ኢጄቶን አደብ ማስገዛት ያስፈለጋል እያልኩ እንሆ መፍትሄው ለሲዳማ  #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

በሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት ከኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌና ትግሬ ቀጥሎ በሕዝብ ብዛት ትልቁ የሲዳማ ማህበረሰብ ነው። 3% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲዳማ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ወደ 3 ሚሊዮን ይጠጋሉ።ጋምቤላዎች፣ ቢኔሻንጉል ጉሞዞች፣ አፋሮች ከሲዳማዎች ያነሱ ናቸው በቅጡር። ከሲዳማዎች ብቻ ሳይሆን ከወልያታዎችና ከጉራጌጌዎችም …ያነሱ ናቸው። ግን ለነርሱ ክልል ተሸንሽኖላቸዋል፡ ሃረሬዎች አስር ሺህ አይሞሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ 0.001% አካባቢ ናቸው። ግን ለሃረሬዎች ክልል ተሰጥቷቸዋል። ለሃረሬዎች ክልል ተፈቅዶ ፣ ለሲዳማዎች መከልከሉ በምንም መስፈርት ትክክል ነበር ማለት አይቻልም። በርግጥም ሲዳማዎች ‘እኛ ለምን ክልል አይሰጠንም ?” ብለው መጠየቃቸው ያለ ምንም ጥርጥር ትክክለኛ ናቸው። ይህ በሲዳማዎች ላይ የታየው ኢፍትሃዊነት በራሱ አሁን ያለው አከላለል በደንብ ሳይጠና የተተገበረ፣ ብዙ ግድፈቶች ያሉትና የተመሰቃቀለ መሆኑን አመላካች ነው።

ሆኖም ግን የሲዳማ ክልል ጥያቄ ጉዳይ በተያያዥ የሚያስከትለው በርካታ ቀውሶችም እንደሚኖሩ መዘንጋት አያስፈለግም። ምን አልባትም ይህ ቀውስ ራሱ የሲዳማ ማህበረሰብን ችግር ውስጥ ሊከትም የሚችል ነው። የሲዳማ ወገኖች፣ በተለይም የአገር ሽማግሌዎች ነገሩን ሰፋ አድርገው በመመልከት ፣ ለማህበረሰቡ ከምንም በላይ የሚጠቅመው፣  ሰላምና ከሌሎች ጋር በፍቅር ተሳስሮ መኖሩ መሆኑን በማሳሰብ፣  በተለይም እንደ ጃዋር ባሉ የኦሮሞ ጽንፈኞች በስተጀርባ እየተገፉ ያሉ፣ ራሳቸውን ኢጂቶ ብለው የሚጠሩና  ችግር እየፈጠሩ ያሉ ወጣቶች ማስተማርና ማግባባት ቢጀምሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።

በሲዳማ ያለውን ጥያቄ እነዚህ የሕግ ማእቀፍ የሌላቸው ኢጄቶዎች በተወሰነ መልኩ፣  እንደ ጃዋር መሐመድ ካሉ የኦሮሞ ጽንፈኞች የሐሳብ፣ የገንዘብና የሕዝብ ግንኙነት ድጋፍ እያገኙ ጉዳዩን ከመጠን በላይ እያጦዙት ያለው።

ክልል በመሆን ጥያቄ ዙሪያ፣ በፓርላማ ተጠይቀው አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሐመድ፣ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ በክብር መቀበሉን፣ ደህደኔ የሚባለው ክልሉን የሚያስተዳድረው ድርጅት ጥያቄውን ተቀብሎ በሕግ አንጻር እየመረመረው እንዳለ ገልጸው፣ ደሃዴን የመጨረሽ ዉጤቱን እሰከሚያሳወቅ፣ ምርጫ ቦርድም ሕዝብ ዉሳኔዉን ለማድረግ ዝግጅቱን እሰከሚያጠናቅቅ በትእግስት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። ነገር ግን በኃይል እና በደቦ ለማስፈጸም የሚሞክሩ አከላት ካሉ፣ መንግስታቸው የኅይል እርምጃ እንደሚወስድ እና የሶማሌ ዕጣ ፈንታ እንደሚጠብቀው የተናገሩት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከሕግ ውጭ የሚደረጉ ተግባራትን በጭራሽ እንደማይታገሱ አስጠንቅቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ይተገብራሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ለምን ማንም ከሕግ በላይ ሆኖ አገር ማመስ ስለሌለበት።

ጠቅላይ ሚኒትስር አብይ አህመድ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ብዙዎች ምን አልባት ልብ ያላላሉት ነጥብ አስቀምጠዋል። “የክልል ጥያቄዎች ሲነሱ አንቀጽ 47ን ማሻሻል ያስፈልጋል። ያ ደግሞ እንዲሆን ጠያቂው አካል ጥያቄ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ክልሎችን ማሳመን ይጠበቅበታል” ነበር ያሉት።

በሕግ መንግስቱ አዲስ ክልልን በመመስረት ዙሪያ በአንቀጽ 47 ሁለት ንኡስ አንቀጾች ተቀምጠዋል። አዲስ ክልል ሲቋቋም ይህ ንኡስ አንቀድ በርግጥም መሻሻል አለበት። የፌዴራል መንግስት አባልት ቁጥር መጠቀስ ላይኖርበት ይችላል። በዚህም ሆነ በዚያ ያንን አንቀጽ ለማሻሻል በሕጉ መሰረት የሌሎችን ክልሎች አዎንታ ማግኘት የግድ ነው። ይሄ አንዱ በሕግ አንጻር ያለው ትልቅ ክፍተት ነው።

ሌላው በሕግ አንጻሩ ጉዳዩ ከታየ በጣም የሚያወዛግብና የሚያከራክር ሌላ ሶስት አብየት ነጥቦች አሉ። “ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል መመስረት ይችላሉ” ይላል አንቀጽ 47 ንኡስ አንቀጽ 2። አንቀጽ 47 ንኡስ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ የክልል ምስረታ ጥያቄው በብሄር ብሄረሰብ ሕዝብ ምክር ቤት 2/3ኛ ድምጽ ማግኘቱ ተረጋግጦ ለክልል ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበት ያስቀምጣል።

አንዱ ጥያቄ እንግዲህ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ሲል ምን ማለት ነው የሚለው ነው። የሲዳማ ዞን ለምሳሌ የክልል ጥያቄ ማቅረብ አይችልም። ለምን የዞን አመራር ወይም ምክር ቤት፣ የብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ ምክር ቤት ማለት አይደለምና። እንግዲህ ዞን ማለት ብሄር ብሄረሰብ ሕዝብ ማለት ካልሆነ፣ ታዲያ የሲዳማ ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ የሚባለው ማህበረሰብ ክልል ይኑረኝ ቢል የትኛውም መሬት ይዞ ነው የራሱ ክልል የሚኖረው ? ይሄ ግልጽ አይደለም።

ሁለተኛው ጥያቄ የሲዳማ ብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ የሚባል፣ በሕግ የታወቀ ሕጋዊ ማንነት ያለው ምክር ቤት አለ ወይ? የሲዳማ አባ ገዳዎች ናቸው ምክር ቤት የሚባሉት? ወይስ የሲዳማ ዞን አስተዳድር ነው እንደ ሲዳማ ሕዝብ ምክር ቤት ተደርጎ የተቆጠረው? ያ ራሱ ትልቅ የሕጋዊነት ችግር ያስነሳል። ሕጋዊነት የሌለውን አካል ዉሳኔ በመጠቀም ሕጋዊ ስራ መስራት ስለማይቻል።

ሶስተኛ በአንቀጽ 39 ንኡስ አንቀጽ ፣ ብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ የሚለውን ሕጋዊ ትርጉም ሲሰጥ ፣ ” ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባረቅ ባህል ወይንም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው። ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይንም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልካ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ይላል። በዚህ አተረጓጎም ክልል ወይንም ዞን በምንም መልኩ ከብሄር ብሄረሰብ ህዝብ ጋር አይገናኝም።

በሲዳማ ዞን በርካታ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት ይኖራሉ። ሆኖም ግን በአንዳንድ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች ሲዳማ ያልሆኑ ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን በስፋት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች አሉ። ለምሳሌ የአዋሳ ከተማን ከወሰድን፣ የአዋሳ ህዝብ በሌሎች የሲዳማ ዞን አካባቢዎች ካለው ማህበረሰብ ጋር በቋንቋ ፣ በስነ ልቦና አመለካከት ብዙ አይዛመድም። በብዛት አማርኛ ተናጋሪ የሆነ፣ ዘዉጋዊ ሳይሆን ሕብረብሄራዊ አመለካእክት ያለው ማህበረሰብ ነው።

ከሰባት ወራት በፊት ” የሲዳማ ክልል ከተባለ አዋሳስ የት ልትሄድ ነው ?” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ አስነብቤ ነበር። በዚህ ጽሁፍ የሲዳማ ዞን ፣ የሲዳማ ብሄረተኞች ብቻ ስለፈለጉ ለሲዳማዎች ብቻ የሆነ የራሱ ክልል ይሁን ከተባለ፣ ከላይ የጠቀስኳቸው ሕጋዊ ውዝግቦችን ከማስነሳቱ በተጨማሪ ከፍተኛ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስም ሊያመጣ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጬ ነበር። ያኔ ከጠቀስኩት ጥቂት ሐሳቦችን እንደገና እዚህ ለማንሳት እሞክራለሁ።

የሲዳማ ክልል ሲመሰረት በስተሰሜን በኩል አዋሳ አለች። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና በመላው የደቡብ ክልል ሕዝብ ያደገች ከተማ ናት። በክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ብዙ ወጭ አዋሳ ላይ ፈሷል። ይችን ዉብ ሕብረ ብሄራዊ ከአዲስ አበባና ከባህር ዳር ቀጥሎ፣ ምን አልባት ከባህር ዳር በላይ፣ ትልቅና ዘመናዊ የሆነች ከተማን ለአንድ ጎሳ ብቻ መስጠት ኢፍትሃዊነት ነው። በመሆኑም ሲዳማዎች ክልል ካልተሰጠ ብለው ድርቅ ካሉ ያለ አዋሳ መሆኑን እንዲረዱ ማድረጉ አስፈላጊና ዉሳኒያቸውን መልሰው እንዲመረምሩ ሊረዳቸው ይችላል። የግድ የሲዳማ ክልል ይንር ከተባለ፣ የአዋሳ ከተማ ራሷን የቻለን ቻርተር ከተማ ሆና እንድትቀጥልም መደረግ ነው ያለበት። አዋሳ የነዋሪዊቿ እንጂ የሲዳማዎች ብቻ አይደለችምና።

ከሲዳማ ክልል በስተደቡብ የሚገኝ ሌላ ትልቅ የደቡብ ክልል ዞን አለ። የጌዴዎ ዞን። የሲዳማ ዞን የሲዳማ ክልል ይሁን ከተባላ የጌዴዎ ዞን ከተቀረው የደቡብ ክልል ዞኖች ጋር ይለያል ማለት ነው። ኩታ ገጥምነቱ ስለሚቀር። የጌዴዎ ዞን ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱ ክልል ሊሆን ነው? ወይስ በሲዳማ ክልል ውስጥ ሊጠቃለል ነው? ስለዚህ የሲዳማ ክልል የመሆን ጉዳይን በተመለከተ ሲዳማዎችን ብቻ ሳይሆን የጌዴዎ ዞን ነዋሪዎችን የሚመለከት ነው የሚሆነው።

የሲዳማ ዞን ጉዳይ ሲታይ በአካባቢው ትልቅ ቀውስና አለመረጋጋት መፍጠሩ የማይቀር ነው። የሲዳማ አክራሪዎች፣ ከአንድ አመት በፊት በወላይታዎች ላይ ያደረሱትን አሰቃቂ እልቂት በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እፈለጋለሁ። ከዚህ በፊት ዘር ተኮር ግጭቶችና ደም መፋሰሶች ተከስተዋል። ወደፊትም የሁሉንም ማህበረሰባት ፍላጎት ባንጸባረቀ መልኩ ችግሮች ካልተፈቱ፣ የተወሰኑ ጽንፈኞችን ለማስደሰት ብቻ ውሳኔዎች ከተላለፉ ነገ የከፋ ችግር መፈጠሩ አይቀርም።

ዶር አብይ በፓርላማ ለተናገሩት፣ ኢጄቶ የተባለው ጽንፈኛ ቡድን መግለጫ በማውጣት “መጪው ሀምሌ 11 ቀን የማንንም ፈቃድ ሳንጠይቅ በራሳችን ምክር ቤት የሲዳማን ክልልነት እናውጃለን” ሲል ለዶ/ር አብይ ንግግር መልስ ሰጧል። ይህ ቡድን፣ ከላይም በተወሰነ መልኩ እንደገለጽኩት፣ ዘረኛ፣ ጸረ-ሕዝብ የሆነ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ላለፉት አንድ ሁለት አመታት በአዋሳና አካባቢዋ ሽብር ሲፈጠር የነበረ ቡድን ነው። የፌዴራል መንግስት ሕግን የማስከበር፣ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት፣ በምንም መልኩ ይህ ቡድን አካባቢዉን እንዲያሸብር ሊፈቅድለት አይገባም። ኢጄቶ አርፎ ካልተቀመጠ፣ በተለይም በአካባቢው ያሉ ሌሎች ማህበረሰባት ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ስለሚችል ፣ ዶ/ር አብይ በፓርላማ የተናገሩት ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀት ያለባቸው መሰለኝ። በተለይም በአዋሳና በአካባቢዋ የፌዴራል መከላከያ ሕግን ስርዓትን የማስከበር ሃላፊነቱን መረከብ ይኖርበታል። የሲዳማ ዞን ሆነ በሲዳማዎች የተሞላ የአዋሳ ከተማ ፖሊስ ከኢጂቶዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ እንደመሆኑ በነርሱ ላይ እምነት መጣል አይቻልም።

የኢጂቶዎች አካሄድ፣ የሲዳማን ማህበረሰብ፣ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከአዋሳ ህዝብና በደቡብ ክልል ካሉ ሌሎች ማህበረሰባት ጋር በቀጥታ የሚያጋጭ ፣ ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል መሆኑን መረዳት አለባቸው።

አሁን ባለው ሕግ መንግስትና አከላለል  የሲዳማ ክልል ከተሸነሸነ፣ ክልሉ የሲዳማዎች ክልል ነው የሚሆነው። አንድ ጎሳ፣ በኦሮሞ ክልል እንዳለው አንደኛ ዜጋ ይሆንና ሌሎች ሁለተኛ ዜጎች ወይም መጤዎች ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። ሲዳማዎች በክልሉ ሙሉ ለሙሉ የበላይነት ይኖራቸዋል። ለሁሉም ነገር መስፈርትና መመዘኛ የሚሆነው ዘር ወይንም ሲዳማነት ይሆናል። ልክ ኦሮሞ ክልል እየሆነ እንዳለው። ይሄ በተለይም እንደ አዋሳ ባሉ ቦታዎች የሚኖረውን ሲዳማ ያልሆነው አብዛኛው ነዋሪ መብት የሚገፍ፣ በአገሩ አንገቱን እንዲደፋ የሚያደርግ ነው። በጣም ሲበዛ አደገኛ የሆነ ነገር ነው።

ሁሉም ነገር ከሁሉም ማእዘናት ታይተው፣ በሲዳማ ዞን ያሉ የሌሎች ማህበረሰባት ጉዳይም ከግምት ውስጥ ተከቶ በሰላም ነው መጠናቀቅ ያለበት። ከላይ እንዳጠቀስኩት፣ በርግጠኝነት ክልል ከተመሰረተም ክልሉ አዋሳ ከተማን ያላካተተ መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ ማስገንዘብ ያስፈልጋል ። እነርሱ እኛ ከደቡብ ክልል ወጥተን የራሳችን ዞን ይኑረን እንዳሉትም፣ የአዋሳም ሕዝብ እኛ ከሲዳማ ዞን ወጥተን የራሳችን አስተዳደር ሊኖረን ይገባል ማለቱ አይቀርምና። ታዲያ ያለ አዋሳ ምን አይነት የሲዳማ ክልል ነው የሚመሰርቱት ?

ይልቅ የተሻለ መፍትሄ እንሆ፡

ለዚያ አካባቢ የተሻለ ነው የምለው የሲዳማ ዞንን፣ የጌዴዎ ዞንን፣ አዋሳ ከተማ ፣ በጌዴዎና በኦሮሞ ክልል ቦረና ዞን መካከል ያለው የኦሮሞ ክልል መሬት፣ በጌዴዎና በሲዳማ ዞን መካክል ያለውን የኦሮሞ ክልል የሰሜን ጉጂ ዞን መሬት አንድ ላይ በማድረግ፣ ዋና ከተማዉን አዋሳ ያደረገ፣ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል መስተዳደር መመስረት ይቻላል። በደርግ ጊዘ ሲዳማ  ይባል ነበር። ያኔ በነበረው የሲዳማ ክፍለ ሃገር የዘር ልዩነት ሳይኖር ነበር ሲኖር የነበረው። ስለዚህ መስተዳደሩ ሲዳማ መባሉ ችግር የለውም።በዚህ መስተዳድር ከአማራና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ወይ ሲዳምኛ፣ ወይ ኦሮምኛ አሊያም ጌዴኦኛ እንደ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል። ዘር፣ ብሄር የሚሉትን ከአስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ያወጣል። እኩልነት፣ እኩል ተጠቃሚነትን ያሰፍናል።