የህገ ወጥና ኮንትሮባንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች የኑሮ ውድነትን እያባባሰ መሆኑ ተገለጸ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ በመዲናዋ የሚከናዎኑ የህገ ወጥና ኮንትሮባንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርና እንዲባባስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር እና እንዲባባስ በሚያደርጉ የዘርፉ ተዋናዮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው ከሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር ምክክር ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከመዲናዋ የ10 ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ከ19 ወረዳ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ቢሮና የንግድ ጽህፈት ቤት የተውጣጡ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ህገ ወጥ የንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው በተለይም በሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ማድረሱን ምክትል ከንቲባው በምክክር መድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ግብዓት የሆኑ ብረቶች ላይም ተመሳሳይ ጭማሪ መታየቱም ተገልጿል።

ጭማሪው የተጋነነ እና የንግድ ስርዓቱ ግልጽነነት የጎደለው መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው በምክክር መድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡
በንግድ ስርዓቱ ላይ ምንም እሴት የማይጨምሩና ምርቶቹ ከተመረቱባቸው ወደ ነጋዴዎች በማቅረብ የሚሳተፉ ደላሎች ችግሩን ማባባሳቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና የክስ ምርመራ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ጥላዬ፥ ወፍጮ ቤቶች ያለደረሰኝ ገዝተው ያለደረሰኝ በመሸጥ በግብርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለዚህም ወፍጮ ቤቶች ሲገበያዩ ደረሰኝ እንዲጠቀሙ በማድረግ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ከፋብሪካ ጋር ትስስር የተደረገላቸው ዳቦ ቤቶችም ቢሆኑ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት የሚወስዱት ግብዓትና የሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ እንዳልሆነም በመድረኩ ተነስቷል።

ስጋ ቤቶች ላይም የዋጋ ጭማሪው እንዳለ ሆኖ የልኬት መሳሪዎቻቸው ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ ሀብታሙ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የግብርና ምርቶችን በአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኙ የተለያዩ መጋዝኖች በማከማቸት ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር የሚሰሩ አካላት እንዳሉም ነው የተገለጸው ሲል የዘገበው ኤፍ ቢሲ ነው፡፡