ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው!

በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ንብረት ማውደም፣ ዕገታና መሰል ድርጊቶች በተፃፃሪ ጎራ ለተሠለፉ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ሠርግና ምላሻቸው እየሆኑ ነው፡፡ በሴራ ፖለቲካ በተተበተበው የኢትዮጵያ አስፈሪ ሁኔታ ምክንያት፣ በአንድ ሰላማዊ ዜጋ ላይ የሚፈጸም ጥቃት የፖለቲካ ቁማር ማድሪያ ሲሆን በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡ የአንድ ግለሰብም ሆነ የብዙ ወገኖች አሳዛኝ ግድያ የፖለቲካ ቁማር እየሆነ፣ ይህንን አስከፊ ድርጊት በጋራ ማውገዝና እንደገና እንዳይፈጸም አቋም መያዝ ሲገባ ማዶ ለማዶ ሆኖ ጣት መቀሳሰር የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በቅርቡ በደራ በአንድ ወጣት ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ በአንድነት በማውገዝ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ፣ የራስን ጎራ ለመከላከል የተሄደበት ርቀት የጭካኔን ጥግ የሚያሳይ ነው፡፡ በእንዲህ መሰሉ አረመኔያዊ ድርጊት ተመሳሳይ አቋም አለመኖሩ አገር እንደሚያፈርስ ግንዛቤ ከሌለ በጣም ያሳዝናል፡፡

አገርን ከገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ለማውጣት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን በየፈርጁ የሚያቀርቡ ትጉኃን ያሉትን ያህል፣ ለችግር ፈቺ ጉዳዮች ጀርባቸውን የሰጡና ትርምስ ላይ የሚያተኩሩ ብዙ ናቸው፡፡ አገር ለገጠማት ፈተና ነባራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ያገናዘበ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሰዎች ተሞክረው መፍትሔ ያላገኙ ንትርኮች ላይ ጊዜ መግደል ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው በሁሉም አቅጣጫዎች ሰላምና መረጋጋት ሲፈጠር ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ሰላም ለማስፈን ተቀራራቢ አቋም መኖር አለበት፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የጠመንጃ ላንቃ መዘጋት ይኖርበታል፡፡ በየቦታው ግጭት ተበራክቶ መረጋጋት ሊኖር አይችልም፡፡ ከሰላም ቀጥሎ ሕዝቡ የሚበላው ምግብ፣ ልብስ፣ የሚጠለልበት ታዛ፣ የጤና ክብካቤ፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ማግኘት አለበት፡፡ እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ እየማቀቀ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የሴራ ፖለቲካ አብቅቶ ሰላም ይስፈን እያለ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ውስጥ የማውጣት አቅም ያላቸው ዜጎች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አቅም ጥበብን ከብልኃት ጋር አዛምደው ሲጠቀሙበት ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ አገር ለምትባለው የጋራ ቤት ማሰብ፣ አርዓያነት ያለው ሥነ ምግባር መላበስ፣ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ ከአድልኦ አሠራሮች በመላቀቅ ዜጎችን በእኩልነት ማስተናገድ፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እውነተኛውና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ማግኛ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ማመን፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከልብ መሥራት፣ ከአመፃና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ፣ ሕዝብን ማክበርና ለፈቃዱ መታዘዝ ከተቻለ የሕዝብ መከራ ይቀንሳል፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን በዋዛ አይደለም፡፡ በበርካታ አደናቃፊ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ሆኖም ለአገር ማሰብ ከተቻለ ከፀሐይ በታች የማይቻል ነገር የለም፡፡ መሰሪነትና ሴረኝነት በተፀናወተው ፖለቲካችን ለቅንነት አንድ ስንዝር ቢገኝለት ሕዝብ ሰላም አያጣም ነበር፡፡

በወጣቱ አረመኔያዊ ግድያ ምክንያት የተከሰተውን ሰሞነኛ የአገር ትኩሳት ማብረድ ከምንም ነገር በላይ የሚቀድም ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በብሔርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከአጋጠሙ ቀውሶች የባሰ አደገኛ ሥጋት ተደቅኗል፡፡ በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ተሿሚዎችም ሆኑ ሌሎች አካላት፣ በአገር ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ በቀና መንፈስ መነሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያጋጠመው ችግር በአግባቡ ተፈቶ አንፃራዊ ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ የሚታሰብ ከሆነ፣ አገር በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ በቅንነትና በስክነት ችግሩን በመፍታት አደጋውን ማስቆም ይገባል፡፡ ለስክነት፣ ለትዕግሥት፣ ለመነጋገር፣ ለመግባባትና በጋራ አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየት ጠቃሚ ነው፡፡ አጋጣሚዎችን አላስፈላጊ ገጽታ በማላበስ ጥላቻ የሚያስፋፉ አካላትን ወደ ጎን በማለት፣ አረመኔያዊውን ድርጊት በጋራ በማውገዝ ሰላም ማስፈን ይገባል፡፡

ብዙዎች እንደሚስማሙበት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የሚስተዋለው ትልቁ ችግር አለመደማመጥ ነው፡፡ መንግሥት ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ሲቀርቡለት በቅጡ ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ጎራዎች ውስጥ ያሉ ኃይሎች እርስ በርስ መደማመጥ አይፈልጉም፡፡ ጠያቂና ተጠያቂ አስተርጓሚ እስከሚያስፈልጋቸው ድረስ መግባባት ተስኗቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚስተዋለው አውቆ አጥፊነት፣ መደማመጥ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ትርጉሙ እንዲጠፋ እያደረገው ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ከአገር በላይ ራሳቸውንና ፍላጎታቸውን ያሳበጡ መነጋገርም ሆነ መደማመጥ እንዳይኖር እያሴሩ ውሉ የጠፋ ነገር በዝቷል፡፡ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ ይዋጣልን የሚሉ መፈክሮች የሚስተጋቡት፣ ከትናንቱ ስህተቶች ለመማር ካለመፈለግ እንደሆነ ከአሉታዊ እንቅስቃሴዎች መብዛት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ትናንት የተፈጸሙ ስህተቶች ኢትዮጵያን ከማሽመድመድ አልፈው፣ ለዘመናት ቁስሉ የማይሽር ደዌ ተክለውባት አልፈዋል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ የራሱ ተግዳሮቶች ሳይበቁት፣ ከትናንት በተላለፉ የታሪክ ዝንፈቶችና ትርክቶች ምክንያት ከባድ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሳዛኝ ሁኔታ ጭልጥ ብላ እየገባችበት ካለው የመከራ ዓውድማ ውስጥ እንድትወጣ ማድረግ የትውልዱ ኃላፊነት ቢሆንም፣ በግራና በቀኝ የፖለቲካ ጎራዎች ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ለሰከነ የፖለቲካ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ከፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ግጭት አንገፍግፏቸዋል፣ ሰላም ደግሞ ናፍቋቸዋል፡፡ ሕግ አክባሪ፣ እርስ በርስ የሚግባቡ፣ ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች የገነቡና ሰላም አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን በሴራ ፖለቲካ ሊንገላቱ አይገባም፡፡ ይልቁንም ሰላምና ፍትሕ ነው የሚገባቸው፡፡ እጅግ መራር ከሆነው የድህነት ኑሮ ተላቀውና ክብራቸው ተጠብቆ መኖር ሲገባቸው፣ በሴራ ፖለቲካ ሳቢያ በሚከሰቱ ግጭቶች ሰለባ እየሆኑ መቀጠላቸው አሳሳቢና ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ በሞታቸው፣ በሥቃያቸውና በመከራቸው የሚካሄደው የፖለቲካ ቁማር ያብቃ፡፡ በስማቸው መነገድ ማቆም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ጊዜ የማይሰጠው ተግባር የሚሆነው!