጽንፈኞች ተጽኖ ወጥተው፣ በተግባር፣ እደግማለሁ፣ በተተተተግግግግግግባባባባባርርርርርርር ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን የመቆም ድፍረቱ ይኖራቸዋል ወይ ? የሚለው ነው።

ድፍረቱ አላቸው፣ ከአብዛኛው ሕዝብ ጎን የመቆም ፍላጎት አላቸው ከተባለ እንግዲያወስ የ፡

– ሕግን ዱላም  ወንጀለኞች፣ ዜጎችን በግፍና በጭካኔ የሚያፈናቅሉ፣ ትጥቅ አንፈታም ብለው ህዝብን የሚያሸብሩ፣ ባንክ የሚዘርፉ፣ አመጽና ረብሻን የሚያወጁና በአደባባይ ዜጎች ሕግን ጥሰው በጉልበት የሚፈልጉትን እንዲያደርጉ የሚያበረታቱት ላይ ያሳርፉ። የፖለቲካ አመለካከቶቻቸውን ስላተመቻቸው ብቻ የተለያዩ አጋጣሚዎች መሰሪ በሆነ መንገድ በመጠቀም፣ በሰላም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካና የሲቪን ማህበር አባላትን፣ ጋዜጠኞችን በጅምላ ማሰርና ማፈን ያቁሙ። በተለይም የባላራደውና የአብን የታሰሩ አባላት በአስቸካይ መፈታት አለባቸው።

– በኦህዴድ ውስጥ የተሰገሰጉ ጸረ-ህዝብ አመለካከት ያላቸው እንደ አቶ አዲሱ አረጋ ያሉትን  ዘረኛ አመራሮች ማሰናበት አለባቸው።

እነዚህን ቀላል እርምጃዎችና ሌሎች ሕዝብ የሚፈለገው ማድረግ ከጀመሩ፣  ከሕዝብ ጎን ከቁሙና ከህዝብ ፍላጎት ጋር ራሳቸውን ካስተካከሉ፣ በጽንፈኞች ተጽኖ ከወጡ፣ በርግጠኝነት የምናገረው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደገና እድል ይሰጣቸዋል። እንደገና አብሯቸው ይቆማል። በዚህ በጭራሽ መስጋት የለባቸውም።