የአዲስ አበባ ጉዳይ አዴፓን ከኦዴፓ ወይም እነ ዶ/ር አብይን ከኦዴፓ መለየቱ አይቀርም #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

የአዲስ አበባ ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ መነጋገሪያ የሆነው፣ በዳዎድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ፣ በሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴፍ፣ በዶ/ር መራራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ እና ሌሎች ሁለት ደርጅቶች በጋራ ሆነው ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ ነው። “ኦሮሞ ካልሆነ አትጋቡ” ያሉት አቶ በቀለ ገርባ ነበሩ መግለጫዉን ያነበቡት። በመግለጫው የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሞው እንደሆነና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ፣ ኦሮሞው “አቃፊ” ስለሆነ መኖር እንደሚችሉ ነበር የተገለጸው። ልክ ኬኒያ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩት ማለት ነው።

የአዋሳው የኢሕአዴግ ጉባዬ ከመደረጉ በፊት ፣ ብአዴን ስሙን ወደ አዴፓ በቀየረበት የባህር ዳሩ ጉባዬ፣ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት የሚል አቋም ነበር ይዞ የተያዘው። በአዋሳው ጉባዬ የአዴፓ ተወካዮች ፣ የባህር ዳሩን ዉሳኔ በመያዝ፣ ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት በአዲስ አበባ ላይ አቋም እንዲወስድ ይጠይቃሉ። በዚህ ጊዜ አብዛኛው የኦህዴድ/ኦዴፓ ተወካዮች “ፊንፊኔ የኦሮሞ ናት” የሚል አቋም በመያዛቸው፣ ስብሰባው ሊረበሽ ሆነ። ዶ/ር አብይ አህመድ ጣልቃ ገብተው ለማረጋጋት ሞከሩ፤ “ጉዳዩን ሌላ ጊዜ እንመለስበት” በሚል። የአዴፓ ተወካዮች ግን “በዚህ ጉባዬ መወሰን ካልተቻለ መቼ ሊወሰን ነው ?” በሚል ጠንከር ያለ አቋም ያዙ። በወቅቱ በነበረኝ መረጃ፣  የአዴፓ፣ ህወሃትና ደሃዴን ተወካዮች በሙሉ ወይም አብዛኞቹ፣ እንዲሁም ወደ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት የተወሰኑ ኦዴፓዎች “ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናት፣ በተለይም ደግሞ የነዋሪዎቿ ናት” የሚል አቋም ያዙ። ይህ አቋም ግን በይፋ አልተገልጸም። አብዛኛው ኦዴፓዎችን ላለማስከፋት በሚልና በኦሮሞ ብሄረተኞች ዘንድ ጩኸት እንዳይሰማ ስለተፈለገ፣ ነገሩ ተሸፋፈነ።

የኦሮሞ ብሄረተኞች “ፊንፊኔ ኬኛ” ፖለቲካቸውን ቀጠሉበት። በኮንዶሚኒየም ዙሪያ እነ ጃዋር መሐመድ በቀሰቀሱት ረብሻ የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደገና አፍጥጦ መጣ። የሚያደራጀው ያጣው የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ አደራጅና የሚጮኽለት አገኘ። በነ እስክንድር ነጋ የሚመራ ፣ “አዲስ አበባ ለሁሉም ኢትዮጵያ፣ ሁሉም ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ” በሚል መርህ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ይህ እንቅስቃሴ የባለአደራ እንቅስቃሴ የሚል ስⷃሜ ያዘ።

አቶ ለማ መገርሳ በዉጭ አገር ህክምና ላይ እንዳሉ፣ በወ/ሮ ጠይባ ሁሴን የሚመራው የኦሮሞ ክልል መንግስት “የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሞው ነው፣ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ጥቅም መጠበቅ አለበት፣ ለኮንዶሚየም እጣ የደረሳቸው ቤታቸውን መረከብ የለባቸው” የሚል ጽንፈኛ ከኢሕአዶኤግ የአዋሳ ጉባዬ ውሳኔ ውጭ የሆነ መግለጫ አወጣ። ዶ/ር አብይ አሀመድ፣ የኦሮሞ ክልል መንግስት ያወጣው መግለጫ ከኢሕ አዴግ ዉሳኔና ከሕግ ያፈነገጠ መሆኑ በግልጽ ማሳወቅ ሲገባቸው ፣ ለነወ/ሮ ጠይባ ሁሴን መግለጫ ቦታ ሰጥተው፣ ከአዲስ አበባ መስተዳደርና ከኦሮሞ ክልል መንግስት የተወጣጡ ስምንት አባላት ያሉበት ኮሚቴ አዋቀሩ። ከነዚህ ስምንቱ አባላት አምስቱ ከኦህዴድ/ኦዴፓ ነበሩ። ሆኖም ኮሚቴው ከጅምሩ ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጠመው። የኮሚቴው አባል እንዲሆኑ የተመረጡት የአዴፓ ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤ ራሳቸውን አገለሉ። መጋቢት አንድ ቀን እነ እስክንድር ነጋ ባደረጉት ስብሰባ ላይም፣ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ “ኦዴፓ ከኦዴፓ ጋር ተደራድሮ በአዲስ አበባ ጉዳይ የመውሰን መብትም፣ የሞራል ብቃትም የለውም ብለው” ዶ/ር አብይ ያዋቀሩትን ኮሚቴ እንደማይቀበሉ አሳወቁ። የኮሚቴውን መቋቋም የገለጸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣም ደብዳቤ የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ፣ ኮሚቴው ፈረሰ። ዶ/ር አብይ ትልቅ የፖለቲካ ሽንፈት ተከናነቡ።

ከተቃዋሚ ድርጅቶች አብን ፣ አዲስ አበባ የነዋሪዎች ናት በሚል፤ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” የሚለውን የኦሮሞ ድርጅቶች የሚያቀነቅኑትን ዘረኛ ፖለቲካ የስግብግበነት ፖለቲካ ሲለው ተቃወመው። ጸረ-እኩልነትና አምርሮ የሚታግለው እንደሆነ በመግለጽ፣ ያለውን ግልጽ አቋም ይፋ አደረገ።

የአዴፓ የአዲስ አበባ አመራሮችና አባላት በአቶ ታከለ ኡማ አመራር ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከኢሕአዴግ አሰራር በጣም በተለየ ሁኔታ በይፋ አሳወቁ። በከተማዋ አስተዳደር የኦዴፓ አመራሮች ቁልፍ ቁልፍ ቦታውን እንደያዙ፣ ዘርና ጎጥ እየታየ ስር እንደሚሰጥ  ፣ ከኦዴፓ ውጭ ያሉ ሃላፊዎች እንደተነሱ ተናገሩ።  በአዴፓና በኦዴፓ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መጣ። አዴፓ በድጋሚ በአዲስ አበባ ላይ አቋሙን ግልጽ አደረገ። “አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት፣ የማንም ብቸኛ ክልል ንብረት አይደለችም” ብሎ።  በርካታ አፍቃሪ ኦዴፓ ጦማሪያን ብእራቸውን አዴፓ ላይ አነሱ።

ያለ አዴፓ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ በፌዴራል መንግስት ሃላፊነታቸው መቀጠል ስለማይችሉ፣ ከአዴፓ ጋር በአዲስ አበባ ጉዳይ የተነሳዉን ውዝግብ ለመፍታት፣ የአዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል፣ አቶ ብናልፍ አያለዉንና የአዲስ አበባ ዋና የኢሕአዴግ አመራሮች ያሉበት ስብሰባ አደረጉ። በስብሰባው ከፍተኛ ጭቅጭቅና ዉዝግብ የነበረ ሲሆን፣ ዶ/ር አብይ “የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሞው ነው” የሚለው አቋም የኦህዴድ/ኦዴፓ አቋም እንዳልሆነ መግለጻቸውን ምንጭች ይናገራሉ። ራሳቸውን ከኦሮሞ ክልል መንግስት አቋም ጋር በተጻረረ መልኩ። ሆኖም ግን ይሄን ከአዴፓ ጋር በተደረገው ስብሰባ ዶ/ር አብይ የተናገሩትን በይፋ ሊናገሩት አልደፈሩም።

በሌላ በኳል የሌላው የኢሕአዴግ አባል ድርጅት፣ የደሃዴን የአዲስ አበባ አመራሮች ፣ አዴⶒን ተከትለው፣ የኦሮሞ ክልል መንግስትን አቋም ውድቅ በማድረግ፣ “አዲስ አበባ የአገራችን መዲና እንደመሆኗ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የነዋሪዎቿ እንደሆነች” ባወጡት መግለጫ አሳወቁ።

በአዲስ አበባ የተመሰረተውና በእስክንደር ነጋ የሚመራው የባለ አደራ እንቅስቃሴ በሚያስደምም ሁኔታ በተለይም በአዲስ አበባ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጣ። አዲስ አበባ ሆነው ጦርንት እየመሩ፣ በሕዝብ ላይ ሽብር እየፈጠሩ፣ በይፋ “ትጥቅ አንፈታም” ሲሉ የነበሩትን፣ “የአፍ ወለምታ ነው” እያሉ ሲታገሱና ሲያባብሉ የነበሩት ዶ/ር አብይ አህመድ፣  የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የባለአደራ ምክር ቤት በአደባባይ ከመወረፍ አልፈው ዛቻና ማስፈራሪያ አቀረቡ። አህያዉን ፈርቶ ዳዉላውን እንደሚባለው ማለት ነው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ዛቻ ከሁሉም ማእዘናት እጅግ በጣም ከፍተኛ ወገዛና ተቃዉሞ አስነሳባቸው።

ዶ/ር አብይ የተነሳዉን ተቃዉሞ ለማለዘብ ነው መሰለኝ፣ የኦህዴድ ሃያ ዘጠነኛውን አመት አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር ፣ “አዲስ አበባ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ነቀምት ሄዶ እንደሚሰራውና የኔ ናቸው እንደሚለው ሁሉ፣ አዲስ አበባም ተመሳሳይ ነች፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ነች።” የሚል አስተያየት ሰጡ። ሆኖም ግን ይህ የዶ/ር አብይ አባባል የርሳቸው ድርጅት ኢሕአዴግ ከዘረጋው የፌዴራል አወቃቀርና ሕግ መንግስት በጣም የተራራቀ አባባል ነው። አሁን ባለው ሕግ መንግስትና አወቃቀር ነቀምቴና ጂማ የኦሮሞዎች፣ መቀሌ የትግሬዎች፣ ባህር ዳር የአማራዎች፣ አገዎች ..፥ እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን አይደሉም። አንዱ ችግር ይሄ ሆኖ እያለ፣ በነቀሜቴ፣ ጂማ  … ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች መብት እንደሚረገጥ፣  እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንደሚቆጠሩ እያወቁ፣  ነቀምቴና ጂማ ..ያሉት መስተዳድሮች ፍታሃዊና በ እኩልነት ላይ የተመሰረቱ ይመስል ፣ ነቀምቴ፣ ጂማ ..የየሁሉም ነው ብለው መናገራቸው፣ ሰው በሳንባ ነቀርሳ እየሳለ ጉንፋን ይዞታል እንደማለት ነው።  (በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)

ለማጠቃለል ይሄን ለብል። የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅነትን ያተረፈውን ኦዴፓ ክፉኛ ጎድቶታል። የኦዴፓና የዶር አብይ ተቀባይነት በእጅጉ አሽቆልቁሏል። በአዴፓና በኦዴፓ መካከል ውጥረቱ እንዳለ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም። ወይም አዴፓ ከኦዴፓ ተለይቶ ይወጣል አሊያም ዶ/ር አብይ ከኦዴፓ ይለያሉ። የአዴፓ ከኦዴፓ መለየት የዶ/ር አብይ አስተዳደር ፍጻሜ ይሆናል። ዶ/ር አብይ ወደፊት እንዳይሄዱ ያደረጋቸውን ጽንፈኛ ኦዴፓ ቆርጠው ከጣሉና ከአዴⶒ፣ ደሃዴንና ሞደሬት ከሆኑ ሕወሃቶችና ኦዴፓዎች ጋር ግንብር ፈጠረው፣ ዘር ላይ ያላተኮረ፣ እክሉነት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲዎች ይዘው ከወጡ፣ ያጡትን ተቀባይነት የመመለስ እድሉ አላቸው።  አሁን ግራፉ ላይ ተቀባይነታቸው ወደታች እየውረደ ነው። ወደ ታች መዉረዱ ቆሞ፣ ወደ ላይ ይነሳ ይሆን ?  ኳሷ በእጃቸው ነው ያለችው።

አዎን አንድ መሪ ጥሩ ሲሰራ መደገፍ አለበት። ዶ/ር አብይን ልንደገፍ እንፈልጋለን። በቃላት የተናገሩት ፣ ታላቂቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የመፍትሄዎች አካል መሆን እንፈልጋለን። ግን እርሳቸው  ጽንፈኞች ምሽግ ሂደው ከተወሸቁ እንዴት ልነግፋቸው እንችላለን። አዎን የሃያ ሰባት አመት ችግር በአንድ ጀምበር አይፈታም። ጊዜ ያስፈልጋል። ግን የሃያ ሰባት አመት ችግሮች እንደሚፈቱ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳለ የሚያሳይ ምልክት ካልታየ፣ እንደውም ሌሎች በፊት ያልነበሩ አዳዲስ ችግሮች እየበዙ ከመጡ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።