ቤቶች ለማፍረስ የአ/አ መስተዳደር ያወጣዉን እቅድ ሃላፊነት የጎደለው ሲል መኢአድ አወገዘው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


 

በሕዝብ ያልተመረጡትና ከአዲስ አበባ መስተዳደር ሕግ ውጭ በኦደፓ በምክትል ከንቲባነት ማ እረግ እንደ ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሕግ ወጥ ናቸው በሚል ከሰላሳ ሺህ በላይ  ቤቶች በአዲስ አበባ ለማፍረስ እቅድ እንዳለ መግለጻቸው ይታወሳል። ይሄንን ተከትሎ በአዲስ አበባ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ያለው የባልደራስ ባላደራው ምክር ቤት ጠንካራ የተቃዉሞ መግለጫ ያወጣ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ፣ የኦዴፓው አመራር ኢንጂነር ታከለ ፣ ቤቶች በርግጥም ህወ ወጥ ስለመሆናቸው ምንም አይነት ገለልተኛና ፍትሃዊ ማጣራቶች ሳይደረጉ ፣ ሊፈናቀሉ ያሉ ዜጎችም ቤታቸው ከመፍረሱ የተነሳ ሜዳ ላይ እንደማይወድቁ ምንም አይነት ማስተማመኛና ዝግጅት ሳይደረግ፣ ሌላ ስንት መሰራት ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ ቤቶችን ለማድፈስ መጣደፉ ሰብአዊነት የጎደለው ነው በሚል ጠንካራ ተቃዉሞና ትችት እያቀረቡ ነው።

የባላደራው ምክር ቤት ለሰጠውም ጠንካራ መግለጫ ጋአር በመሆን፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ሰኔ ሰባት ቀን ባወጣው መግለጫ በኢንጄር ታከለ የተሰጠው ቤቶችን የማፍረስ እቅድን አጥብቆ መቃወሙን ገልጿል። ” የከተማ አስተዳደሩ ለልማት በሚል ሰበብ ቤት አፍርሳለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን እንገልፃለን፡” ሲል ነበር መኢአድ በኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚመራውን የአ/አ ከተማ መስተዳደር ሕግ ወጥ ቤቶችን የማፍረስ እቅድ  ያወገዘው።

እንደ ለገጣፎ ባሉ አካባቢዎች በኦዴፓ ባለስልጣናት በርካታ ዜጎች በግፍና በጭካኔ መፈናቀላቸውም ይታወቃል። ተፈናቃዮችም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሲሆን ምንም አይነት መንግስታዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ መኢአድ ፣ ” በመዲናችን አዲስ አበባ ዙሪያውን በሚገኙ ከተሞች ያለአግባብ ቤታቸው ፈርሶ በሜዳ ላይ ወድቀው የሚገኙት ወገኖቻችን ረሃብና ጥም ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው አንድም የመንግስት አካላት እነዚህን ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አለመመላከቱ ድርጅታችንን እጅግ ያሳዘነ ነው” ሲል የተፈናቃዮች ጉዳይ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው ጠይቋል።

በአዲስ አበባ በተፈናቃዮች ዙሪያ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ወቅታዊ ጉዳይች ላይ መኢአድ ያውጣውን መግለጫ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ቀርቧል።

——————-

ህዝቡን ከአደጋ መጠበቅ  የመንግስት ተቀዳሚ ስራው ሊሆን ይገባል!!
ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ድርጅታችን መኢአድ ላለፉት 28 ዓመታት ሰፊ ድርጅታዊ መዋቅር ዘርግቶ ሲታገል እና ሲያታግል የቆየ አሁንም በመታገል ላይ ያለ ጠንካራ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አሁንም በህዝባችን ላይ በመድረስ ላይ ያለው የማያቋርጥ ግፍና መከራ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን፡፡

በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት በሚማሩ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል እንዲሁም በንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት ድርጅታችን መኢአድ አጥብቆ የሚያወግዘው መሆኑን እየገለፅን መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነቱን አልወጣም ብሎ በፅኑ ያምናል፡፡
የዚህ እኩይ ድርጊት ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች በውል ተለይተው የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ታወቀ ለህዝቡ መግለፅና ደግሞ እንደዚህ አይነት ሥርዓት አልበኝነት የወሰደው ድርጊት እንዳይፈፀም ማስተማሪያ የሚሆን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ብሎ ድርጅታችን ያምናል፡፡

በሌላ በኩል በመዲናችን አዲስ አበባ ዙሪያውን በሚገኙ ከተሞች ያለአግባብ ቤታቸው ፈርሶ በሜዳ ላይ ወድቀው የሚገኙት ወገኖቻችን ረሃብና ጥም ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው አንድም የመንግስት አካላት እነዚህን ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አለመመላከቱ ድርጅታችንን እጅግ ያሳዘነ ሲሆን በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ለልማት በሚል ሰበብ ቤት አፍርሳለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የነበረው አስተዳደር ህዝብንና ህግን መሰረት ያደረገ ሥራ መስራት የሚገባው ህዝብን ያገለለ እና ኢ-ፍትሀዊ በሆነ ውሳኔ የተሰሩ ህገወጥ ድርጊቶች ሁሉ አሁን ያለው አስተዳደር እየቀረቡ ያሉት የመብትና የጥቅም ጥያቄዎች መንግስትንም ሆነ  አገሪቱን ለከፍተኛ ወጭ መዳረጋቸው ግልፅ ሆኖ እያለ አሁንም በዚያው የስህተት መንገድ መከተልን የመረጠው አስተዳደሩ ኢህአዴግን አለ ለሚለው ለውጥ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ልማት ለአንድ አገር ህዝብ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም በለማና ፅዱ በሆነ አካባቢ ዜጎች የመኖር መብታቸውን የተጠበቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የሕዝብን መኖሪያ ቤት አፈርሳለሁ ብሎ ሲነሳ አስተዳደሩ ቤታቸው ለሚፈርስባቸው ዜጎች አማራጭ መጠለያ ማዘጋጀት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ድርጅታችን ያምናል፡፡ ይህ በእንዱህ እንዳለ በመዲናችን አዲስ አበባና በመላ ሀገሪቱ እየተከሰተ ያለው የኑሮ ውድነት እና እየጨመረ ያለው የዋጋ ንረት ህዝባችን ከመኖር ወደ አለመኖር ሥጋት ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በተደጋጋሚ የመብራትና የውሃ አለመኖር፣ የኑሮ ውድነቱን በከፍተኛ ሁኔታ እያናረው ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን በአገራችን ተከስቶ ያለው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ ሳይሆን በኢኮኖሚውም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሆኑም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው በመላ ሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች ጊዜው በጨመረ ቁጥር አደገኝነታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አያጠያይቅም፡፡
መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች

1ኛ. መንግስት ላወጣው ሕገ-መንግስት ተገዥ ሆኖ የዜጐችን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳሰባለን፡፡

2ኛ.ባለፉት ዓመታት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርን መሰረት ባደረገ ግጭቶች መከሰታቸውን እየታወቀ ክትትል አለመደረጉን እናወግዛለን፡፡3ኛ. በየዩንቨርስቲው በተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ አጥብቀን እያወገዝን ለችግሩ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ገለልተኛ አጣሪ ተቋቁሞ የችግሩ መንስኤ ተጣርቶ አጥፊዎቹ ለህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡

4ኛ. በአዲስ አበባና አካባቢው ቤት የፈረሰባቸው ወገኖቻችን አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው አሁንም ለዜጎች አማራጭ ሳይቀርብ ቤት አፈርሳለሁ የሚለውን አስተዳደሩ በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን፡፡

5ኛ. በውሃ፣ በመብራትና በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ ሀገሪቱም እያጣች ያለውን ገቢ ከግምት ውስጥ በማስገባት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

6ኛ. አሁን በአገሪቱ የተከሰተው ወረርሽኝ አስመልክቶ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እየጠየቅን የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎቻችን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም መላው ህዝባችን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ በሙያ፣ በቁሳቁስ፣ በጉልበት፣ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንድታደርጉ አስቸኳይ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፤ በየትኛውም አካባቢ እና በትምህርት ተቋማት ላይ እንዲሁም በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
ሰኔ 07 ቀን 2011 ዓ.ም.አዲስ አበባ